"ሰዎች ማን እንደሆኑ ሲያሳዩህ በመጀመሪያው ቀን እመናቸው" ትላለች ማያ አንጀሎ
ይህንን ጽሑፍ ከትናንት በስቲያ ጽፌው ስሜታዊ ሆኜ እንዳይሆን በሚል ትንሽ ቆይቼ ልመልከተው ብዬ አሳደርኩት:: በቆይታ ሃሳቤ ሊቀየር ስላልቻለ እንደወረደ ለጥፌዋለሁ:: የምናገረው ነገርም እሳቸው ስለ ድንግል ማርያም ከተናገሩት አይከፋም:: ነገረ ሃይማኖታዊ መልስ ከበቂ በአደባባይ ተሰጥቶበታል:: ጉዳዩ ላይ ግን የምለውን ልበል::
@diyakonhenokhaile
ፍኖተ ድድቅ የሚባል እባጭ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከወጣ ጀምሮ አንዴ ዘፈን በሚመስል መዝሙሩ ፣ አንዴ ምንፍቅናን በሚያገሣ ስብከቱ ምእመናንን ሲያወዛግብ ሰንበትበት ብሎ ነበር:: ጌታ በወንጌል "ኀበ ሀሎ ገደላ ህየ ይትጋብዑ አንሥርት" "በድን ባለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ" እንዳለው የፍኖተ ድድቅ ባለቤት ሙዳ ሥጋ ይጥላል ብለው ተስፋ ያደረጉ ሰዎች ዙሪያውን ስለከበቡት ላለፉት ጥቂት ዓመታት ቤተ ክርስቲያን ከነንፍጡ ካልወደደችው ብለው ሲሟገቱ ከርመዋል:: በመሠረቱ ሁኔታው ሰውዬው ደኃ ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ተወግዞ ነበር እንድል ያደርገኛል:: ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ማኅበር ለማጥራት ጊዜው አሁን ነው::
"ከእኛ ወገን ነህ ወይንስ…?" የሚል ኢያሱያዊ ጥያቄ ለመጠየቅ ጊዜው አሁን ነው::
ሰሞኑን ደግሞ በፖለቲካ ቤዛነት የተሾሙ የሆኑ አንድ ጳጳስ ድንግል ማርያም ቤዛ አትባልም ብለው በፍኖተ ድድቅ አዳራሽ ሲያስጨበጭቡ ሰማን:: ከንዑሰ ክርስቲያን ያነሰ እውቀት ያላቸው እኚህ ጳጳስ ሽልማት እንደሚጠባበቅ አዝማሪ ሰውዬውን ያስደስታል ብለው ያሰቡትን ሁሉ ሲዘባርቁ ነበር::
ከቅርብ ዘመናት ወዲህ እንደ ፓስተር ለማውራት የሚጋጋጡ አባቶች ማየት ከጀመርን ሰነበትን:: አይናቸውን አስሬ የሚጨፍኑ ፣ በግድ እየጨመቁ ዕንባ ለማውጣት የሚታገሉ ፣ ከአሁን አሁን በልሳን ለፈለፉ ብለን በስጋት የምናያቸው ምሁር ለመባል የቤተ ክርስቲያንን ነባር እሴቶች የሚያጣጥሉ የቤተ ክርስቲያን ማድያቶች ብቅ ብቅ ካሉ ሰነበቱ::
ያሁኑ ጳጳስ ትንሽ የሚለዩት ምንም ፈሊጥ የሌለው ያልተለሳለሰ $@&@@ ስለሚናገሩ ብቻ ነው:: የሆነ ቪድዮ ላይ Faith Alone የሚለውን የሉተር ትምህርት የኦርቶዶክስ ቆብ ደፍተው ሲሰብኩ ትንሽ እንኩዋን አላፈሩም:: በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተሹመው ተሸልመው ክህደት እያስተማሩ መቀጠል እንደማይቻል ለማሳየትና አንዴ ከጰጰሱ ምንም አይኮንም ዓይነት አመለካከትን ለማረም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ዕድል ሊጠቀም ይገባዋል:: በ3ኛው ክፍለ ዘመን ጳውሎስ ሳምሰጢ (Paul of Samosata) በአንጾኪያ ሲኖዶስ የተወገዘው ፣ ንስጥሮስ በ4ኛው ክፍለ ዘመን የተወገዘው ጳጳስ ከሆኑ በኋላ ነው:: ቤተ ክርስቲያን መና () —ንን ለመለየት ጵጵስናቸውን ፈርታ አታውቅም::
@diyakonhenokhaile
በወላዲተ አምላክ የነገረ ድኅነት ሱታፌ ላይ በጳጳስ ደረጃ ሲቀለድ አይተን ዝም ልንል አንችልም:: ከቅዱስ ሲኖዶስ ጠንከር ያለ ውሳኔ እንጂ ማስተባበያ አንጠብቅም:: የተነቃነቀ ጥርስ ቀን ይጠብቃል እንጂ መውለቁ አይቀርም:: እንደ ተራ ስኅተት ይቅርታ እንዲጠይቁም አንጠብቅም:: ያስተማሩት የታሰበበት ክህደት ነውና የተብራራ መልስ ከቀኖና ጋር እንጠብቃለን:: "የበራላቸው" ለመባል የብርሃን እናትን ሊጋርዱ የሚጥሩ ሰዎች ማላገጫ ሆነንም አንቀርም::
ሙሴ ቤዛ በተባለበት መጽሐፍ ቅዱስ እያመኑ ድንግል ማርያም ቤዛ አትባልም ላሉት ጳጳስ ቅዱስ ሲኖዶስ ቤዛ ሲሆናቸው ማየት አንፈልግም:: ጠንከር ያለ ቀኖናዊ እርምጃ እንጠብቃለን::
ርጉመ ይኩን ዘይረግመኪ
ወቡሩከ ይኩን ዘይባርከኪ
ነገራተ ክልዔ ኢይርሳዕ ልብኪ
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ገሊላ ፳ኤል
ሚያዝያ 15 2017 ዓ.ም.
#share
@diyakonhenokhaile