እውነተኛ ወዳጅ፥ ወዳጅ መኾኑ የሚታወቀው ጓደኛውን መገሠጽ ሲችል ነው፡፡ ኹላችንም በየጊዜው ኃጢአት እንሠራለን፡፡ አብዛኞቻችን ደግሞ ኃጢአታችንን እንዳላየነው ኾነን ለማለፍ እንጥራለን፡፡ ለራሳችን ይቅርታ እንቸራለን፡፡ ወይም ምንም እንዳላጠፋ ሰው ለመምሰል እንሞክራለን፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሰዓት እውነታውን በትክክል እናይ ዘንድ ዓይናችንን የሚከፍት እውነተኛ ወዳጅ ያስፈልገናል፡፡
አንተ ሆይ! እስኪ ራስህን መርምር፡፡ ጓደኛህ እውነታውን እንዲያይ ታደርጋለህ? ጓደኛህ ኃጢአት ሠርቶ ሲያበቃ ለራሱ ይቅርታ ሲያደርግ ይቅርታው ያደረገው ይቅርታ ትክክለኛ እንዳልኾነ እንዲያውቅ ታደርጓለህን? እንዲህ እውነታውን ስትነግረው ምናልባት ጓደኛህ አለአግባብ ሊቈጣህ ይችላል፡፡ ታዲያ ሲቈጣህ ለመታገሥ ዝግጁ ነህን? ወይስ ከዚህ በተቃራኒ የጓደኛህን ኃጢአት አይተህ እንዳላየህ ነው የምትኾነው?
ጓደኛ ስንመርጥ ከእኛ ጋር እውነተኛ ወዳጅ ሊኾን የሚገባውን መኾን አለበት፤ ስንቈጣው እንኳን ቁጣችንን ታግሦ ስናጠፋ የሚያርመን ሊኾን ይገባል፡፡ እንደዚህ ካልኾነ ጓደኝነት ጥልቀት አይኖረውምና፤ ጓደኞች ነን መባባላችን ጥቅም የለውምና፡፡
ልናውቀው የሚገባን ነገር ግን አለ፡፡ ጓደኛችን በሚያጠፋበት ሰዓት ተግሣጽ አስመስለን እንዲሁ ክብሩን በሚነካ መልኩ ልንናገረው አይገባንም፡፡ ተግሣጻችን ኹልጊዜ እውነቱን ብቻ እንጂ የተጋነነና ሌላውን መልካምነቱን የሚክድ መኾን የለበትም፡፡ ጥፋቱን ስንነግረው ኹልጊዜ በቀና ልብ እንደምንነግረው እርግጠኛ እንዲኾን ማድረግ አለብን፡፡ ይህን የምናደርገው ከፍቅራችን የተነሣ እንጂ ከቅናት ወይም ከንቀት እንዳልኾነ እንዲያውቅ ማድረግ አለብን፡፡ እውነተኛ ወዳጅነት ማለት ይህ ነውና፡፡
@memhrochachn