በተማሪዎች ምገባ ላይ የተደረገዉ ማሻሻያ ለአንድ ተማሪ በቀን ከሚያስፈልግ ወጪ ጋር የሚመጣጠን አይደለም ተባለ‼️
በተማሪዎች ምገባ ላይ ምላሽ መሰጠቱ መልካም ቢሆንም አሁንም በቂ በጀት አለመመደቡን መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው ዩኒቨርስቲዎች ገልጸዋል። በነበረው የምግብ ሜኑ ወይም ዝርዝር ላይ ምንም አይነት የሚጨምር ነገር አይኖርም በማለት ከ22 ብር ወደ 1 መቶ ብር ከፍ ማለቱ መልካም ምላሽ ቢሆንም አሁንም ካለው የገበያ ንረት አንጻር በቂ በጀት አይደለም ሲሉ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን አቶ አለምነው መልካሙ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
በነበረው በጀት ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ለተማሪዎች ምገባ የሚሆን በጀት አልነበረንም ሲሉ የተናገሩት የተማሪዎች ዲኑ ምናልባት አዲሱ ውሳኔ በተወሰነ ሽፋን ሊሰጥ እንደሚችል ገልጸዋል። የገበያው ሁኔታ በየቀኑ እየናረ የተማሪዎች ምግብና አመጋገብ ደግሞ በተለመደ አይነት ሁኔታ እየቀጠለ ነው የነበረው አዲሱ በጀትም ከዚህ የተለየ ገበያውን በመቆጣጠር መፍትሄ ይሆናል ብለን አናምንም ሲሉ አቶ አለምነው ተናግረዋል።
ከ22 ብር ወደ 1 መቶ ብር ማደጉ ነገሩን ያረጋጋዉ እንደሆነ እንጂ በጥራትም ሆነ በምግባ አገልግሎቱ ላይ ለውጥ አያመጣም ሲሉ የወልዲያ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች አገልገሎት ዲን ዶ/ር ዮሃንስ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡
ከሶስት ወር በፊት ነሐሴ ወር ላይ ብቻ በተሰራ ዳሰሳ ለአንድ ተማሪ ወጪ በትንሹ 1መቶ 54 ብር ያስፈልግ ነበር ሲሉ ያከሉት ዲኑ አሁን ያለው የገበያ ሁኔታ ደግሞ ከሶስት ወር በፊት ከነበረው እጅግ የተለየና ጭማሪ ያሳየ በመሆኑ የተጨመረው ጭማሪ መልካም ቢሆንም ጠቃሚ ነው ማለት ግን እንደማይቻል ዶ/ር ዮሃንስ ገልጸዋል። ገበያው ውድ ከመሆኑ የተነሳ በርካታ ስራዎች እየተስተጓጎሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከትምህርት ሚኒስቴር የመጣ ይፋዊ የድጎማ ማሳወቂያ ባይኖርም ዩኒቨርሲቲዎቹ እስካሁን በሰሙት መረጃ መሰረት የተደረገው ድጎማ አሁንም ተጨማሪ ማሻሻያ የሚያስፈልገዉ እና በቀን ለአንድ ተማሪ ይወጣል ተብሎ ከሚታሰበዉ ጋር እንደማይመጣጠን አመላክተዋል፡፡
@Elshio_Academy@Elshio_Academy@Education_Fana