ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha
Toifa: ko‘rsatilmagan


ይህ ቻናል የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሲሆን ይህ ቻናል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆኑ አስተምህሮቶች በየእለቱ የሚለቀቅበት ቻናል ነው ቻናላችን ስለተቀላቀሉ በእግዚአብሔር ፅኑ ፍቅር እናመሰግናለን ።
#የፈለገ_ጥበብ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_የመረጃ_ሚዲያ_እና_ህዝብ_ግንኙነት_ክፍል
#FTM

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Toifa
ko‘rsatilmagan
Statistika
Postlar filtri




ቅዱስ ዮሐንስ በላዩ ላይ የነበረችውን ልብስ በመንገድ ለነዳይ ሰጥቶ: በፈንታው ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ ከወላጆቹ በር ላይ ለመነ:: "እባካችሁ አስጠጉኝ" አላቸው:: ወላጆቹ በጭራሽ ሊለዩት አልቻሉም:: ነገር ግን አሳዝኗቸዋልና በበራቸው አካባቢ ትንሽ ቤት ሠሩለት::

በዚያች በዓት ውስጥ እንዳስለመደ በትጋት ለ7 ዓመታት ተጋደለ:: በእነዚህ ዓመታት እንኳን ሌላው ሰው ወላጆቹም ቢሆኑ ፍርፋሪ ከመስጠት በቀር አይቀርቡትም ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ "ይሸተናል" የሚል ነበር:: በመጨረሻም መልአከ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ "ከ7 ቀናት በኋላ ታርፋለህ" አለው::

እናቱን ጠርቶ "አንድ ነገር ልለምንሽ" አላት:: "እሺ" አለችው:: "ከሞትኩ በኋላ በለበስኳት ጨርቅ እንድትገንዙኝ: በበዓቴ ውስጥም እንድትቀብሩኝ" አላትና የወርቅ ወንጌሉን አውጥቶ ሰጣት:: ያን ጊዜ አባቱም ደርሶ ነበርና ደነገጡ::

የወርቅ ወንጌሉን ለዩት:: ልጃቸውን ግን መለየት አልቻሉምና እያለቀሱ ስለ ልጃቸው የሚያውቀው ካለ እንዲነግራቸው ለመኑት:: እርሱም "ልጃችሁ ዮሐንስ እኔ ነኝ" አላቸው::

በዚያ ቅጽበት ወላጆቹ የሰሙትን ማመን አልቻሉም:: በፍጹም ዋይታ እየጮሁ አለቀሱ:: ለቅሷቸውን የሰሙ ሁሉ ተሰበሰቡ:: ለ7 ቀናት እኩሉ እያለቀሰ: እኩሉ እየተባረከ በዓቱን ከበው ሰነበቱ:: በ7ኛው ቀን መልአኩ መጥቶ በክብር ነፍሱን ተቀበለ::

እናቱ የልጇን አደራ ረስታ (እሷስ መልካም አደረግሁ ብላ ነው) ለሠርጉ ባዘጋጀችው የወርቅ ልብስ ገነዘችው:: ወዲያው ግን በጽኑ ታመመች:: አባት ግን ፈጠን ብሎ በዚያች ጨርቅ ገንዞ በበዓቱ ውስጥ ቀበረው:: ያን ጊዜ እናት ፈጥና ዳነች:: ከቅዱሱ መቃብርም ብዙ ተአምራትና ፈውስ ተደርጓል::

††† ቸሩ እግዚአብሔር ከወዳጆቹ በረከት ያሳትፈን፡፡

††† ጥር 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ (ሰማዕትና ጻድቅ)
2.ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ (ቅዳሴ ቤቱ)
4.አባ አብድዩ ጻድቅ
5.ቅዱስ ብሕኑ ሰማዕት
6.ቅዱስ አብሮኮሮስ ሐዋርያ (የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር)
7.አባ ኖሕ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት
3.ቅዱስ አሞንዮስ
4.ቅዱስ ካሌብ ንጉሠ ኢትዮጵያ
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሂት

††† "እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ: የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ: በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ:: በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሱ:: የመዳንንም ራስ ቁር: የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ:: እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው:: በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ:: በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ::" †††
(ኤፌ. ፮፥፲፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

የፈለገ ጥበብ የዲጂታል ሚዲያን ይቀላቀሉ ለሌሎች ያጋሩ🙏🙏🙏

👉ዩቲዩብ (Youtube)

👉ቲክቶክ (Tiktok)

👉ኢኒስታግራም (Instagram)

👉ፌስቡክ (Facebook)

👉ቴሌግራም (Telegram)


††† እንኳን ለቅዱሳን አክሎግ ቀሲስ: መርምሕናም: ወዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አክሎግ ሰማዕት †††

††† ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ዓበይት ሰማዕታት አንዱ ይህ ቅዱስ ነው:: "አክሎግ" ማለት "በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ (ተወዳጅ)" ማለት ነው:: እውነትም ጥዑም ዜና: ጣፋጭ ሕይወት ያለው አባት ነው:: "መልአክ ስምን ያወጣል" የሚባለው እንዲህ ላለው ነውና::

እርሱ የወላጆቹ ፍሬ ነው:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘ የነበሩ ወላጆቹ ለልጃቸው ያወረሱት ሞልቶ የተረፈ ሃብታቸውን አልነበረም:: ይልቁኑ ፍቅረ ክርስቶስን: ምሥጢረ መጻሕፍትን: ክርስቲያናዊ ስምን ነው እንጂ::

ቅዱስ አክሎግ ገና ከልጅነቱ ወደ ት/ቤት ገብቶ: ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሮ: ሐዲስ ኪዳንን በሙሉ: መኀልየ ነቢያትን: መዝሙረ ዳዊትን አክሎ በቃሉ አጠና:: ቅዱስ ቃሉ ለእርሱ እውቀት አልነበረም: ሕይወት እንጂ:: ሳይሰለች ያነበው: በሕይወቱም ይተረጉመው ነበርና::

በዚህ ንጹሕ ሕይወቱም ፈጣሪውን አስደስቶ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል:: ከዚያም ተጋድሎውን ቀጥሎ በትሕርምት ኑሯል:: ቀሲስ ሆኖ ሲሾምም ቅዱሳን መላእክት "ይገባዋል!" ሲሉ 3 ጊዜ ጮሁ:: በጽድቅ ጸንቶም ዘመናት አለፉ::

በዘመነ ሰማዕታትም ነጭ በነጭ ለብሶ ብዙ መከራን ተቀበለ:: በዚህች ቀንም ከብዙ ተከታዮቹ ጋር ደሙ ፈሷል:: ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን "ጻድቅ: ንጹሕ: ድንግል: ባሕታዊ: ቀሲስ ወሰማዕት" ብላ ታከብረዋለች:: ጌታም "ስምህን ያከበረውን: የተሰየመውን እምርልሃለሁ" ብሎታል::

††† ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት †††

††† ሰማዕቱ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ዐበይት ቅዱሳን አንዱ ነው:: በየአብያተ ክርስቲያናቱ ከሚሳሉ ቅዱሳንም አንዱ ነው:: ሃገሩ አቶር (በፋርስ አካባቢ) ሲሆን አባቱ ሰናክሬም የሚባል ንጉሠ ነገሥት ነው::

እናቱ ምንም ክርስቲያን ብትሆንም ስለ ፈራች ሁለቱን ልጆቿን (መርምሕናምና ሣራን) ክርስትናን አላስተማረቻቸውም:: ሁለቱም ወጣት በሆኑ ጊዜም ከንጉሥ አባታቸው ጋር ይወጡ ይገቡ ነበርና እናታቸው በሐዘን ጸለየች:: ወዲያውም ወጣቷ ሣራ በለምጽ ተመታች::

የሚፈውሳት ጠፋ:: መርምሕናም ግን ጐበዝ ወጣት ነውና 40 የጦር አለቆችን ይመራ ነበር:: በዚያው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ቅዱስ መርምሕናም 40 ተከታዮቹን ይዞ ለአደን ወደ ዱር ሲወጣ ከአባ ማቴዎስ ገዳማዊ ጋር ተገናኘ::

ጻድቁ ለብዙ ዓመታት በበርሃ የኖሩ አባት ናቸው:: አካላቸው በጸጉር ስለ ተሸፈነ ደንግጦ ሲሸሽ "ልጄ አትፍራ! እኔም እንዳንተ የክርስቶስ ፍጡር የሆንኩ ሰው ነኝ" አሉት::

እርሱ ግን "ደግሞ ክርስቶስ ማነው?" ሲል ጠየቃቸው:: አባ ማቴዎስም ምሥጢረ ክርስትናን ከመሠረቱ አስተምረው የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ነገሩት::

ቅዱስ መርምሕናም ግን "ክርስቶስ አምላክ እንደ ሆነ አምን ዘንድ እህቴን አድንልኝ" አላቸው:: "አምጣት" ብለውት አመጣት:: ጻድቁ ጸሎት አድርሰው መሬትን ቢረግጧት ውኃን አፈለቀች:: "በእምነት: በስመ ሥላሴ ተጠመቁ" አሏቸው::

ቅዱሱ: እህቱ ሣራና 40 የጦር አለቆች ተጠምቀው ሲወጡ ሣራ ከለምጿ ነጻች:: ፈጽሞም ደስ አላቸው:: ወደ ቤተ መንግስት ተመልሰውም ቅዱስ መርምሕናም ከእናቱ: ከእህቱና ከ40 ተከታዮቹ ጋር ክርስቶስን ሊያመልኩ ጀመሩ::

ንጉሡ ሰናክሬም ግን ነገሩን ሲሰማ ተቆጣ:: እነርሱም ወደ ተራራ ሸሹ:: ንጉሡ "ልጆቼ! መንግስቴን ውረሱ" ብሎ ቢልክባቸውም እንቢ አሉ:: ስለ ተበሳጨም ቅዱስ መርምሕናምን: ቅድስት ሣራንና 40ውን ቅዱሳን በሰይፍ አስመታቸው::

ሥጋቸውን በእሳት ሊያቃጥሉ ሲሉ ግን መነዋወጥ ሆኖ ብዙ አረማውያን ሞቱ:: ንጉሡም አብዶ አውሬ (እሪያ) ሆነ:: ያን ጊዜ አባ ማቴዎስ ከበርሃ ወጥተው ንጉሡን ሰናክሬምን ፈወሱት::

እርሱም አምኖ የልጆቹና የ40ውን ሥጋ በክብር አኖረ:: በሃገሩ አቶርም የእመ ብርሃን ማርያምን ቤተ መቅደስ አነጸ:: በክርስትና ኑሮም ዐረፈ:: እርሱ ከተቀበረ በኋላ ግን የከለዳውያን ንጉሥ መጥቶ አቶርን ወረራት::

ንግሥቲቱን (የቅዱሳኑን እናት) ከሕፃኑ ልጇ ጋርም ገደለ:: በኋላም "ለጣዖት ስገዱ" ማለቱን የሰሙት የቅዱስ መርምሕናም ወታደሮች ደርሰው በምስክርነት ተሰየፉ:: ቁጥራቸውም 170,000 ሆነ::

††† ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ) †††

††† ቅዱሱ "ወንጌሉ ዘወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ከሌሎች "ዮሐንስ" ከሚባሉ ቅዱሳን ለመለየት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን እድሜ ልኩን የሚያነበው: ከእጁ የማይለየውና አቅፎት የሚተኛ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል ስለ ነበረው ነው::

የቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩ በሆነ መንገድ ከመርዓዊ (ሙሽራው) ገብረ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ሙሴ ሮማዊ ጋር ተመሳሳይነት አለው::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
በሮም ግዛት ሥር የሚኖሩ አጥራብዮስና ብዱራ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ:: እግዚአብሔር በቀደሰው ትዳር የሚኖሩና ነዳያንን የሚዘከሩ ነበሩና ይህንን ቅዱስ ወለዱ:: ስሙን ዮሐንስ ብለው: እንደሚገባም አሳድገው: ምሥጢረ መንግስተ ሰማያትን እንዲረዳ ለመምህር ሰጡት:: ቅዱስ ዮሐንስ ከመምህሩ ዘንድ ቁጭ ብሎ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን ተማረ::

ለወላጆቹ ቅንና ታዛዥ ነበርና አባቱ "ልጄ! የምትፈልገውን ጠይቀኝ:: ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለው:: ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድሮ እኛን የሚያምረን ሁሉ አላሰኘውም:: አባቱን "ቅዱስ ወንጌልን ግዛልኝ: በወርቅም አስለብጠው" አለው:: አባትም የተባለውን ፈጸመ::

ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እስካረፈባት ቀን ድረስ ቅዱስ ዮሐንስና የወርቅ ወንጌሉ ተለያይተው አያውቁም:: ሁሌም ያለመታከት ያነበዋል:: ሲቀመጥም ሲነሳም: ሲሔድም ሲተኛም አብሮት ነበር::

ቅዱስ ዮሐንስ ወጣት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይድሩት ዘንድ ተዘጋጁ:: ልብሰ መርዐም (የሙሽራ ልብስ) አዘጋጁ:: በዚያው ሰሞን ግን አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤታቸው መጥቶ ያድራል:: በዚያች ሌሊት መነኮሱ በጨዋታ መካከል ስለ ቅዱሳን መነኮሳት ተጋድሎና ክብር ነገረው:: የሰማው ነገር ልቡናውን የማረከው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደ ፈጣሪው ይለምን ነበር::

አንድ ቀን ግን ያ መነኮስ በድጋሚ መጥቶ አደረ:: ቅዱስ ዮሐንስ መነኮሱን ወደ ገዳም እንዲወስደው ቢጠይቀው "አይሆንም: አባትህ ያዝንብኛል" አለው:: ቅዱሱ ግን "በእግዚአብሔር ስም አማጽኜሃለሁ" ስላለው ሁለቱም በሌሊት ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ::

አበ ምኔቱ "ልጄ! የበርሃውን መከራ አትችለውም: ይቅርብህ" ቢለውም "አባቴ! አይድከሙ:: ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር አይለየኝም'' ስላላቸው እንደሚገባ ፈትነው አመንኩሰውታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከመነኮሰ በኋላ በጾም: በጸሎት: በስግደትና በትሕርምት ያሳየው ተጋድሎ በርካቶችን አስደነቀ::

ለሥጋው ቦታ አልሰጣትምና በወጣትነቱ አካሉ ረገፈ:: ቆዳውና አካሉም ተገናኘ:: ሥጋውን አድርቆ ነፍሱን አለመለማት:: በእንዲሕ ያለ ሕይወት ለ7 ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በራዕይ "ወደ ወላጆችህ ተመለስ" እያለ 3 ጊዜ አናገረው::
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ አበ ምኔቱ ሔዶ ቢጠይቀው "ራዕዩ ከእግዚአብሔር ነው" ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አሰናበተው::




††† እንኳን ለጻድቅ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን †††

††† በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን (በተለይ ከ13ኛው እስከ 15ኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለው) የብርሃን ዘመን ይባላል:: ምክንያቱም ዘመኑ
*ክርስትና ያበበበት::
*መጻሕፍት የተደረሱበት::
*ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት::
*ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው::

ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ:-
¤አቡነ ተክለ ሃይማኖት::
¤አቡነ ኤዎስጣቴዎስ::
¤አባ ሰላማ ካልዕ::
¤አቡነ ያዕቆብ::
¤ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ::
¤አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ::
¤አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው::

በተጨማሪም:-
¤12ቱ ንቡራነ ዕድ::
¤7ቱ ከዋክብት::
¤47ቱ ከዋክብት::
¤5ቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር:: ከእነዚህ መካከልም የ7ቱ እና የ47ቱ ከዋክብት አስተማሪ: የአበው 3ቱ ሳሙኤሎች (ዘዋልድባ: ዘጣሬጣና ዘቆየጻ): የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::

ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው: አስተምረው: አመንኩሰው: መርቀው ሰደው: ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ::

ከእነዚህ ቅዱሳን የጻድቁ ፍሬዎች አንዱ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ናቸው:: ጻድቁ አንዳንዴ "አፍቀረነ እግዚእ" እየተባሉም ይጠራሉ:: ትርጉሙም "ጌታ ወደደን" እንደ ማለት ነው::

ያፍቅረነ እግዚእ የነበሩት በ14ኛው መቶ ክ/ዘ ሲሆን ቁጥራቸው ከ7ቱ ከዋክብት ነው:: ጻድቁ ከልጅነት ጀምሮ በሥርዓቱ ከማደጋቸው ባሻገር እጅግ የተማሩ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል::

ለምናኔ ከወጡ በሁዋላ ከኖሩባቸው ቦታዎችም 3ቱ ተጠቃሽ ናቸው:: የመጀመሪያውና ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ደግሞ ደብረ በንኮል ነው:: ጻድቁ በዚህ ገዳም ከታላቁ ቅዱስ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሥርዓተ ገዳምን : ትኅርምተ አበውን : ተጋድሎተ ቅዱሳንን አጥንተው ለመዓርገ ምንኩስና በቅተዋል::

በገዳሙም ለተወሰነ ጊዜ አገልግለው ወደ ጣና አካባቢ ከአቡነ ያሳይና ከአባ ሳሙኤል ዘዋሊ ጋር መጥተዋል:: የመምጣታቸው ምክንያትም ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስና ገዳማትን ለመመሥረት ነው::

ሶስቱ ቅዱሳን ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በሁዋላ አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ ደግሞ ማንዳባን አቀኑ:: ያፍቅረነ እግዚእም ጌታ ባዘዛቸው መሠረት ጣና ውስጥ ገዳም አቅንተው ኑረዋል:: ይህ ገዳማቸው ዛሬም ድረስ በስማቸው ይጠራል::

ጻድቁ አፍቀረነ እግዚእ 3ኛው የሚታወቁበት ገዳም ማኅበረ ዴጌ (ጻድቃነ ዴጌ) ሲሆን ገዳሙ በአክሱም ዙሪያ ይገኛል:: እርሳቸው 3ሺ ቅዱሳን የተሠወሩበትን ገዳም በማገልገላቸውም ዛሬም ድረስ በአካባቢው የታወቁ ሆነዋል::

በተረፈም አክሱም አካባቢ ሌሎች ገዳማትን እንዳቀኑም ይነገርላቸዋል:: ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ለብዙ ዘመናት በተጋድሎ : በስብከተ ወንጌልና ገዳማትን በማስፋፋት ከኖሩ በሁዋላ በዚህች ቀን ዐርፈው ለክብሩ : ለርስቱ በቅተዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ አማላጅነት ይቅር ብሎ በረከታቸውን ያሳድርብን::

††† ጥር 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ (አፍቀረነ እግዚእ ዘጉጉቤ - ጣና ውስጥ - ከሰባቱ ከዋክብት አንዱ)
2.አባ ባሱራ
3.ቅድስት ኔራ
4.ቅድስት በርስጢና
5.አባ ዝሑራ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ታቦታቸው ጎንደር ከተማ ቀበሌ 09 አካባቢ ይገኛል)
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† ቅዱሳንን ታስቡ ዘንድ ቸል አትበሉ::

††† "እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. 36:28-31)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

የፈለገ ጥበብ የዲጂታል ሚዲያን ይቀላቀሉ ለሌሎች ያጋሩ🙏🙏🙏

👉ዩቲዩብ (Youtube)

👉ቲክቶክ (Tiktok)

👉ኢኒስታግራም (Instagram)

👉ፌስቡክ (Facebook)

👉ቴሌግራም (Telegram)


የፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል የፈለገ ጥበብ ፕሮዳክሽን የሰርግ፣ልደት፣ክርስትና፣መዝሙር እና ልዩ ልዩ የፎቶ እና ቪዲዬ አቅርቦት ፣ የሞንታርቦ አቅርቦት ፣ የዲኮር ስራ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሰሩ ያውቃሉ?
እንግዲያውስ ለኦርቶዶክሳዊ መርሀግብር ልዩ ቅናሽ ስላዘጋጀን በውስጥ መስመር ያናግሩን ።




+በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ: ቅድስት ማርያም ከጌታ
ሥር ተንበርክካ: ናርዶስ የሚሉትን የ300 ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ
አፈሰሰች:: መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ"
እንዲል ምስጥ የሚያደርግ ሽታ ቤቱን ሞላው::

+በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል:: ቅድስት
ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ"
ብሎ አመስግኗታል:: ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ
ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል::

+ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ
እናድርግ" ብሎናል:: (ቅዳሴ ማርያም) ቅድስት ማርያም
በጌታችን ክርስቶስ በኅማሙ ጊዜ: ሲቀብሩት ነበረች::
ትንሳኤውንም ዐይታለች::

+ከጌታ እርገት በሁዋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል
አገልግሎት ተግታለች:: ቅድስት እናታችን ማርያም እንተ ዕፍረት
ዛሬ በዓሏ ከእህቷ ቅድስት ማርታ ጋር ይከበራል::

=>ጥር 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጊዮርጊስ መክብበ ሰማዕታት (ዝርወተ ዓጽሙ)
2.ቅዱሳት ደናግል ማርያ እና ማርታ (ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት)
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንፅቢን (ከ318ቱ)
4.ቅዱስ ባኮስ ኢትዮዽያዊ (አቤላክ / አቤሜሌክ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ
3.አባ አኖሬዎስ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ
5.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ

+"+ የጌታም መልአክ ፊልጶስን። ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው።
ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤
ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።
መንፈስም ፊልጶስን። ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው።
ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና። በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው።
እርሱም። የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።
ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?
ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ። እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው።
ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ጌታ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት።
በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው።
ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ።
ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም።
ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና። +"+ (ሐዋ. ፰:፳፮)

>


=>+"+ እንኩዋን ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ: ቅዱስ
ባኮስ: ቅዱስ ያዕቆብና ደናግል ማርያ ወማርታ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+" ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ "+

=>መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው: አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ7 ዓመታት ስቃይ በሁዋላ ተሰይፏል:: ይሕስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ:-

+ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::

+ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት-ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::

+ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና 70 ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ::

+ከዚያም ለተከታታይ 7 ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን
ተቀበለ:: 3 ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው: ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል:: "ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ:
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ::

+ከ7 ዓመታት መከራ በሁዋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ
ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: 7 አክሊላትም
ወርደውለታል::

+" ዝርወተ ዓጽሙ "+

=>ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ 'ዝርወተ አጽሙ' ትባላለች:: በቁሙ
'አጥንቱ የተበተነበት' እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ጊዮርጊስን
ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ
አሸነፋቸው:: 70 ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ
ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ
ለሰማዕትነት አበቃ::

+በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን
እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው:
በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት:: ያለ ርሕራሔም አካሉን
አሳረሩት:: ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት::

+በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ)
ወጥተውም በነፋስ በተኑት::
"ሐረድዎ ወገመድዎ: ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል::
(ምቅናይ)

+እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም
ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ:: ስለዚህም ይሕቺ ዕለት
ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው::

+ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት
ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ:
አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው:: 70ው ነገሥታት ግን አፈሩ::

+" ቅዱስ ባኮስ ጃንደረባው "+

=>'ጃንደረባ' የሚለው ቃል በግዕዙ 'ሕጽው' ተብሏል:: ይህ ስም
በቤተ ክርስቲያን የተለመደ እንጂ እንግዳ አይደለም::
መድኃኒታችን እንዳለው በተፈጥሮ የሆኑ: ሰዎች እንዲያ
ያደረጉዋቸውና ራሳቸውን ስለ ጽድቅ ጃንደረባ ያደረጉ ብዙዎች
ናቸውና::

+ኢትዮዽያዊው ጃንደረባ ቅዱስ ባኮስም (አንዳንዴ አቤላክ /
አቤሜሌክም ይባላል):-
*በ1ኛው መቶ ክ/ዘመን በሃገራችን ኢትዮዽያ ተወልዶ ያደገ
*ነገሥታቱንና ሃገሩን በሙያው ያገለገለ
*በተለይ ከ34 እስከ 46 ዓ/ም ለነገሠችው ንግሥት ሕንደኬ
ገርስሞት በገንዘብ ሚንትርነት ያገለገለ
*በገንዘቧ ላይ ሁሉ አዛዥ (ታማኝ) የነበረ
*ጃንደረባ በመሆኑ ለንግሥቲቱና ቤተሰቧ ቅርብ የነበረ
*መጻሕፍትን የሚያነብና የሚመረምር
*ዘወትር ወደ ኢየሩሳሌም እየሔደ ከቅዱሳት መካናት የሚሳለም
በጐ ሰው ነበር::

+በግብረ ሐዋርያት ምዕ. 8:26 ላይ እንደ ተጠቀሰው ቅዱሱ
ከኢየሩሳሌም ለፋሲካና ለእሸት በዓል ነበር የሔደው:: ሲመለስ
መንፈስ ቅዱስ ከፊልዾስ ጋር በጋዛ አገናኝቶታል:: በዚያም
ምሥጢረ ክርስትናን ተምሮ: በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት
አምኖ ተጠምቁዋል::

+ክርስትናን ለኢትዮዽያ በ34 ዓ/ም አምጥቷል:: "ጃንደረባው
ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ" ሲል ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንደ
ተናገረው ወደ ሃገራችን ተመልሶ: ስለ ክርስቶስ ሰብኮ በርካቶችን
አሳምኗል::

+ቀጥሎም ሃብቱን ንቆ (መንኖ): ከኢትዮዽያ እስከ ሕንድ
ወንጌልን ሰብኮ በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ዐርፏል::
(ተሰውሯል የሚሉም አሉ)

>

+" ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን "+

=>ይህ ቅዱስ ሰው:--
*እጅግ የተመሠከረለት ሊቅ
*በፍጹም ትሕርምት የኖረ ገዳማዊ
*በርካቶችን ወደ ክርስትና ያመጣ ሐዋርያዊ
*ለአእላፍ ምዕመናን እረኛ የሆነ የንጽቢን (ሶርያ) ዻዻስ
*ለጀሮ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን የሠራ ገባሬ መንክራት
*ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንትን ያፈራ
ታላቅ መምሕር
*ለክርስቶስና ለእመቤታችን ታጥቆ የተገዛ የፍቅር ሰው
*እጣቶቹ እንደ ፋና የሚያበሩለት ማኅቶት
*ራሱን ዝቅ አድርጐ በቆሸሸ ልብስ የሚኖር የትህትና ሰው ነው::

=>በ325 (318) ዓ/ም: በኒቅያ 318ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡና
አርዮስን ሲያወግዙ እርሱ አንዱ ነበር:: በሥፍራውም ሙት
አስነስቶ ሕዝቡን አስደምሟል:: በዚያም የቤተ ክርስቲያንን
ሥርዓት ሠርቶ ወደ ሃገሩ ተመልሶ በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን
ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::

+"+ ደናግል ማርያ ወማርታ +"+

=>በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ 'እንተ ዕፍረት-ባለ ሽቱ'
ተብለው የሚጠሩ 2 እናቶች ነበሩ:: 2ቱም ስማቸው ማርያም
ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን 'ማርያም ኃጥዕት-
ከኃጢአት የተመለሰች': 2ኛዋን ደግሞ 'ማርያም እኅተ
አልዓዛር-በቢታንያ የነበረችው ብለው አበው ይጠሯቸዋል::

+በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት
የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል 12:1 ላይ ያለችው
የአልዓዛር እህት (ድንግሊቱ) ናት:: ዛሬም የምናስባት ይህቺውን
እናታችን ነው::

+ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም
መጥቶ በሚያስተመርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች
ድንግል ወጣት ናት:: ወላጆች ባልነበረበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ
አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል::

+በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው::
አልዓዛርን ከ72ቱ አርድእት: ማርያምና ማርታን ደግሞ ከ36ቱ
ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል:: ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ
ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር::

+ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ:: በ4ኛው
ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት ሰግዳ
"እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ-አንተ በዚህ
በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች:: (ዮሐ. 11)

+ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ::
ወዲያውም በስልጣነ ቃሉ አዞ አልዓዛርን አስነሳው:: ከፋሲካ
(ጌታ ከመሰቀሉ 6 ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ::
እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው:: (ዮሐ. 12:1)


ይመልከቱ ለሌሎች ያጋሩ
https://youtu.be/ffB01WYpA0Q?si=I0jCesFfPf3GmEGM






በተመሳሳይ ቅዱሳኑ ሲወስዱት 2ቱንም ቅዱሳን ታላቁ መቃርስ በበዓታቸው ቀብሯቸዋል:: ቦታውም "ደብረ ብርስም (በርሞስ)" ተብሏል:: ትርጉሙም "የሮማውያኑ ቅዱሳን ደብር" እንደ ማለት ነው::

††† አምላከ ቅዱሳን በእነርሱ ላይ የበዛች ፍቅሩን ለእኛም ያድለን:: ፍሬ ትሩፋት: ፍሬ ክብር እንድናፈራም ይርዳን:: ክብራቸውንም አያጉድልብን::

††† ጥር 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን እና ክቡራን የሚሆኑ አባቶቻችን "መክሲሞስ እና ዱማቴዎስ"

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ (ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዘቆዽሮስ
3.አባ ገሪማ
4.አባ ዸላሞን ፈላሲ
5.አባ ለትፁን የዋሕ
6.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)

††† "ፍቅር ያስታግሳል:: ፍቅር ያስተዛዝናል:: ፍቅር አያቀናናም::ፍቅር አያስመካም:: ፍቅር አያስታብይም:: ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም:: አያበሳጭም:: ክፉ ነገርን አያሳስብም:: ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም:: ሁሉን ይታገሣል:: ሁሉን ያምናል:: ሁሉን ተስፋ ያደርጋል:: በሁሉ ይጸናል::" †††
(1ቆሮ. 13:4)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

የፈለገ ጥበብ የዲጂታል ሚዲያን ይቀላቀሉ ለሌሎች ያጋሩ🙏🙏🙏

👉ዩቲዩብ (Youtube)

👉ቲክቶክ (Tiktok)

👉ኢኒስታግራም (Instagram)

👉ፌስቡክ (Facebook)

👉ቴሌግራም (Telegram)


††† እንኳን ለቅዱሳን ወክቡራን ጻድቃን መክሲሞስ ወዱማቴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አበዊነ መክሲሞስ ወዱማቴዎስ †††

††† እኒህ ቅዱሳን የሥጋ ወንድማማቾች ሲሆኑ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እጅግ ተወዳጅ አባቶች ናቸው:: ስንጠራቸውም "አበዊነ ቅዱሳን : ወክቡራን : ሮማውያን : መስተጋድላን : ወከዋክብት ብሩሃን" ብለን ነው::

ይኸውም "እንደ ንጋት ኮከብ የምታበሩ : ተጋዳይ : ቅዱሳንና ክቡራን የሆናችሁ ሮማውያን አባቶቻችን" ማለት ነው:: ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ሁና አባታቸው ንጉሥ ለውንድዮስ ይባላል::

ይህ ንጉሥ ሮምን በምታክል ታላቅ ሃገር በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነግሦ ሳለ መልካም ሰው ሆኖ ተገኝቷል:: ከመልካም ሚስቱ (ንግሥቲቱ) ከወለዳቸው መካከልም 2ቱ ከዋክብት ይጠቀሳሉ:: 2ቱ ቅዱሳን በአጭር የጊዜ ልዩነት የተወለዱ በመሆናቸው እንደ መንትያ ይቆጠራሉ::

ንጉሡ ለውንድዮስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ላገኛቸው ልጆቹ ስም ሲያወጣ ታላቁን መክሲሞስ : ታናሹን ደግሞ ዱማቴዎስ ብሎታል:: ቅዱሳኑ በንጉሥ አባታቸው መልካም ፈቃድ ክርስትናን ተምረዋል::

ምንም እንኩዋ የንጉሥ ልጆች እና ልዑላን ቢሆኑም ተቀማጥለው አላደጉም:: ምቾት ብዙዎችን አጥፍቷልና:: ይህንን የተረዳ አባታቸው ሞገስን በፈጣሪያቸው ዘንድ እንዲያገኙ እንዲህ በበጐ ጐዳና አሳደጋቸው::

ቅዱሳን መክሲሞስና ዱማቴዎስ ካደጉና ለአካለ መጠን ከደረሱ በሁዋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ ይተጉ ነበር:: በተለይ ዜና ቅዱሳንን ከማንበብ አይጠግቡም ነበር:: እግዚአብሔርንም በፍቅር እያመለኩ በጾምና በጸሎት ይገዙለት ነበር::

ቅዱሳኑንም ለየት የሚያደርጋቸው አንዱ ይሔው ነው:: ወርቅና ብር በፊታቸው ፈሶ: በእግራቸው እየረገጡት: አገሩና ምድሩ እየሰገደላቸው: የላመ የጣመ ምግብ እየቀረበላቸው: የሞቀ የደመቀ መኝታ እየተነጠፈላቸው . . . ሁሉንም ስለ ፍቅረ ክርስቶስ መናቃቸው ይደነቃል::

እነርሱ በክርስቶስ ፍቅር ሆነው የዚህን ዓለም ጣዕም ንቀዋልና የአባታቸውን ቤተ መንግስት ሊተዉ አሰቡ:: አሳባቸው ደግሞ በመመካከር ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት: "እንደ አንድ ልብ መካሪ: እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ" እንዲሉ አበው በጌታ መሪነት ነው::

ወደ በርሃ ሔደው ለፈጣሪ ለመገዛት ሲያስቡ መውጫ መንገዳቸውን ይሹ ነበርና አንድ ጐዳና ተገለጠላቸው:: ከዚያም ለንጉሥ አባታቸው ሔደው "አባ! እኛ ወደ ኒቅያ (ታናሽ እስያ) ሔደን መባረክ እንፈልጋለን" ሲሉ ጠየቁት::

ወቅቱ ቦታዋ ስለ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ሞገስን ያገኘችበት ጊዜ ነበር:: አባታቸውም መንፈሳዊ ሰው ነበርና ደስ እያለው ፈቀደላቸው:: ብዙ ወርቅን ሰጥቶ: ሸልሞ ከብዙ ሠራዊት ጋር ሸኛቸው::

ቅዱሳኑ መክሲሞስና ዱማቴዎስም ለጥቂት ጊዜ በኒቅያ ሲጸልዩና ሲባረኩ ሰነበቱ:: ቀጥለውም የአባታቸውን ሰራዊት ሰብስበው "እኛ ሱባኤ ልንይዝ ስለ ሆነ እንመጣለን" የሚል ደብዳቤን ሰጥተው ወደ ሮም ሸኟቸው::

ወታደሮችን ከሸኙ በሁዋላ ቅዱሳኑ በአካባቢው ወደ ሚገኝ አንድ ገዳም ሒደው ለአንድ ደግ መናኝ ምሥጢራቸውን ገለጹለት:: ልክ የንጉሡ ለውንድዮስ ልጆች መሆናቸውን ሲያውቅ "አመንኩሰን" ያሉትን እንቢ አላቸው::

"ለምን?" ሲሉት "ደጉን አባታችሁን ማሳዘን አልፈልግም:: ግን ፈቃዳችሁ እንዲፈጸምላችሁ ወደ ሶርያ ዝለቁ:: በዚያ አባ አጋብዮስ የሚባል ጻድቅ ገዳማዊ ሰው ታገኛላችሁ" ብሎ ወደ ሶርያ አሰናበታቸው::

በምድረ ሮም: በተለይም በቤተ መንግስቱ አካባቢ የ2ቱ ልዑላን መጥፋት (መሰወር) ሲሰማ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ:: ንጉሡ አባታቸው በወታደሮቹ ዓለምን ቢያካልልም ሊያገኛቸው አልቻለም:: እርሱ ፈጽሞ ሲያዝን እናታቸው ፈጽማ መጽናናትን እንቢ አለች::

መክሲሞስና ዱማቴዎስ ግን ምድረ ሶርያ ገብተው የጻድቁ አባ አጋብዮስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ:: በእርሱም ዘንድ ለምናኔ የሚያስፈልጉ በጐ ምግባራትንና ትሩፋትን ከተማሩ በሁዋላ 2ቱንም አመነኮሳቸው:: በዚያ ቦታም እየታዘዙ: ፈጣሪን እያመለኩ: በጾም: በጸሎትና በትህትና ኖሩ::

አንድ ቀን ግን አባ አጋብዮስ ጠርቶ "ልጆቼ! ተባረኩ! በእናንተ ምክንያት ደስ ብሎኛልና:: በዚህች ሌሊት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርዮስ በራዕይ ተገልጦ : 'ልጆች እንዲሆኑኝ ስጠኝ' ብሎኛልና እኔ ሳርፍ ወደ ግብጽ ገዳመ አስቄጥስ እንድትሔዱ" አላቸው::

አባ አጋብዮስ ካረፈ በሁዋላ ግን እንደ ትዕዛዙ አልሔዱም:: ውዳሴ ከንቱን ይፈሩ ነበርና:: በዚያው በምድረ ሶርያ ግን በጥቂት ጊዜ (ገና በወጣትነት) ከብቃት መዓርግ ስለ ደረሱ በርካታ ተአምራትን ሠሩ:: በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ ሆኑ::

ስም አጠራራቸውም ሶርያን መላት:: በዘመኑ በአካባቢው አንድ ግዙፍ ዘንዶ ተነስቶ ሰውንም እንስሶችንም ፈጃቸው:: ሕዝቡም ሒደው በቅዱሳኑ ፊት አለቀሱ:: ያን ጊዜ ቅዱስ መክሲሞስ (ትልቁ) ክርታስ አውጥቶ "አንተ ዘንዶ ይህ ክርታስ ወደ አንተ ሲደርስ ከማደሪያህ ውጣ: ሙት: ወፎችም ይብሉህ" ሲል ጻፈበት::

"ሒዳችሁ በበሩ ጣሉት" አላቸው:: አንድ ደፋር ሰው ተነስቶ ሰዎች ሁሉ እያዩት ወስዶ በዘንዶው መውጫ ላይ ጣለው:: በቅጽበትም ዘንዶው ወጥቶ ሞተ:: አሞሮችም ተሰብስበው በሉት:: ከዚህ ድንቅ ተአምር የተነሳ ሕዝቡ የቅዱሳኑን አምላክ አከበረ::

ከዚህ በተረፈም በቅዱሳኑ ስም ታላላቅ ተአምራት ተደረጉ:: ርኩሳት መናፍስት ሁሉ ስማቸውን እየሰሙ ይሸሹ ነበርና:: ድውያን እነሱ በሌሉበት ስማቸው ሲጠራላቸው ይፈወሱ ነበር:: የአካባቢው ሰው ስማቸውን እየጠራ: በእነርሱም እየተማጸነ ከመከራው ሁሉ ይድን ነበርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሞገስ ሆኑ::

መርከበኞች ደግሞ ከማዕበል ለመዳን የቅዱሳኑን ስም በጀልባዎቻቸው ላይ ይጽፉ ነበር:: አንድ ቀን ግን የንጉሡ ለውንድዮስ ባለሟል ይህንን ጽሑፍ ተመልክቶ ስለ ጠረጠረ መርከበኛውን በንጉሡ ፊት አቀረበው::

ንጉሡም መርከበኛውን "የጻፍከው የማንን ስም ነው?" ቢለው "በሶርያ የሚገኙ 2 ወንድማማች ቅዱሳን ስም ነው" አለው:: ልጆቹ እንደ ሆኑ ገምቶ በመርከበኛው መሪነት ንግሥቲቱንና ሴት ልጁን ላካቸው:: እነርሱ በሐዘን ተሰብረው ነበርና::

ወደ ሶርያ ወርደው ባገኟቸው ጊዜም ከናፍቆትና ደስታ የተነሳ ታላቅ ጩኸትን እየጮሁ አለቀሱ:: "እንሒድ ወደ ሮም" ሲሏቸው ግን ቅዱሳኑ "የለም! እኛ የክርስቶስ ነን" ብለው እንቢ ስላሏቸው እያዘኑ ተመለሱ:: ንጉሡ ግን ይህንን ሲሰማ ደስ አለው:: "እነርሱ የዚህን ዓለም ኃላፊነት ተረድተዋል" ሲልም አወደሳቸው::

በሁዋላ ግን "የሮሜ ሊቀ ዻዻሳት መሆን አለባችሁ" የሚል ነገር ሲሰማ ቅዱሳን መክሲሞስና ዱማቴዎስ ከሶርያ ወጥተው ወደ ግብጽ ወረዱ:: ከታላቁ ቅዱስ መቃርስ ዘንድ ደርሰውም ልጆቹ እንዲሆኑ ለመኑት::

"ልጆቼ! በርሃ አይከብዳችሁም?" ቢላቸው "ግዴለም!" አሉት:: በዚያም ከተራራው ሥር በዓት ሠርቶላቸው ለ3 ዓመታት በአርምሞ ቆዩ:: አንድ ቀንም ቅዱሳኑ እየጸለዩ ከአፋቸው የወጣ የብርሃን ምሰሶ ከመንበረ ጸባኦት ሲደርስ አይቶ ታላቁ መቃርስ አደነቀ::

በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢም ጥር 14 ቀን ታላቁ ቅዱስ መክሲሞስ ዐረፈ:: በዕለቱም የሰማይ ቅዱሳን ሁሉ ወርደው እየዘመሩ ወሰዱት:: ከ3 ቀን በሁዋላ ደግሞ ቅዱስ ዱማቴዎስ ዐረፈ::




+ወደ ቤቱ ተመልሶም የወላጆቹን ላም "እውነትን ተናገር" ብሎ ገስጾታል:: ላሙም ሰይጣን እንዳደረበት በሰው ልሳን ተናግሮ: የቅዱሱን ወላጆች ወግቶ ገድሏቸዋል:: ቅዱስ ፊላታዎስ ግን ላሙን አስገድሎ: ወላጆቹን ከሞት አስነስቶ ከአካባ

ቢው ሰው ጋር በስመ ሥላሴ አስጠምቁዋቸዋል::

+በድንግልና ኑሮም ዘመነ ሰማዕታት ሲጀምር በርጉም ዲዮቅልጥያኖስ እጅ ብዙ ተሰቃይቷል:: በጸሎቱም ጣዖታቱን (እነ አዽሎንን) ከነ አገልጋዮቻቸው ወደ ጥልቁ አስጥሟቸዋል:: እርሱም በዚህች ቀን በሰይፍ ተከልሎ ለክብር በቅቷል:: ለእኛ ለኃጥአን የሚሆን ቃል ኪዳንንም ከጌታው ተቀብሏል::

=>የቅዱሳን አባቶቻችን አማናዊት ርስት ድንግል ማርያም አትለየን::

=>ጥር 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ፊላታዎስ ሰማዕት
2.አባ ዸላድዮስ ገዳማዊ
3.ማር ዳንኤል ሶርያዊ
4.አባ ዮሐንስ መሐሪ (ሊቀ ዻዻሳት)
5.11,004 ሰማዕታት (የቅ/ቂርቆስ ማሕበር)
6.11,503 (የቅ/ፊላታዎስ ማሕበር)
7.አባ ጽሕማ (ከተስዓቱ ቅዱሳን አንዱ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.በዓለ ኪዳና ለድንግል
2.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.ቅድስት ኤልሳቤጥ
5.አባ ዳንኤል
6.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
7.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ

=>+"+ ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል::
እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል::
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል::
በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ::
ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ::
ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ:: +"+ (መዝ. 91:12)

>

የፈለገ ጥበብ የዲጂታል ሚዲያን ይቀላቀሉ ለሌሎች ያጋሩ🙏🙏🙏

👉ዩቲዩብ (Youtube)

👉ቲክቶክ (Tiktok)

👉ኢኒስታግራም (Instagram)

👉ፌስቡክ (Facebook)

👉ቴሌግራም (Telegram)


✝✞✝ እንኩዋን ለአበው ቅዱሳን "አባ ዳንኤል" : "አባ ዸላድዮስ" : ወቅዱስ "ፊላታዎስ ሰማዕት" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝

+*" ማር ዳንኤል "*+

=>"ዘዓምድ" በሚል ስም ከሚታወቁ የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል 4ቱ ቅድሚያውን ይይዛሉ:: እነዚህም:-
1.ቅዱስ ስምዖን ዘዓምድ:
2.ቅዱስ አጋቶን ዘዓምድ:
3.ቅዱስ ዳንኤል ዘዓምድ እና
4.ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ ናቸው::

+"ዘዓምድ" የሚለውን ቃል ምሥራቃውያን በልሳናቸው 'THE STYLITE' ይሉታል:: የእኛው ቃል ደግሞ ከግዕዝ የተወረሰ ነውና በቁሙ ቢተረጐም "የምሰሶው" የሚል ትርጉምን ይይዛል:: ይህም በ2 ምክንያቶች ነው::

+አንደኛው ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን የፈጸሙት ከረዥም ምሰሶ ላይ ወጥተው በመጸለይ ስለሆነ ነው:: ሌላኛው ምክንያት ደግሞ እነዚህ አባቶች በዘመኑ ለነበሩ ምዕመናንና መነኮሳት አጽናኝ: አስተማሪ: መሪና ፈዋሽ በመሆናቸውና እንደ ምሰሶ ተተክለው ሳይነቃነቁ በመጸለያቸው ነው::

+ልክ ከዓለም ሃገራት ብዙ ስውራንን እና ቅዱሳን ነገሥታትን በመያዝ ሃገራችን ቀዳሚ እንደ ሆነችው ሁሉ ምሰሶ ላይ ወጥተው የሚጋደሉ ቅዱሳንም ሶርያውያንና ምሥራቃውያን ናቸው:: በዚህ ዕለትም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የታላቁን ቅዱስ ማር ዳንኤልን በዓል ታከብራለችና ከዜና ሕይወቱ ለበረከት ጥቂት እንካፈል::

=>ይህ ቅዱስ ሰው (በስዕሉ የሚታየው) ሶርያዊ ሲሆን ተወልዶ ያደገባት አካባቢ በቀድሞው አጠራር "ሃገረ ዓምድ" ይሏታል:: "ማር" የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን ቅድስናንና አለቅነትን የሚገልጽ ስም ነው:: በዚህ ስም ጥቂቶች ብቻ ሲጠሩበት ለሊቃውንትም: ለሰማዕታትም: ለጻድቃንም አገልግሏል::

+ቅዱሱ "ማር" ብቻ ሳይሆን "ዘዓምድ" ተብሎም ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እርሱም በፊት እንደ ጠቀስናቸው አበው ምሰሶ ላይ ተጠግቶ (ቆሞ): ትኩል ከመ ዓምድ ሆኖ በመጸለዩ ነው::

+ማር ዳንኤል በምድረ ሶርያ ስመ ጥር ጻድቅ ነው:: በዘመነ ጻድቃን መጨረሻ አካባቢ ከክርስቲያን ወገኖቹ ተወልዶ: በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድጐ: ገና በልጅነቱ ለቤተ እግዚአብሔር ተሰጥቷል::

+የወቅቱ የሃገረ ዓምድ ዻዻስ (አባ ዼጥሮስ) ለማር ዳንኤል ፍኖተ ጽድቅን (የሕይወት - የእውነትን ጐዳና) በማሳየት ከፍ ያለውን አስተዋጽኦ አበርክቷል:: አስተምሮም ለመዓርገ ክህነት አብቅቶታል::

+ቅዱሱ በእድሜው እየበሰለ ሲሔድ ግን ምርጫው ምናኔ ሆኖ በመገኘቱ በፈቃዱ ወደ በርሃ ሔደ:: በዚያም መዓርገ ምንኩስናን ተቀብሎ በጾም: በጸሎትና በትሕርምት ይጋደል ገባ::

+ማር ዳንኤል በበዓቱ ተወስኖ ሲጾም: ሲጸልይና እግዚአብሔርን ሲያመልክ ከጸጋ (ከብቅዓት) ደረሰ:: ብዙ ተአምራትንም በመሥራቱ ስም አጠራሩ በአካባቢው ተሰማ:: እርሱ ግን ከሰው: ይልቁንም ከሴቶች ይርቅ: ላለማየትም ራሱን ይከለክል ነበር::

+ለአንድ መናኝ በሰዎች መካከል: ይልቁንም በተቃራኒ ጾታ ጐን መኖር ያልተፈቀደ: ፈታኝም ድርጊት ነውና ከፈጣሪው ጋር እንዲህ የሚል ቃልን ገባ:: "ከዚህ በሁዋላ ሴት ልጅን አላይምም" አለ:: በእንዲህ ያለ የቅድስና ሕይወት ሳለ ወላጅ እናቱ ልታየው ተመኘች::

+ወደ ገዳሙ መጥታም "ልጄ! ላይህ ሽቻለውና ልግባ : ወይ ብቅ በል" ስትል ላከከችበት:: ቅዱሱ ግን "እናቴ! ሴትን አላይም ብየ ቃል ስለ ገባሁ አልችልም" ሲል መለሰላት:: በጣም አዝና "እኔ ወልጄ: አዝዬ: አጥብቼ: አሳድጌ እንደ ሌሎች ሴቶች አስመሰልከኝ? በል ፈጣሪ 2 ሴቶች በአንድ ልብስ ሆነው ይዩህ!" ብላ ረግማው ወደ ቤቷ ተመለሰች::

+የሚገርመው ማር ዳንኤል በበርሃ የበቃውን ያህል እናቱ በዓለም ሳለች በጐ ሰርታለችና እርሷም ጸጋውን አብዝቶላታል:: በምን ይታወቃል ቢሉ:- ያቺ የተናገረቻት ነገር ሁሉ ደርሶበታልና::

+አንድ ቀን ለገንዘብ ሲል አንድ ሰው የገደለውን አምጥቶ በቅዱሱ በር ላይ ጣለው:: ቅዱሱም ያለ አበሳው ታሥሮ ወደ ከተማ ሲወሰድ መታጠቢያ (shower) ቤት ውስጥ የነበሩ ሴቶች ሊያዩት ቸኩለው: አንድ ልብስ ለብሰው ወጥተዋል:: ማር ዳንኤል ይህንን ሲያይ የእናቱ ነገር ትዝ ብሎት ሳቅ ብሏል::

+በታሠረበት ቦታ ግን የሞተውን ሰው በጸሎቱ በማስነሳቱ በክብር ወደ በዓቱ ተመልሷል:: የከተማዋ ንጉሥም ገዳምን አንጾለታል:: በተረፈ ዘመኑም ለብዙ ቅዱሳን አባት ሆኖ እስከ እርጅናው አገልግሏል:: በዚህች ቀንም በክብር ዐርፏል::

+*" አባ ዸላድዮስ "*+

=>አባ ዸላድዮስም በተመሳሳይ የዘመነ ጻድቃን ፍሬ ነው:: በርሃ ከገባባት ቀን ጀምሮ ጾምን: ጸሎትን አዘውትሮ ክርስትናውን አጽንቷል:: ሙሉ እድሜውን በጐ በመሥራት በማሳለፉ ፈጣሪውን ሲያስደስት ለብዙዎች አንባ: መጠጊያ መሆን ችሏል::

+በጸሎቱ አካባቢውን በደህንነት ይጠብቅ ነበር:: ምዕመናን እንኩዋን ወደ እርሱ መጥተው ተባርከው ባሉበት ቦታ ሁነው ተማጽነው እንኩዋ መሻታቸውን አያጡም ነበር:: ምንም ያህል ኃጢአተኞች ይሁኑ እግዚአብሔር ስለ አባ ዸላድዮስ ሲል ይለመናቸው ነበር::

+አንድ ቀን አንድ ነጋዴ ሰው በባሕር ላይ ሲሔድ ድንገት ማዕበል ይነሳበታል:: ብቻውን ነበርና ጨነቀው:: እሱ ያለባት ጀልባም ትንሽ በመሆኗ ልትሠበር ደረሰች:: መዳን እንደ ማይችል ሲያውቅ ተስፋ ቆረጠ::

+ድንገት ግን አባ ዸላድዮስ ትዝ ብሎት ቀና ብሎ "ጌታየ! ስለ ቅዱሱ አባት ብለህ ብትምረኝ ለወዳጅህ መቶ ዲናር ወርቅ እሰጣለሁ" ሲል ተሳለ:: ቃሉን ተናግሮ ሳይጨርስ አባ ዸላድዮስ በጀልባው ላይ ቁጭ ብሎ ታየው:: ማዕበሉም ጸጥ እንዲል አድርጐ ከወደብ አድርሶ ተለየው::

+ነጋዴውም ፈጣሪውን ስለ ድኅነቱ እያመሰገነ 100 ዲናር ወርቁን ይዞ አባ ዸላድዮስን ፍለጋ ወጣ:: የሚያውቀው በዝና ብቻ ነበርና:: መንገድ ላይም ሞሪት የሚባል መሪ አግኝቶ ከአባ ዸላድዮስ በዓት ደረሰ::

+ከቅዱሱ ተባርኮ ወርቁን ቢያቀርብለት "ልጄ! እኔ ይህን አልፈልገውም:: ለነዳያን በትነው" አለው:: ነጋዴው ሲወጣ ግን ሞሪት (መሪው) ገንዘቡን ፈልጐ ገደለውና ከጻድቁ በር ላይ ጣለው:: ሃገረ ገዢውም ሲሰማ አባ ዸላድዮስን አሠረው::

+ጻድቁ ግን የሞተውን ባርኮ አስነሳውና "ማን ገደለህ" ቢለው "ሞሪት" ሲል መልሷል:: መኮንኑ ሞሪትን ሊገድለው ቢልም "የለም" ብሎ ነጋዴውን በደስታ: ሞሪትን ደግሞ በንስሃ ሸኝቷቸዋል:: አባ ዸላድዮስ ግን ተረፈ ዘመኑን በቅድስና ሲጋደል ኑሮ በክብር ዐርፏል::

+*" ቅዱስ ፊላታዎስ ሰማዕት "*+

=>"ፊላታዎስ" ማለት "መፍቀሬ እግዚአብሔር - እግዚአብሔርን የሚወድ: እርሱም የሚወደው" ማለት ነው:: ቅዱሱ የዘመነ ሰማዕታት (3ኛው መቶ ክ/ዘመን) ፍሬ ሲሆን ለየት ያለ ታሪክ ያለው ቡሩክ ወጣት ነው::

+እርሱ የባለ ጸጐች ልጅ: ስለ ክርስትና ምንም ሰምቶ የማያውቅ ሕጻን ነበር:: ወላጆቹ የሚያመልኩት ላምን ሲሆን የአካባቢው ሰው ደግሞ ለጸሐይ ይንበረከክ ነበር:: ቤተሰቦቹ ስለ አምልኮ ሲጠይቁት "እናንተ የምታመልኯቸው ፍጡራን ስለ ሆኑ አልፈልግም" አላቸው::

+ሕጻን ቢሆንም ስለ ፈጣሪው ተመራመረ:: በመጨረሻውም ፀሐይን "አንተ ምንድነህ?" ቢለው "እኔ ፍጡር ነኝ" ሲል መልሶለታል:: በዚያች ዕለት ግን ቅዱስ መልአክ ወርዶ: ሁሉን ነገር አስተምሮ የክርስቶስ ወታደር አድርጐታል::






††† እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ: ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

✝✞✝ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ✝✞✝

††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው:: በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው:: ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል::" (ማቴ. 7:17)

መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብጹዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል:: ቡርክተ ማሕጸንም እንላታለን:: የተባረከ ማሕጸኗ የተባረከ ልጅን ለ9 ወር ተሸክሟልና::

በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕጻን እርሷን መስሎ: እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና:: አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብጹዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች::

በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ:: በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር::

ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት:: መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኩዋ የመጮህ እድል አልነበረውም:: ምክንያቱም የሚሰማው አልነበረም::

በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ:: የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር:: ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ: ካልሆነ ደግሞ ሃገርን ጥሎ በዱር: በገደል መሰደድ ነበረበት::

እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም:: ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና::

ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብጽዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) ፍሬ ናቸው:: በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ:: ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው::

በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት (ኢጣልያዊት) ብጽዕት ኢየሉጣም በመበለትነት (ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ) ትኖር ነበር:: ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና 3 ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው: ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር::

እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕጻን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች:: ሃብት ንብረቷን: ወገንና ርስቷንም ትታ: ሕጻን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች:: መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም::

እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት:: ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት:: መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው" አለችው:: ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው:: ሞክሼ (ሞክሲ) ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ" አለችው::

"ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የ3 ዓመት ሕጻን ፈልገህ አምጣና ተረዳ" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው:: የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር::

ቅዱሱ ሕጻን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕጻን - ደስ የተሰኘህ ሕጻን እንዴት ነህ" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታየ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል:: አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ" አለው::

በሕጻኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ" አለው:: ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ: ስሜ ክርስቲያን ነው:: እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው" ሲል መለሰለት::

ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕጻን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ:: ከዚህ በሁዋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር (እጽፍ) ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም::

በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ::
*7 ብረት አግለው በዐይናቸው: በጆሯቸው: በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ::
*በ4 ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው::
*በእሳት አቃጠሏቸው::
*ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ::
*ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው::

እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ:: ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት:: ከብዙ ስቃይና መከራ በሁዋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕጻኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል:: ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል::

††† ቅዱስ አብድዩ ነቢይ †††

††† "አብድዩ" ማለት "የእግዚአብሔር አገልጋይ" ማለት ነው:: ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን የቅዱስ ኤልያስ ታላቁም ደቀ መዝሙር ነው:: ቅዱሳን ነቢያት ዮናስና ኤልሳዕም ባልንጀሮቹ ነበሩ::

ቅዱስ አብድዩ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የከሃዲው ንጉሥ የጦር መሪ ሆኖ በሃምሳ አለቃነት አገልግሏል:: ግፈኛዋ ኤልዛቤል ነቢያተ እሥራኤልን ስታስፈጅ 50ውን በአንድ ዋሻ : 50ውን ደግሞ በሌላ ዋሻ አድርጐ አትርፏቸዋል:: 900ው ግን ተጨፍጭፈዋል::

ያተረፋቸውንም ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ መግቧቸዋል:: አክአብና ኤልዛቤል ከሞቱ በሁዋላም ቅዱስ ኤልያስን ተከትሎ ሹመቱን ትቷል:: እግዚአብሔር ገልጾለትም ትንቢት ሲናገር: ሕዝቡንም ሲገሥጽ ኑሯል::

በብሉይ ኪዳን ካሉ የትንቢት መጻሕፍትም በጣም አጭሩን የጻፈው ይሕ ነቢይ ነው:: ትንቢተ አብድዩ ባለ አንድ ምዕራፍ ብቻ ናትና:: ቅዱሱ በዚህች ቀን ዐርፎ ወገኖቹ ቀብረውታል::

††† አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን:: በይቅርታው ኃጢአታችንን ይተውልን:: ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን::

††† ጥር 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ
2.ቅዱስ አብድዩ ነቢይ
3.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
4.ቅድስት ሶፍያ
5.ቅድስት አድምራ
6."11,004" ሰማዕታት (ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር በሰማዕትነት ያለፉ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
2.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
3.ቅድስት ክርስጢና
4.ቅድስት እንባ መሪና

††† "በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር: ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ: በልብህም:- 'ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው?' የምትል አንተ ሆይ! የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል:: እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ: ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን: 'ከዚያ አወርድሃለሁ' ይላል እግዚአብሔር::" †††
(አብድዩ 1:3)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር
†††

የፈለገ ጥበብ የዲጂታል ሚዲያን ይቀላቀሉ ለሌሎች ያጋሩ🙏🙏🙏

👉ዩቲዩብ (Youtube)

👉ቲክቶክ (Tiktok)

👉ኢኒስታግራም (Instagram)

👉ፌስቡክ (Facebook)

👉ቴሌግራም (Telegram)

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.