ኤልሮኢ:(⚜ምክረ አበው⚜)
የአንድ አባት ምክር
በአንድ ወቅት በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ተገኚቼ ነበር፡፡ በዚያ ገዳም የሚኖሩ አባት የነገሩኝ ነገር ለሕይወት መመርያ የሚሆን ነው፡፡ አሁን ከደረስንበት ወቅት ጋር የሚሄድ ነውና ላካፍላችሁ፡፡
በወቅቱ እንደ ዛሬው በቤተ ክርስቲያን ላይ የፈተና ማዕበል ተነሥቶ ነበር፡፡ ያ ወቅት የፖለቲካው ማዕበልም እጅግ ያየለበት ጊዜ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምንሰጠው አገልግሎት ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ምንስ ለውጥ ያመጣል? ችግሩ እንደሆነ እየባሰው እንጂ እየተሻለው አልሄደም፤ ታድያ ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን እና ዕውቀታችንን ዝም ብለን እየከሰከስን ይሆን? አሁን የኛ ልፋት የክፉ ሰዎችን ክፋት ለመሸፈን እና በክፋታቸው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ካልሆነ በቀር ችግሩን ይፈታዋል? ወዘተ፣ ወዘተ፣ ጥያቄዎች ይነሡ ነበር::
ያን ጊዜ እኒህ አባት እንዲህ አሉን፡፡
«ብዙ ልጆችን የወለደች የምትወድደው ባሏ የሞተባት አንዲት እናት ነበረች፡፡ ቤተ ዘመዶቿ ምንም ሳይራሩ ያለ ፍላጎቷ ለአንድ ክፉ ባል አጋቧት፡፡ ይህ ባል ግዴለሽ፣ ገንዘብ ወዳድ፣ ጠጥቶ ከመስከር፣ በልቶ ከመጥገብ፣ በስተቀር ሌላ ሞያ የለውም፡፡ ሲወጣ ሲገባ ይደበድባታል፡፡ እንጨት ሽጣ፣ ኩበት ለቅማ፣ እንጀራ ጋግራ፣ ጠላ ጠምቃ ያጠራቀመቻትን ገንዘብ ነጥቆ ይወስድባታል፡፡ ለዘመዶቹም ይበትነዋል፡፡
የት ትሂድ? የሠፈሩ ሕግ፣ ባህሉ እና ልማዱ፣ በሙሉ የእርሷን ሮሮ እና ልመና የሚሰማ አልሆነም፡፡ እርሱን እንደ ሕጋዊ ባልዋ ነው የሚቆጥሩት፡፡ የት ሂዳ መከራዋን ትናገር፡፡ የትስ ሂዳ ከችግሩ ትገላገል?
ይህ ክፉ ባልዋ እርሷን ብቻ ሳይሆን ልጆቿንም ያሰቃያቸው ነበር፡፡ እነርሱም በዚያ ቤት ውስጥ መከራውን እና ስቃዩን፣ ረሃቡን እና ጭቅጭቁን እየሰሙ መኖር መረራቸው፡፡ በዚያ ቤት ሰላም ጠፋ፡፡ ፍቅር ጠፋ፡፡ ምንጊዜም የሚሰማው ክፉ ነገር እና ልብ የሚያደማ ነገር ሆነ፡፡ ሰው ሁሉ ስለዚያ ቤት ያወራል፡፡ መንገድ ላይ ሲያገኛቸው ስለ ቤታቸው ይጠይቃቸዋል፡፡ እነርሱም በሃፍረት ይሸማቀቃሉ፡፡ ስለዚህም እናታቸውን ጥለው ወደ ሌላ ቦታ መሄድና ስለዚያ ቤት ከማያስቡበት እና ከማይሰሙበት ቦታ መድረስ ፈለጉ፡፡ የሚችሉትን ያህል እየሠሩ፣ ለራሳቸው የሚበቃቸውን እየኖሩ፣ መከራውን መገላገል እና እፎይ ብለው መኖር አሰኛቸው፡፡
ታድያ ይህንን ሃሳባቸውን ለአንድ ሽማግሌ ጠቢብ ሰው ነግረው ገንዘብ እና ሃሳብ እንዲሰጣቸው ፈለጉ፡፡ ሄደውም አማከሩት፡፡ ያም ሽማግሌ ሃሳባቸውን ሁሉ ከሰማ በኋላ እንዲህ አላቸው፡፡
«ልጆቼ ልክ ናችሁ ሩቅ ሀገር ሄዳችሁ፣ የምትችሉትን ያህል እየሠራችሁ፣ የራሳችሁን ኑሮ በመኖር ችግሩን ሁሉ መርሳት እና መገላገል ትችላላችሁ፡፡ ምን ያስጨንቃችኋል? ቤት ያለው እዚህ ብቻ ነው እንዴ? ሀገርስ ያለው እዚህ ብቻ ነው እንዴ? ግን አንድ ነገር አስቡ፡፡ እንዲህ ማድረጋችሁ ራሳችሁን ብቻ ከችግሩ ታወጣላችሁ እንጂ ችግሩን አትፈቱትም፤ እናንተ ችግሩን ትረሳላችሁ እንጂ ችግሩን አታስወግዱትም፡፡
«ደግሞም የእንጀራ አባታችሁ እናታችሁን የበደለውን ያህል እናንተም ትበድሏታላችሁ፡፡ እስኪ አስቡት ለዚህች ለእናታችሁ ከእናንተ በቀር የደስታዋ ምንጭ ማን ነው? ሁሉም ነገርዋ የሚያሳዝን እና የሚያስመርር ነው፡፡ እናንተ ግን የደስታዋ ምንጮች ናችሁ፡፡ የእንጀራ አባታችሁ እናታችሁን ያሳዝናታል፤ የእናንተ ጥላችኋት መሄድም ያሳዝናታል፤ እርሱ ብቻዋን እንድትለፋ ትቷታል፤ እናንተ ጥላችኋት ስትሄዱም ያለ አጋዥ ትተዋታላችሁ፤ እርሱ በመስረቅ ዘረፋት፣ እናንተም ባለ መስጠት ዘረፋችኋት፤ ታድያ ከእርሱ በምን ተሻላችሁ?
እናንተኮ ያሰባችሁት ለእናታችሁ ሳይሆን ለራሳችሁ ነው፡፡ እናታችሁ ስለተቸገረች አይደለም ያዘናችሁት፣ ችግሩ እናንተን ስለነካ ነው፤ እናታችሁ ስለተራበች አይደለም ያዘናችሁት ረሃቡ ስለነካችሁ ነው፡፡ በእናታችሁ ላይ የደረሰው ችግሳይሆን ስለችግሩ ከየሰው አፍ መስማት ነው የሰለቻችሁ፤ ችግሩን ለመቅረፍ አይደለም መሄድ የፈለጋችሁት፤ ችግሩን ላለማየት እና ላለመስማት ነው፡፡
ከዚያ ይልቅ ሥራ ሠርታችሁ ገንዘብ አግኙ እና ለእናታችሁ ምግብ ስጧት፤ የሚያስርባትን የእንጀራ አባታችሁን በዚህ ትቃወሙታላችሁ፣ ልብሷን ቀይሩላት፣ የሚያሳርዛትን አባታችሁን በዚህ ትቃወሙታላችሁ፣ ስትታመም አሳክሟት፣ የሚያሳምማትን የእንጀራ አባታችሁን በዚህ ትቃወሙታላችሁ፤ የወግ እቃዎቹን ሰብስቡና አስቀምጡላት፤ዝክረ ታሪኳን ሊያጠፋ የተነሣውን የእንጀራ አባታችሁን በዚህ ትቃወሙታላችሁ፤ እርሱ እያረጀ ሲሄድ እናንተ ግን እያደጋችሁ ነው፡፡ ስለዚህም እየበዛችሁ እና እየመላችሁ ሂዱና ይህንን ቀፍድዶ የያዛትን የመንደሩን ሕግ አስተካክሉት፡፡ ምናልባት የእንጀራ አባታችሁ ቢሞት ሌላ የእንጀራ አባት ደግሞ እንዳይተካ፡፡ እንደዚያ ካደረጋችሁ እናንተ የእናታችሁ ልጆች ናችሁ፡፡ ያለ በለዚያ ግን የእንጀራ አባታችሁ ተባባሪዎች ናችሁ፡፡
ሸረሪት ታውቃላችሁ፡፡ ከሰው ቤት ግድግዳ ላይ ድር አድርታ፤ ወልዳ ከብዳ ትኖራለች፡፡ ቤቱ በእሳት ሲያያዝ ግን ከቤቱ ወጥታ ቀድማ የምትሮጥ እርሷ ናት፡፡ ቤቱ የኖርኩበት ነው፡፡ ወግ መዓርግ ያየሁበት ነው፤ እሳቱን በማጥፋት አስተዋጽዖ ማድረግ አለብኝ አትልም፡፡ መሸሽን ብቻ ነው የምትፈልገው፡፡ ለራስዋ ብቻ ነው የምታስበው፡፡ ይህ ከሸረሪትነቷ የመጣ ነው፡፡
እናንተ ግን ሰዎች እንጂ ሸረሪቶች አይደላችሁም፡፡ ሰዎችን እያያችሁ ከሀገራችሁ እና ከቤተ ክርስቲያናችሁ ልትርቁ አትችሉም፡፡ አያገባንም ልትሉ አትችሉም፡፡ እሳቱን ማጥፋት ትታችሁ ከእሳት ለማምለጥ ብቻ ልትሮጡ አትችሉም፡፡ ይህንን ካደረጋችሁ ሸረሪቶች እንጂ ሰዎች አይደላችሁም፡፡» አሏቸው
ይህንን ሰምተው ልጆቹ ወደ እናታቸው ተመለሱ፡፡
እስኪ እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ የዚህች ሀገር እና የዚህች ቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ፍላጎት ምንድን ነው? ይህች ሀገር እና ይህች ቤተ ክርስቲያን ያለ ረዳት እንዲቀሩ ማድረግ አይደለምን? እናንተም እንተዋት፣ እናቁም፣ እንሽሽ ስትሉ ያለ ረዳት እያስቀራችኋት ነው፡፡ የእነርሱ ፍላጎት ኢትዮጵያን እና ተዋሕዶን ተስፋ ማስቆረጥ አይደለምን? እናንተም ተስፋ ከቆረጣችሁ ተሳካላቸው ማለት ነው፡፡ ልጆቻቸውን እያስመረሩ ማስኮብለል አይደለምን? ከኮበለላችሁ ተሳካላቸው ማለት ነው፡፡ ታሪክን፣ ቅርስን፣ ክብርን፣ ልዕልናን መመዝበር እና ማራከስ አይደለምን? እናንተም ታሪኩን፣ ቅርሱን፣ ባህሉን፣ ክብሩን ርግፍ አድርጋችሁ ትታችሁ በራሳችሁ ዓለም ብቻ ስትቀሩ የእናንት ፍላጎት ሳይሆን የእነርሱ ፍላጎት ተሳካ ማለት ነው፡፡
ታድያ አሁን እናንተ መመለስ ያለባችሁ አንድ ጥያቄ ነው፡፡ የምትፈልጉት የጠላቶቿ ፍላጎት እንዲሳካ ነው ወይስ በመከራ ውስጥ ያለችውና ቀን የጣላት የእናታችሁ ፍላጎት እንዲሳካ ? ምረጡ፡፡
✍ሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
@aleroe
@Alerobot