እንደምን አላችሁ?
የነቢያት ጾም ሰንበታት የራሳቸው ስያሜዎች እንደ ዐቢይ ጾም ያላቸው ሲሆን የነገው ሰንበት ከጌታችን ፱ቱ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው ስያሜውም ስብከት ይባላል!
ለነገው ቅዳሴ እንዲያግዝ የዕለቱ ግጻዌ ከነ ዝማሬው ከelam የቴሌግራም ገጽ በክቡር አባታችን አባ ኃይለ ሚካኤል የተዘጋጀ እናጋራችኋለን፤
መልካም በዓል
መዝሙር ዘስብከት ከታኅሣሥ ፯ - ፲፫
(በ፪/ዩ) ወልዶ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ፤ አክሊለ ሰማዕት ሠያሜ ካህናት ወተስፋ መነኮሳት ወልዶ መድኅነ ንሰብክ ወልዶ መድኅነ ንሰብክ
ትርጕም፦
ቅድመ ዓለም የነበረ መድኃኒት ልጁን እንሰብካለን፤ የሰማዕታት አክሊል፣ ካህናትን የሚሾም፣ የመነኮሳት ተስፋ የሆነ መድኃኒት ልጁን እንሰብካለን።
የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፩፥፩ - ፍ፤
፪ጴጥ ፫፥፩ - ፲፤
ግብ ፫፥፲፯ - ፍ፤
የዕለቱ ወንጌል፦ ዮሐ ፩፥፵፬ - ፍ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
የዕለቱ ምስባክ፦
ፈኑ እዴከ እምአርያም፤
አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ፤
ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ ነኪር። መዝ ፻፵፫፥፯፤
ትርጉም፦
እጅህን ከአርያም ላክ፤
ከብዙ ውኃም አድነኝ፤
ከባዕድ ልጆችም አድነኝ።
ምሥጢር፦
ረድኤትህን ከአርያም ላክ አንድም ልጅህን በሥጋ ላክ፤
ከብዙ ጦር/ሠራዊት አድነኝ አንድም ከፍትወታት እኩያት ከኃጣውእ ርኩሳት ከፍዳ ከመከራ ነፍስ ፈጽመህ አድነኝ።
ከነናምሩድ ከነሳኦል ልጆች እጅ አድነኝ አንድም ከዲያብሎስ ወገኖች ሥልጣን አድነኝ።
ክንድ ከአካል ተገኝቶ ከአካል ሳይለይ ይኖራል፤ እሱም ከአብ ተገኝቶ ከአብ ሳይለይ ይኖራልና። ቦ የሰው ኃይሉ በክንዱ እንዲታወቅ የአብም ኃይሉ በወልድ ታውቋልና። ቦ ክንድ ከአካል ሳይለይ የወደቀ አንሥቶ ይመለሳል፤ እሱም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ የወደቀ አዳምን አንሥቶ ተመልሷልና። ቦ በክንድ የራቀ ያቀርቡበታል የቀረበ ያርቁበታል፤ የራቀ አዳምን አቅርቦበታል የቀረበ ዲያብሎስን አርቆበታልና። ቦ በክንድ አሥረው ያጠብቁበታል ወርውረው ያርቁበታል፤ ዲያብሎስን በእሳት ዛንጅር ይዞ በነፋስ አውታር አሥሮ ከሰው ሕይወት አርቆበታልና። ቦ በክንድ የታሠረ ይፈቱበታል የተፈታ ያሥሩበታል፤ የታሠረ አዳምን ፈትቶበታል የተፈታ ዲያብሎስን አሥሮበታልና። ኋላም ሑሩ እምኔየ ብሎ ያርቅበታል ንዑ ኀቤየ ብሎ ያቀርብበታልና እጅህን ላክ አለ።
መልእክት፦
ዛፍ ከሥሩ ሳይነቀል ጫፉ መሬት ነክቶ ይመለሳል የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢርም እንዲሁ ነው። ምሥጢሩ የዚህን ያህል ጥልቅና ረቂቅ ከሆነ በምሥጢረ ሥጋዌ ዙሪያ አምላክ እንዴት ሰው እንደሆነ ሰውም እንዴት አምላክ እንደሆነ ተመራምሬ እደርሳለሁ ማለት የውቅያኖስን ውኃ በእንቁላል ቅርፊት ቀድቶ ለመጨረስ እንደመሞከር ነው።
©
https://t.me/elam12