የዲያቆን አቤንኤዘር ተክሉ ገጽ


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha


Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Statistika
Postlar filtri


ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት በሰማይም፤ በምድርም የሚመስለው የለም!


ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስለ ክርስትና የምራቸውን ነው?

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በዛሬው የፓርላማ ውሎአቸው እንዲህ አሉ፤

" ... ክርስትና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ተመሥርቶ የትም ዓለም ሳይስፋፋ የገባው ኢትዮጵያ ነው። ያ ክርስትና ድህነትን ለመምታት "tool" (መሣሪያ ለማለት ይመስለኛል)ኾኖ ማገልገል ነበረበት። ነበረበት ነው አላገለገለም።..." ብለዋል።

በተደጋጋሚ እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ወቀሳ፣ ኦርቶዶክስን ከግብጽ ቤተክርስቲያን ጋር አያይዞ ማቅረብ እንግዳ ነገር  አይደለም። ይህ የሚሉ ሰዎች እንኳ፣ ሙሉውን የኦርቶዶክስ ክርስትና፣ በደፈናው ሲያጠለሹ አንመለከታቸውም። ከዚህ ዘልሎ ግን በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ክርስትና ጠቅላላው ድህነትን ለመምታት "ያላገለገለ መሣሪያ" ነው ማለት ለእኔ ከባድ ጽርፈት ነው። በሥራ ሕይወታቸውም ኾነ ባህላቸውም አንቱ ተብለው የተከበሩ አገልጋዮችም፤ አማኞችም የነበሩአትና ያላት ርትዕት ክርስትና ዛሬም አለችና!

ይልቁን በክርስትና ስም "ሥራ ፈትና አጭበርባሪ፤ እልል ያሉ ወንበዴ ነቢያትና ሐዋርያት፣ በመንግሥት ስም በተቋቋመ ባንክ ስም ብር የሚያበዛ ATM በጉባኤያቸው ሲያድሉ የሚውሉ፣ ብር አበዛን የሚሉ አለሌ ጌቶችን" በክርስቲያንነት ቆጥረው ከኾነ ልክ አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ያሉ "ነቢያትና ሐዋርያት" ከምንጊዜውም በላይ በርሳቸው ዘመን ነውና የበዙት አደብ ቢያሲዙልን መልካም ነው። ቃሉም፦ “ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች ናቸው...፤(ሮሜ 13፥3) ይላልና።

ነገር ግን አንድም ጥናት ባልቀረበበት፣ በደፈናው ክርስትናን እንዲህ ማዋረድ ከአንድ መሪ ፈጽሞ አይጠበቅም። የክርስትና ግልጽ መርህ፣ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ”(2ተሰ. 3፥10) ብሎ እንኳን አለመሥራትን፣ ሥራ አለመውደድን የሚጠየፍ ነውና።

የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek

440 0 2 11 17

የአጫብር ከበሮ ስልተ ምት ሊቅ ሊቀ ጠበብት ጥበበ ደጉ፣ ለወንጌል እንደ ተነቀፉ፤ በስሙ መከራን ተቀብለው "በሆዳቸው ሳይወድቁ" ስሙን እንዳስከበሩ የኖሩ አባት። በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተስፋ እንዳንቆርጥ ከሚያደርጉት ዕንቁ አባቶች መካከል አንዱ ናቸው።

በወንጌል ስም እንደ ተነቀፉ ኖሮ በዚያው እንደ ተጠሉ መሞት መታደል ነው!

የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek


እግዚአብሔር ኀጢአትንና ኀጢአተኝነትን ይጠየፋል!


መስመር ለዩ እንጂ!

“... በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤”(ቆላ. 3፥16) እንዲል ቅዱስ ቃሉ፣ ዝማሬ ለጌታ ክብር ብቻ የሚቀርብ ቅዱስ አምልኮ ነው። በሌላ ስፍራም፣“በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤”(ኤፌ. 5፥19) ተብሎአል።

ይህ ሊለወጥ የማይችል እውነት በሰማይም ጸንቶ አለ፤ “በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ ... በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም[ለክርስቶስ] ይሁን ሲሉ ሰማሁ።”(ራእ. 5፥13) እንዲል፣ ፍጥረተ ዓለሙ ከበጉ በቀር ለሌላ ለማንም የዝማሬ ኃይሉን አይሰጥም።

ታድያ ከሰሞኑ እኒህ ኹለት ዘማርያን ዝማሬ አውጥተዋል። የዝማሬ ሰንዱቃቸውን ቁጥር ሲሰጡ፣ ትዝታው ቁ. 8 ያለ ሲኾን፣ ሐብታሙ ደግሞ ቁ. 7 ብሎ ነው። ኹለቱም ኦርቶዶክስ ቤት እያሉ ያወጡትን ዝማሬዎቻቸውን ጭምር ቆጥረው ነው እዚህ ቁጥር ላይ የደረሱት። ግን በምን መመዘኛ?! ኹለቱም እስከ ቁ. 5 በሠሩአቸው ሥራዎች "ምርቅና ፍትፍት" በአንድነት ነበር ያቀረቡት።

ትዝታው፣ "እኔስ አልፈራም ድንግልን ይዤ" ብሎ፤ ሐብታሙ ደግሞ "ጻድቃኔ ማርያም ደጓ እናቴ" ብለው የሸቀጡበትን ቆጥረው ማለት ነው። ብዙዎች "አያይ ይኸንማ እንዴት ይቆጥሩታል? በአደባባይ ሲቃወሙ አይደል ወይ የምናያቸው?" የሚሉ ይኖራሉ። ጥያቄው ግን መልስ የማያገኘው፣ ዘማሪዎቹ የሸቀጡትንም፤ አምነንበታል ያሉትንም ምንም መስመር ሳያበጁለት ይኸው ሲቆጥሩልን ስናይ ነው።

ኦርቶዶክስ ቤት ያወጣችኹትን "ዝማሬ" ከወደዳችኹት መቁጠር እንዳታቆሙ! ፍጡር ያስመለካችኹበትን ያንን ሥራችኹን ዛሬም የምትቆጥሩ ከኾነ፣ አፍና ልባችኹ አልተስማማምና እስኪ ብትችሉ መስመር ለዩ!


"ሕጋዊ ከለላ ያስፈልገናል"

ኹለቱ "አባይ ነቢያት" የጋራ ግንባር የፈጠሩ ይመስላል። ግንባር የፈጠሩት ደግሞ፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ለመፈጸም አይደለም። ስድብ በዝቶብናልና የሕግ ከለላ ያስፈልገናል ሊሉ ነው። አለመታደል። የሕግ ከለላ እኮ የሚሰጠው፣ በሕጉ መሠረት ሕጋዊ ሥራን ለሚሠራ ሰው ወይም ተቋም ነው።

እኒህ፣ የጽድቅ አገልጋዮች ቢኾኑ፣ መነቀፍና መተቸትን እንደ የደስታ ምንጫቸው እንጂ ፈጽሞ ሊጠሉት አይችሉም ነበር። ቅዱስ ቃሉ በግልጥ እንዲህ ይላልና፣

"ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።" (ማቴ. 5፥11-12)

እኒህ ግን ጌቶችና አለቆች እንጂ አገልጋዮች አይደሉም፣ ከጌታ ኢየሱስ ይልቅ ራሳቸውን ማስከበር ይፈልጋሉ። በርግጥ ሕግ ቢኖርና ቢዳኙ፣ እንደ ኢዩ ጩፋ አይነቱ ሰው፣ ስፍራው ከርቸሌ እንጂ፣ ሕግ ከለላ መጠየቅ አልነበረም። ሌላው የሚያሳዝነኝ፣ ያ ኹሉ "የሕዝብ መንጋ" በጩኸት ማጨብጨቡ።

የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek


ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት፣ የሰሞኑ " ቤተክህነት ውስጥ አፍጥጦና አግጦ የታየው ጉበኝነትና የለየለት ስርቆት" እንደ ለምጽ የነደደ ምስክር ነው። ይህ እንኳ እየታየ ለመመለስ፣ ለመስተካከል ከሚደረገው ጥረት ይልቅ በማናቸውም መንገድ ተሐድሶን መግፋትና መጥላት ተያይዘውታል።

እኛ ኦርቶዶክስ፣ ተሐድሶ ያስፈልጋታል ስንል "ጴንጤ አልያም የፕሮቴስታንት ቅርጽ ሊኖራት ይገባል" እያልን አይደለም። ለወንጌል እውነት ተገዝታ፤ በትምህርቷና በሕይወቷ ወንጌል፤ ወንጌል እንድትሸትት፤ እግዚአብሔርን ከምታስቀናበት የፍጡር አምልኮ ነጻ እንድትወጣ ... በባህሏና በዐውዷ ወንጌል ይስረጽ እያልን ነው። ይህ ባይኾን ግን የደነደነ አንገት መሰበሩ አይቀርም።

የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek


አዲስ አበባ ሐ/ስብከት 27Mil. ብር ከባንኮች ጋር ተሻርኮ ሰ*ለቀ*ጠ፤ ለቅጥር እስከ 1Mil. ብር ጉቦ ይቀ*በላል ... ይህ የቅርቡን ይቅርና የሩቁንም ጆሮ ጭው ያደርጋል! አቤቱ ማረን! ይቅር በለን!


በኢትዮጵያ ምድር፣ ሰብዓዊነት ነግሦ ዓይ ዘንድ ምኞቴ ነው፤ ሰብዓዊነት፦ ሰው፤ ሰው መሽተት። ሌላው ኹሉ ቀጥሎ የሚደርስ ይመስለኛል።


ኤርምያስ፤ ፍርድና ተስፋን ተናጋሪ ነቢይ!


የእስራኤልን ወደ ባቢሎን መማረክ፣ ፊት ለፊት ከተናገሩት ነቢያት መካከል ቀዳሚው ነቢዩ ኤርምያስ ነው። ነቢዩ ዘመኑን በእንባና በልቅሶ ያሳለፈና አብዝቶ ከማልቀሱም የተነሣ “አልቃሻው ነቢይ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ነው። የኤርምያስ ዘመኑ ብቻ ሳይኾን ሕይወቱም ጭምር አሳዛኝና በሕመም፤ በሰቆቃ የተሞላ ነበር።


የእግዚአብሔርን ፍጹምና እውነተኛ ቃሎቹን በግልጽ ማለትም፣ ኢየሩሳሌምና ሕዝቦችዋ እንደሚማረኩ (ኤር. 8፥18፤ 13፥17) በመናገሩና ለባቢሎን ንጉሥ እንዲገዙ፣ እጅ እንዲሰጡ ከእግዚአብሔር የተላለፈውን ትእዛዛዊ ትንቢት በመተንበዩ ተጠላ፤ ብዙዎችም ሊገድሉት አሰቡ (ኤር. 11፥21፤ 26፥11፤ 36፥26፤ 38፥6)። በዚህ ሳይበቃ በእግር ግንድ ተያዘ፤ በጭቃ ጕድጓድ ውስጥም ተጣለ፤ ተወረወረም፤ (20፥2፤37፥13፤38፥28)፤ እያበደ ትንቢት የሚናገር ሰው ተባለ (29፥26)። ከዚህ በዘለለ አስቀድሞ ሊመጣ ያለውን ጥፋት ስላየለት፣ ከሚደርስበትም ጥልቅ የመንፈስ ስብራትና ሐዘን ሊጠብቀውም ስላሰበ ሚስት እንዳያገባ፣ ልጆችን እንዳይወልድ፣ ወደ ግብዣና ልቅሶ ስፍራም እንዳይሄድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ከለከለው (ኤር. 16)።

ይህ ኹሉ በኤርምያስ ሕይወት የኾነው፣ የእስራኤልን ኀጢአት በመግለጡና ይህን ተከትሎም የሚመጣውን አይቀሬውን ፍርድ በመናገሩ ምክንያት ነው። በተደጋጋሚ በብዙዎች ዘንድ የመጠላቱና የመገፋቱም ምክንያት “ከዚህ ፍርድ ታመልጡ ዘንድ፣ ንስሐ ግቡ” ማለቱ እንጂ ሌላ አልነበረም። ነቢዩ በተለይም እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን ሕዝቦቿንም ጭምር እጅግ በመውደዱ ምክንያት (ኤር. 8፥18፤ 13፥17) የሚደርስባቸውን መከራና ሰቆቃ በማስተዋል ፍጹም አዝኖአል፤ ተጨንቆአል፤ ተሰቃይቶአል። እስራኤልና ኢየሩሳሌም ግን ይህን ጥልቅ ሐዘኑንና ስብራቱን ፈጽሞ አላስተዋሉለትም። የምርኮውን ፍጻሜ እንደምናስተውለውም ኤርምያስ በፍጻሜው ከሕዝቡ ጋር አብሮ የምርኮው ገፈት ቀማሽ ኾኖአል፤ አብሮ ሰቆቃውን ተሰቅቆአል።

ይህ ነቢይ በዚህ ጥልቅ መከራ ውስጥ ቢያልፍም፣ ነገር ግን ስለ እስራኤል ተስፋና ተሐድሶ ከመናገር ከቶውንም ቸል አላለም። ራሱም ነቢዩ እንኳ፣ “ለዚህም ሕዝብ የተመሸገ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤ ይዋጉሃል እኔ ግን ለማዳን ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም።” (ኤር. 15፥20) የሚለውን የአምላኩን ቃል በመታመን፣ እግዚአብሔርን እንደ ተስፋው እጅግ አድርጐ ይጠብቀው ነበር።

እግዚአብሔር በኀጢአታችን ፈጽሞ ቢቀጣንም፣ ርሱ ግን “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ።” (103፥12) እንዲል፣ በደላችንንና ኀጢአታችንን ፈጽሞ ያርቃል፤ ይቅርም ይለናል። የፍጻሜ ተስፋውና ዕቅዱ እኛን ማዳንና መመለስ ነው። ዘወትር ግን መዘንጋት የሌለብን እውነት አለ፤ እርሱም እግዚአብሔር ኀጢአትን ፈጽሞ ይጸየፋል፤ አይወድም፤ ርሱም እጅግ ከክፋት የራቀ አምላክ ነውና።

ዛሬ በምድራችን ላይ የምናየው ሰቆቃና ዋይታ፤ ዕንባና ጥልቅ ሐዘን የእግዚአብሔር ልብ ላላቸው እውነተኛ አማኞች ፈጽሞ እፎይታ የሚሰጥ አይደለም። እንደ ኤርምያስ አልቃሻና “ነጭናጫ” የሚያደርግ ነው። አገራችንን ጨምሮ በምድራችን ላይ አያሌ ስፍራዎች እጅግ አሰቃቂ ጦርነቶች እየተደረጉ ነው፤ ሰዎች በብዙ ዓይነት ጎዳናዎች በሞትና በሰቀቀን መንገድ ሕይወታቸው እያለፈ ነው። በስደት፣ በርስ በርስ ጦርነቶች፣ በራብ፣ በቸነፈር … ወንጌል ሳይሰሙና ሳይደርሳቸው የሚሞቱ ሰዎች እጅግ በርካቶች ናቸው።

ይህን ኹሉ በማየት ለመላለሙ ልትማልድ የተጠራች ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር ብትኖርም፣ እንደ ስሟ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ደካማ ይመስላል። ከገዳዮች ጋር ትኹን ከሟቾች ጋር፣ የቱ ጋር እንዳለች ሚናዋ ግራ ያጋባል፤ የራሽያና የዩክሬን ጦርነቶችን ባራኪዎቹ “ጳጳሳት” ነበሩ፤ በኛም ምድር ላይ የተደረጉትን ጦርነቶች ባራኪዎቹ ጳጳሳትና ፓስተሮች ነበሩ፤ ይህ እጅግ በጣም ቅስም የሚሰብር፤ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነው።

እንደ ኤርምያስ፣ ከክፋቱ ጋር የማትተባበር፤ ዓመጻን የምትጠየፍና የምትጠላ፤ ከእግዚአብሔር የሚመጣውን የጽድቅ ፍርድ ሳታወላዳ የምትናገር፤ የኀጢአትን መራርነት በጽኑ የምትመሰክር፤ ደግሞም ተስፋንና ምሕረትን፤ ይቅርታንና ተሐድሶን ለሕዝቡ የምታሳይ ቤተ ክርስቲያን፤ እንዲኹም ጽኑ ዕንባ፤ ጠንካራ ሐዘኔታ ያላቸው አገልጋዮችና አማኞች ያስፈልጉናል።

ነቢዩ ኤርምያስ እጅግ የምወደው ነቢይ ነው፤ ለኪዳኑ ሕዝብ እንዳለቀሰ፤ ከኪዳኑ ሕዝብ ጋር መከራ እንደ ተካፈለ በፍጻሜውም ከኪዳኑ ሕዝብ ጋር አለፈ፤ ቤተ ክርስቲያን እንደ ኤርምያስ በሚደነግጥና በሚራራ ልብ እንድትገለጥ ብርቱ መሻቴ ነው!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

የጡመራ መድረክ አድራሻ - https://abenezerteklu.blogspot.com/2024/10/blog-post.html
የኦሮሚኛና የአማርኛ መልእክቶችን ለማግኘት - https://www.youtube.com/@-abenezertekludiyakon8842


ከዚህ በላይ ቤተክርስቲያን እንደምትሳሳትና እንደ ወደቀች ምን ዋቢ አለ?!

አባ አብርሃም እንዲህ ይላሉ ...

“ቤተ ክርስቲያን የሙሰኞች ዋሻ ሆናለች የሚለው ዘርፈ ብዙ ፍርጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንጂ ሲቀንስ አይታይም ... ይህ ለምን ሆነ ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ እውነታውን በመጋፈጥ ችግሩን ለማስቆም ከመትጋት ይቅል ቸልተኝነት እየመረጥን በብዙዎቹ መሥዋዕትነት የሚሰበሰበው ሀብት እንዲመዘበር የተስማማን በሚመስል ሰምተን እንዳልሰማን መሆናችን እንደሆነ ...” ጠቁመው በተጨማሪም፦“... ይህን አስነዋሪ ድርጊት እያወገዝን እውነትን ተላብሰን ከሙሰኞች የጸዳችና የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለተተኪው ትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል።” ... በማለት መልዕክታቸውን ሲቋጩም፦“ርትዕ የሰፈነባት ቤተ ክርስቲያንን ለተተኪ ትውልድ ለማስረከብ እንትጋ።”

ብለዋል። እና ከዚህ በላይ የተመሠከረለት ውድቀት እያለ ንስ መግባትና መመለስ አይቀልም ወይ?!

(ምንጭ ዜና ተዋሕዶ)

የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek


ስለ እ*ስራ*ኤ*ል ሲነሣ አብዛኛው የወንጌላውያንና የኦርቶዶክስ አማኝ ለየት ያለ ስሜት ይሰማዋል። እና ስለ ፍልስጥኤማውያን ክርስቲያኖችና በዚያ እየተፈጁ ስላሉ ሕዝቦች ደግሞ ብዙም ግድ አይሰጣቸውም። ነገር ግን የእስ*ራኤ*ል ሃይማኖት መሪ በግልጽ፦

"እኛ የምንይዘው ቦታ ኹሉንም አብያተ ክርስቲያናት እናፈርሳለን።"

ይህንም የእስራኤል አምላክ አዝዞናል ብሎአል። እንግዲህ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የገባውን የመላለሙን ኪዳን እያጣጣሉ፣ ለእስራኤል የተለየ ተስፋና ኪዳን አለ ለማለት፣ አንዴ ባንዲራቸውን በግል "አጥቢያቸው" ተክለው አልያ ልብሶቻቸውን ለብሰው "በቤተክርስቲያን ላይ ለሚሸቅጡ"፣ ይህን መራራ ነገርም አብረው እንዲቀበሉ እንላለን። ቅዱሱ መጽሐፍ ግን እንዲህ ይላል።

“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።”(ገላ. 3፥28)

የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek


በጅማ ሊሙ ገነት፣ ወንጌልን በብዙ ተቃውሞ ውስጥ እያገለገላችኹ ላላችኹ ወንድሞችና እህቶች ጸጋና ሠላም ይብዛችኹ፤ እናንተ ብትታሠሩ ወንጌል አይታሠርም፤ ለኦርቶዶክስ ዛሬም ወንጌል ይሻላታል እንላለን!


በምድር ላይ የእግዚአብሔር ትልቁ አጀንዳ፣ ልጁ ኢየሱስና ቅዱሱ ወንጌል ብቻ ናቸው!


በግሪኩ አርዮስፋጎስ ሜዳ፣ በኢትዮጵያውም የኢሬቻ ሖራ፤ "ስበክ!" ተብዬ ዕድል ቢሰጠኝ፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ርዕሴ የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻ ነው!




ባህል፣ ማኅበራዊ እሴት፣ አገር ወዳድነት ... የቱንም ስም ስጠው፣ ኢየሱስ የሌለበት የቱም ኅብረት፤ የቱም ጉባኤ የቱም ደማቅ ስብስብ ... ለሰው ሥርዓት ከኾነ እንጂ ለወንጌል እውነት ባዳና ባዕድ ነው!


“አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” (ማቴ. 16፥16)


ጌታችን ኢየሱስ፣ በምድርም ኾነ በሰማይ ካለ ከየትኛውም ፍጡር፣ ባህልና ልምምድ፤ ከየትኛውም የዓለም ሥርዓትና አስተዳደር ጋር አይወዳደርም! ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን በማስተዋል ነው፣ የተገለጠለትን እውነት የመሰከረው። ይህ ቅዱስ ምስክርነት፣ ክርስትና ተንጣልሎ የተመሠረተበት ሕያውና ዘላለማዊ መሠረት ነው። የቤተ ክርስቲያን ሕይወት፣ ተልእኮ፣ ታላቅ ተስፋና ዘላለማዊነት የተወሰነውና የሚጸናው፣ ይህን ታላቅ ምስክርነት በመቀበልና በማመን ብቻ ነው።


ይህን ምስክርነት የሰጠው፣ በሰማይ አምላክ በእግዚአብሔር አብ ገላጭነት ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፤ ታላቁ መጽሐፍ፣ “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።” እንዲል (ማቴ. 16፥17)። ያለ አብ ገላጭነት ይህን እውነት መመስከር የሚቻለው ማንም የለም።

እግዚአብሔር አብ፣ ዛሬም ስለ ልጁ ጮኸን እንድንመሰክርለት ይሻል፤ መንፈስ ቅዱስም እንኳ፣ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐ. 14፥26) ብሎ እንደ ተናገረ፣ ርሱም የሚመሰክረው ስለ ብላቴናው የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው።

አብም፤ መንፈስ ቅዱስም የሚመሰክሩለትን ይህን ጻድቅ ብላቴና፣ ቤተ ክርስቲያንም ትመሰክለት ዘንድ ተጠርታለች። በተለይም በቅዱስ ጴጥሮስ አንደበት፤ በአብ አባታችን ገላጭነት የተገለጠውን እውነት፣ ቤተ ክርስቲያን ድምጽዋን አሰምታ መመስከር ከተሳናትና ለዚህ እውነት ያላትን ታማኝነት ካጎደለች፣ ተልእኮዋን መፈጸም የተሳናት፤ ደካማ፤ በአቅራቢያዋ ካሉ ዓለማዊና ብሔር ተኰር ባህላት ጋር በቅይጥነት ለመኖር የምትጎመጅ ልትኾን ትችላለች።

ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሕያው ምስክር ናት፤ ለመሲሑና ለሥራዎቹ፤ ላዘዛትም ተልእኮው በትክክል ካልታዘዘች፣ ፍጻሜዋ አስፈሪና የተጠራችለትን ሕያው ምስክርነት በዓለሙ ፊት የምትጥል ተላላ ያደርጋታል። በተለይም ልክ በአገራችን እየተመለከትን እንዳለነው፣ ለባህል እምነቶችና ለፖለቲካ እሴቶች “እጅ ሰጥታ” ወደ መማረክ ከሄደች፣ ጨለማውን ታበረታለች፤ አልጫውንም ይበልጥ አልጫ ታደርገዋለች።

ቅዱስ ጴጥሮስ ከመሰከረው ውጭ ያለው የትኛውም አስተምኅሮ ወይም ቅዱስ ጴጥሮስ የመሰከረውን እውነት የማይመሰክር የትኛውም ባህለ ትምህርት፣ የገሃነም ደጅ ነው። ጌታችን ኢየሱ ደግሞ እንዲህ ብሎአል፤ “በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።”። ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ለኢየሱስ ቃሎች ከታመነች፣ “የገሃነም ደጆች” በማይችሉት መንፈሳዊ ትጥቅ ተውባ፣ በልዩነት ብቻዋን መቆም ትችላለች።

ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል ምስክርነት ደፋር መኾን መቻል አለባት፤ ይህን ድፍረት ደግሞ የምታገኘው፣ እውነትን በሚገፋው፤ ነገር ግን እውነት አጥብቆ በሚያስፈልገው ዓለም ውስጥ እግዚአብሔርንና መንግሥቱን ብቻ ወክላ የቆመች እንደ ኾን ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት ከየትኛውም ባህላዊ ትምህርትና ልምምድ ይበልጣል፤ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ፣ ለቅዱስ ጴጥሮስ በገለጠው ሕያው እውነት ላይ ጸንታ በመቆም፣ በምድራችን ባሉ ባህሎችና ልምምዶቻቸው ፊት በድፍረት የወንጌልን ኃይል ልትገልጥ፣ ይህን በማድረግ ውስጥ የሚያስፈሩ የሚመስሉትን “የገሃነምን ደጆች” ኹሉ ሳትፈራ ልትቆም ይገባታል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ ለወንጌልህ ታማኞች አድርገን፤ ለእውነትህ በፍጹም መገዛትን ስጠን፤ መንግሥትህን ያለፍርሃት እንመሰክር ዘንድ ድፍረትን እንደ ሐዋርያት ስጠን፤ አሜን!



የጡመራ መድረክ አድራሻ - https://abenezerteklu.blogspot.com/2024/10/1616.html የኦሮሚኛና የአማርኛ መልእክቶችን ለማግኘት - https://www.youtube.com/@-abenezertekludiyakon8842


"ምዕመናን ገንዘባቸውን የሚሰጡት ለሃይማኖት ማስፋፊያ እንጂ ለዘረፋ አይደለም።" (ፓትርያርክ አባ ማትያስ)

ከተሐድሶ ጥያቄዎች አንዱ፣ ብልሹ አስተዳደር፣ በሙስናና በበሰበሰ ሥነ ምግባር የወደቀ ሥርዓትና ልምምድ በቃለ እግዚአብሔርና በቅድስና ሕይወት ይስተካከል የሚል ነው። ቤተክርስቲያን በሙስናና በዘረፋ ከተጨማለቀች፣ ግልጽ የኾነ ውድቀት አለ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሚቃናው በቅዱስ ወንጌል ትምህርትና በጌታ ጸጋ ብቻ ነው።

ጌታ እግዚአብሔር እውነተኛ መመለስን ለቤተክርስቲያን ይስጥ፤ ጌታ ሆይ እባክኽን ስምህን በቤተክርስቲያንና በትውልዱ ላይ ቀድስ፤ አሜን።

የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek


“ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” (ፊል. 4፥4)

የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን፣ በኹለተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት የተወለደች ቤተ ክርስቲያን ናት። ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ኹለተኛው ሐዋርያዊው ጉዞው፣ ብዙ መከራና እንግልትን ተቀብሎአል። የመጀመሪያው ሐዋርያዊው ጉዞው ብዙ መከራ የሌለበትና ቀለል ያለ ነበር፤ ኹለተኛው ግን ጠንካራና በብዙ መገፋት ውስጥ ያለፈበት ነው።

በርዕሳችን ላይ ያነሳነውን ቃል የተናገረው፣ ሐዋርያው በእስር ቤት ኾኖ ነው። እየተናገረ ያለውም፣ የመልእክቱ መቋጫ ላይ ኾኖ ነው። በክርስቶስ ወንጌል ምክንያት፣ በእስር ላይ ያለ ሰው ምን ሊናገር ይችላል? እኛ በወንጌል ጉዳይ በእስር ውስጥ ብንኾን፣ ምን ልናስብና ምን ልንመክር እንችላለን?
ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ንግግር፣ በብዙ አማኞች ዘንድ የተወደደ ነው። የመወደዱን ያህል ግን በብዙዎች ሕይወት ላይ በትክክል የሚንጸባረቅ አይደለም። እንዲህ ያለውን ጥልቅ ደስታ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እጅግ አስቸጋሪ በኾነ ኹኔታ በእስር ቤት ሳለ የተናገረው ነው። ይህን ቃል ግን ብዙዎች፣ ቅዱስ ጳውሎስ ባለፈበት መንገድ ውስጥ ኾነው ሲጠቅሱት እምብዛም አይስተዋልም።

“መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ።” (ፊል. 4፥12) የሚለው ቅዱስ ጳውሎስ፣ በእነዚህ ኹኔታዎች ውስጥ ኾኖ፣ እጅግ በጌታ ስለ መደሰት ይናገራል። በርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ እኒህን ሃያላን ተግዳሮቶች፣ ኃይልን በሚሰጠው በክርስቶስ እንደሚችል እንጂ በራሱ እንደማይችል ያምናል። እናም በክርስቶስ እንዲህ ያሉ ከፍ ያሉ ተግዳሮቶችን እኛም የማለፍ ተስፋ እንዳለን ይነግረናል።

ቅዱስ ጳውሎስ በተደጋጋሚም፣ የፊልጵስዩስ አማኞች፣ ከኹኔታዎች ይልቅ በክርስቶስ ጌታችን ላይ ተስፋ እንዲያደርጉ ያበረታታል። ይህን እያደረገ ያለው፣ እንደ አነቃቂ ተናጋሪዎች ለሌሎች አይደለም፤ በሕይወቱ ኖሮና ተፈትኖ እየኖረና እያለፈ ያለበትን እውነት በመጥቀስና፣ በራሱ ጥንካሬም ሳይኾን በክርስቶስ በመደገፍ ጭምር በመናገር። በብቸኝነት ተከብቦ፣ ወደ ሞት እየሄደ ቢኾንም፣ በክርስቶስ ላይ ያለውን ታማኝነት ፈጽሞ አልጣለም!

“ደስ ይበላችሁ” የሚለው ቃል፣ በመከራ ለተከበበና ላለ ሰው ስላቅ ይመስላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በድካማችን ብርቱ ነው! አነቃቂ ንግግሮች ወይም የራስን ቃል ማወጅ ሰውን ብርቱና ደስተኛ አያደርግም፤ ኃይልም፤ ደስታም፤ ብርታትም ከክርስቶስ ብቻ ነው! በጨለማ ቤት ለታሠረ ሐዋርያ፣ በእግር ብረት ሰውነቱ በቁስል ነፍሮ ለተተወ አገልጋይ፣ በብዙ መከራ ውስጥ እያለፈ ላለ እውነተኛ የኢየሱስ ባሪያ … ደስታና ሰላም ከክርስቶስ ዘንድ አለው! ይኸውም፦

· አማኝ ለመጪና ሂያጁ፤ ለመውጣትና መውረዱ፤ ለከፍታና ዝቅታው … ለማናቸውም ኹኔታዎች የሚበገር አይደለም፤ ልዑሉ ክርስቶስ ኹኔታዎቻችንን ኹሉ ይቈጣጠራል፤ ደስታችን ከኹኔታዎቻችን ውስጥ የሉም፤ በክርስቶስ ኢየሱስ እንጂ!

· ክርስቶስ እንጂ ሌላ ነገር የትኵረታችን ማዕከል ሊኾን አይገባውም፤ ክርስቶስ ዋና ትኵረታችን ከኾነ፣ ሌላውን በርሱ ኃይል ድል እንነሣለን። ከክርስቶስ ግን ትኵረታችንን በቀነስን ልክ፣ ኹኔታዎቻችን ገዝፈው ይታዩንና ሊያሸንፉን ይችላሉ።

· በሰማይም በምድርም ክርስቶስ በቂያችን እንደ ኾነ እናስተውል፤ ክርስቶስ ካለን ኹሉም ነገር አለን! ክርስቶስን አጥተን ኹሉም ነገር ቢኖረን ግን ያለን ነገር ኹሉ፣ የትካዜና ያለ መርካት ምንጭ እንጂ “እምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችንንና ዐሳባችንን ሊወርሰው አይችልም”!

· ደስታችንን ከራሱ ከደስታ አምላክ፤ ከሐሴት ምንጭ፤ ከእርካታ መገኛ ከክርስቶስ እንጂ ከሌላ አንሻ፤ በዓለም ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ተወዳድሮ የሚበልጥ ደስታ ፈጽሞ የለምና!
እናም እኔም የቅዱስ ጳውሎስን ቃል እደግመዋለሁ! “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ።”

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek

የጡመራ መድረክ አድራሻ - https://abenezerteklu.blogspot.com/2024/10/44.html

የኦሮሚኛና የአማርኛ መልእክቶችን ለማግኘት - https://www.youtube.com/@-abenezertekludiyakon8842

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.