መባቻ


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha
Toifa: ko‘rsatilmagan


"ሰውነት"ን መረዳት፣ ሰው፣ለሰው በሰው ለመሆን ትልቁ አቅም ነው ።
ሰውነት ይልቃል!

Связанные каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Toifa
ko‘rsatilmagan
Statistika
Postlar filtri




ከጠመንጃ አፈሙዝ፣
እምነት ፅናት ሲቆም ተዋሕዶን አክሎ
በሰባሹን ስጋ እንጂ፣
ነፍስና እውነትን ማን ይገድላል ችሎ!


ዛሬ ኀሙስ ነው!

ወደ ሰውነት እንመለስ

ያሬድ ጌታቸው (ጃጆ)

የሆነ የሚያደክማችሁ ነገር የለም፤ የምናየውን ተመልከቱት የምንሰማውን አድምጡት ጉዟችንን አስተውሉት የሆነ አይነት ራዕይ ሳይሆን ሽሽት የወለደው ስደት፤ ከሆነ "ሰው" ከሚሉት ዓለም ሊመለሱ በማይመስል ሁኔታ ርቆ መንጎድ ... ቆም ብላችሁ ስታስቡት አይደክማችሁ ተስፋ እራሱ በእኛ ተስፋ ማድረግ ተስፋ የቆረጠ እስኪመስለኝ ዛሬ ላይ ቆሜ ነገን ሳየው ያስፈራኛል ጨለምተኝነትም አይደል ሊነጋ ሲል እንደጨልምም አምናለው ነገ ይነጋል አንዳለል እንደሰውኛ ጭላንጭላችን የተስፋ ሻማችን ላይ የመቃተቶች ትንፋሽ ድርግም ሊያደርጋት ያስፈራራናል።

ሰው ነን እና ምን እናድርግ እንደሰው በራሳችን እንደሰው ከሰው ጋር እንፈታዋለሁ የምንለው አሁን አሁን ከአቅማችን በላይ የሆነውን እንኳ ከእኛ በላይ ለሆነው አምላክ ለመስጠት ሁላ ግርዶሹን ጥሎብናል።

መንፈሳዊነት በቅርበት ገብቷቸዋል ያልናቸውም እኛ ራቅ ብለን ዓለማዊነትም መንፈሳዊነትም በእኩል ስበት የሚጎትቱን እስክንታዘባቸው ሆነዋል። ቋንቋው እዝነትና ፍቅር የሆነውን ፈጣሪ ልክ የሆነውን አምላክ ልክ ባልሆነ ቋንቋ ካላወራነው እያልን ኃጢዓት ለመጋገር መልካሙን ፍሬ በመርዝ ለውሰን በሐይማኖት ምጣድ ፖለቲካ እንጋግራለን።

አገር እንዲህ መላ አጥታ የእናውቅልሃለን ባለሃሳቦች ከአገርነት አንሰው ሆድ ሲያክሉ ማየት ራሱ እኮ ሚያጨልል ነገር ነው። ከፍ ሲሉ እኮ አቅምና ሁኔታው ወደታች ለመመለከት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ኃላፊነት በከፍታ ልታዩበት እንጂ ልትታበዩበት አይሁን!

ያኔ ..
ሁሉም ቀን ደስ ይላል!
@ymebacha


"ዝም አይነቅዝም" ቢሉ፣
ምለው ሳለ ዝም አልኩ
ይኸው ከራሴ ጋር አደናቆራለሁ፣
ወደውስጤ እየጮኹኩ!

ጃጆ


ዛሬ ኀሙስ ነው!

መምሰል ጥላነትም ነው በሌሎች ፀሐይ አቅጣጫ ራስን በፅልመት መሳል ነው።

ያሬድ ጌታቸው (ጃጆ)

ሕይወት በመሆንና በመምሰል የተዋቀረችም ነች። ሰውነት ከሰው እንዲቀዳ የተለያዩ አመለካከቶችና ከብዙዎች ሊቃረም ይችላል። ይኽ ደሞ ሰዋዊና ተፈጥሯዊ ነው ከደመነፍሳዊ ድርጊት ውጪ የሰው ልጅ ራሱን ሚሰራበት የተሰጠውን አዕምሯዊ አቅሙን ተጠቀሞ እውቀትን ጥበብን ከሕይወት እየቀዳ ማንነቱን የሚቀርፅበት ማህበራዊ ልምምድ ፥ ሰው መሆንነት ነው።

መሆን የራስን እውነት በመከተል ውስጥ የገነባነው እኛነትም ጭምር ነው። መምሰል ደግሞ ምናልባትም በሰው ዳና የት እንዲያደርስ በማናውቀው መንገድ እንደመጓዝ ነው።

መሆን እንደፀሐይም ነው፣ ያንን ማንፀባረቅ ነገን ትልቅ ሊሆን የሆነ የፀሐይነት ጅማሮ ነው ማንፀባረቅ መመሰል አይደለም ብርሃናዊ ሀሳብ ከጨለማ በላይ ገዥ ሀሳብ ነውና።

መሆን በአብሮነት ውስጥ አለ በአብሮነት ውስጥ የሚወለድ ሀሳብ አሸናፊ ሀሳብ የመሆኖች ራስን ፈጥሮ ትልቅ መሆንን ይሆናል አብሮነት ውስጥ ያለ ማይሞግት ማንነት ሀሳብ ያለገዛው ማንነት የመምሰል ሌላ መልኩ ነው።

መምሰል ጥላነትም ነው በሌሎች ፀሐይ አቅጣጫ ራስን በፅልመት መሳል ነው። አለፍ ሲል የሰውነት እኩለ ቀን ፀሐይ ስትወጣ በእግር የሚረገጥ ምንምነት!


በመሆን ውስጥ የምታጣው በመምሰል ምታገኘውን ነው። መሆን ብቻህን ቢነጥልህ እውነት በመሆን ውስጥ አለ ያኔ ብቻህን አይደለህም ተገፍተህ በትወድቅም ኅሊናህን ያለፀፀት ትንተራሳለህ።

መሆንን መምሰል፥ መምሰልን መሆን አይከተለው።

ሆናችሁ ዋሉ ያኔ ...

ሁሉም ቀን ደስ ይላል !




ዛሬ #ኀሙስ ነው!

ልናስብበት ፋታ
ልናልምበት የእንቅልፍ አፍታ
አጣን!

ያሬድ ጌታቸው (ጃጆ)

ዘመኑ የመረጃ ጅረት የበዛበት ፋታ የሚያሳጡ አጀንዳዎች ያለማሰለስ ወደኛ የሚነጉዱበት ሆነ። የቱን ይዘን የቱን እንድንጨብጥ ግራ ገብቶናል፤ በዚህም እረፍት አጣን፤ እፎይ ብሎ ተንፍሶ ራስን ማረጋጋት እስኪሳነን ድረስ ነገሮች ወጥረው ያዙን፤

የቱን ሀሳብ መዝዘን የቱን እንለቃለን? ለማሰብም ማሰብ ያስፈልጋል፤ አንዱን ስታስብ እሱን ሳትጨርስ ሌላ የሀሳብ ጎርፍ ደራሽ ሆኖ ይመጣል። ደራሹ እያንከባለለ ከጥልቁ ባህር ይከትሃል። ተረጋጋሁ ብለህ ማሰብ ስትጀምር፥ ሌላ አጀንዳ ማዕበል ሆኖ ከወዲህ ወዲያ ያላጋህ ይይዛል። ይኽም ያታክታል፥ ያዝላል።

ሕይወት ውጣ ወረዷ በበዛበት ከተራ ሀሳብ ሻል ያለውን እንዳናስብ አስበው እንዳያሳስቡን ገዥ ሀሳብ ሲያቀብሉን የነበሩት ሳይቀር በተራ ሀሳቦች ተሸንፈው እጅ ሰጡ። በወደቁበት በአጀንዳ እጃቸው ጠልፈው እያጣሉን የትክክል ፍኖት እኛ ነን ይሉናል።

ሀሳብን ከሃሳብ መዝዘን እንነሳልን የሃሳብ ሰበዝ ቢበዛ አክራማው አንድነቱን ካላነፀ፣ባለእጅ ካለተጠበበት ሰበዙ ተሰብስቦ ቢከመር ስፌት አይሆንም። እናም ባሉበት መርገጥ፣ ተራመድን ስንል መዳህ፣ መንፏቀቅን መረጥን ቆመን ስንሄድ የነበርን ሰማየ ሰማያትን በክንፋችን መቅዘፍ ሲገባን ትንሽነትን ከትልቅነታችን ውስጥ በመፈለግ ተራ ሀሳብ ምርኮ ሆንን።

ጥበብን ተጫምተን በማሰተዋል እንዳያራምደን፣ ጠብበን የጥበብ ጫማን ሰፋነው። ሰው ማከል ተፈጥሯችን ሆኖ ሳለ አውሬነትን ከዱር ተዋስን። ዛሬያችን በኛ ክፋት ከ*ፋ ሰውነታችን እጅ እጅ አለ። በትናንት እርሾ ቂም አቦካንበት፤ በዛሬ ምጣድ ላይ በቀል ጋገርንበት። የመጣው ሁሉ ትናንትን ያስናፍቀናል። ትናንት ናፋቂ ሆነነ የቀረነው እኮ ለትናነት አክብሮት እጦት የቆሙበትን መሰረት ከመካድ ባለፈ በመናድም በተጠመዱትም ነው። ወደፊት መራመድ ካቃተን ታድያ እንዴት የከፍታችንን ትናንት አይደለም ቁልቁለታችንን የጀመረበት ምዕራፍ አያስናፍቀን!

ልናስብበት ፋታ
ልናልምበት የእንቅልፍ አፍታ
አጣን

እርምጃችን የስጋት
ወጥቶ መገባት ከጀግንነት
ተቆጠረ

ቀልብያችን ከአቅሉ
ሰውነት ከፈጠረው ከቃሉ
ተጣላ

ፍርድ ቢዘገይ ከፈጣሪ
እኛው ፈራጅ እኛው መርማሪ
ሆንን

ከደስታው ልቆ ላዘኑ
ከደጃችን ድንኳኑ
ከረመ

የጀገነበት ትናንት ያለው
ዛሬን ወዴት ሊሄድ የጠፋው
ሆንን

ልንንኖርበት ተሰፋችንን ተገዳደሩት።

በዚህ ሁሉ ስንከሳር ውስጥ ሆነን ግን የቻልንበት...

ሁሉም ቀን ደስ ይላል!




ዛሬ ኀሙስ ነው!

የአንድ ወገን እውነት ፍትህን ታዛባለች!

ያሬድ ጌታቸው (ጃጆ)

"ያዘው ...ያዘው...ያዘው" የሚል ድምፅ ከውጪ ይሰማል፤ ታክሲ ውስጥ ያለ የቀኝ ጆሮ ሁሉ ወደ ተሰማው ድምፅ አሰገጉ እንድ አዳፋ ልብስ የለበሰ ወጣት ባዶ ማደበሪያ ነገር ይዞ ሲሮጥ ብቻ ይታየኛል፤ ያለንበት ታክሲ ረዳት ተሳፋሪ እንደሚጠራ ግማሽ ሰውነቱን ከውጪ አሳፍሮ "ያዘው ሌባ ሌባ" እያለ የአካባቢ ጥሪ በገራው ድምፁ ሞቅ አድርጎ እየተከተለ አገዛቸው ሲሮጥ የነበረው ልጅም በሰዎች ትብብር ተያዘ "የታባቱ "አለ ረዳቱ በኩራት የክትትሉ አካል እንደነበረ እየተሰማው ።

ይኸው ረዳት እዛው አካባቢ ሰዎችን አወረደ ፤ ሲጭን በማስፈራራት አይነት የሰባት ብር መንገድ ግንባሩን እንደመጋረጃ ሸብሽቦ የትም ሃያ ሃያ ብር ነው! ይላል።

አንተም እኮ "ያዘው ያዘው ብሎ አሯሩጦ ሚይዝህ የለም እንጂ እኮ ያው ያንተም ተግባር ከርሱ የተለየ አይደለም አልኩት በቀልድ እያዋዛው ። ብሶት የወለደው ተሳፋሪም እየሳቀ... "እውነቱን ነው! ፣ ልክ ነህ ፣ እውነት ብለሃል፣ አዎ ይሄስ ሰው ኪስ ገብቶ ከመስረቅ በምን ይለያል" እያለ ድጋፉን አድናቆቱን አዥጎደጎደልኝ የሚገርመው ከነዚህ ውስጥ በዋነኝነት ረዳቱን ወቃሽ እኮ ሰልፍ ሰርቆ ተራ ሲጠብቅ የነበረን አንድ ሰው ወደኋላ አስቀርቶ የገባ ነው 😊

ነገርየው ከዚህ ታሪክ ጋር ተመሳሳይነትም አለው ። በአርምሞ (meditation)መቆየት የሚያዝናናቸው አራት ጓደኛሞች ነበሩ። ለሰባት ቀናትም በአርምሞ ለመቆየት ይስማማሉ በዚህንም ጊዜ ቃል ማውጣት እንደሌለባቸው ስለተስማሙ ፍላጎታቸውን ሊያሟላላቸው የሚችል ሰው መቅጠር እንዳለባቸው ያምናሉ እናም ይቀጥራሉ።

በቀጣይ ቀን ማልደው የአርምሞ ተግባራቸውን ጀመሩ። ቀኑን በጥሩ ሁኔታ አለፉና መሸ ሲመሽም ረዳታቸው ኩራዝ ለኮሰ ጊዜውም እየገፋ ሲሔድ ላምባው ሊያልቅ ሆነ እነሱን ለመርዳት የተቀጠረው ሰው በሀሳብ ጭልጥ ብሎ ሩቅ ሔዷል።

ይህንን የተመለከተው አንደኛው ጓደኛቸው "ኩራዙን ተከታተለው እንጂ" ሲል ጮክ ብሎ ተናገረ። እሱን ተከትሎ ሁለተኛው ጓደኛቸው "ረሳኸው እንዴ መናገር አልነበረብህም እኮ" አለ።

ሦስተኛው ወዳጃቸው ተበሳጭቶ "እናንተ ሞኞች ለምንድን ነው የምታወሩት? ይላል" መጨረሻ የቀረው "ፀጥ ብዬ የቆየሁት እኔ ብቻ ነኝ" ብሎ ይታበያል። ግን ማንም ከሰባቱ አንዱንም ቀን በአርምሞ የተወጣ የለም አንዱ ሌላውን በመውቀስ
ብቻ ደከሙ፣ አንዱ አንዱ ላይ በመፍረድ የያዙትን አላማ ሳቱ።

ሌላን ለመውገር ብዙዎቻችን ድንጋይ ይዘናል እኛ ላይ ድንጋይ የሚያሲዘውን ግን ለማየት ለአፍታም አናስብም። የአንድ ወገን እውነት ፍትህን ታዛባለች ለመፍረድም ግራ ቀኝ ሊታይ ግድ ነው። አበው አትፍረድ የሚሉት ወደው አይደለም እኮ።

ሁሉም ቀን ደስ ይላል!




ዛሬ #ኀሙስ ነው!

ተስፋ ራሱ ልጅነትን ይመስላል።

ያሬድ ጌታቸው(ጃጆ)

ትናት አመሻሽ ወደቤት ለመሔድ የታክሲ ሰልፍ ይዤ የታዘብኩትን ነው ምነግራችሁ። በምስሉ ላይ የምትመለከቷት ታዳጊ ከእናቷ ጋር አሰልቺውን የታክሲ ተራ ይጠብቃሉ ልጅቷ ምናልባት የ12 ዓመት ትሆናለች፤ አታካቹን ሰልፍ ግን እጇ ላይ ባለ ጠመኔ (chalk ጠመኔ ምነድነው የሚል ካለ ብዬ ነው 😊) አስፋልቱ ላይ ትስላለች፥ ትፅፋለች እኔን ጨምሮ በዙ ሰው በአግራሞት ይመለከታታል። ኢትዮጵያ እወድሻለሁ፣ ሰላም፣ ጤና፣ ደስታ፣ ሀገር ፍቅር በሚስብ መልኩ መሻቷን ምኞቷን መውደዷን ፍቅሯን ተስፋዋን አለፍ ብላ ደግሞ ሌላ ቦታ ላይም ጤና ይሁን፤ ሰላም ይሁን፤ ደስታ ይሁን ለሀገሬ ብላ በልጅ አንደበቷ አገሯን ትመርቅማለችም።

እንዲህ ለአገሩ መልካም የሚያስብ አገሩን የሚወድ ልጅ ስታይ ተስፈኛ ትሆናለህ።

አንዳንዴ ወስብስብ ባለ ነገር ውስጥ ተስፋ ማድረግ ሞኝነት ይመስለኛል። ተስፋ አለማድረግ ግን ከተስፋ መቁረጥ የተለየ መሆኑን እዚህ ጋር ልብ ይሏል። እንደሀገር ደግሞ እንዲህ ነገሩ ሁሉ ጫፍ አልቦ በሆነበት፣ መኖርን እንደሰው ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ ሲሆን ጨለማው ይጎላል። እኛ በአዋቂነት በተጨባጭ ምድር ላይ ያለውን ነገር ለምናውቅ፣ በብዙ ማሰላሰል ውስጥ ሆነን የዛልንበትን እውነት ርቆ የተሰቀለብን አንድነት ሰላም ፍቅር ደስታ ወይንም ራሳችንን ያሳመንነው ነገር በተስፋ አቅርበን ለማየት እንዲሳነን ሆነናል ወደንም ባይሆን። ታዳጊዋ ግን የዚህ ዓለም ክፋት ያልጎበኘው፣ አብዝቶ መልካሙን በሚያየው ልቧ መሬት ላይ ስብከቷን ፃፈች።

ተስፋ ራሱ ልጅነትን ይመስላል ልበል። ለራስህ በየዋህነት፣ በቅንነት ነገ ጥሩ ይሆናል ብሎ በተጨበጠውም ባልተጨበጠው፣ ላይያዝ ጭራው በሸጎረው ሁነት ላይ ሁሉ እያሳሳቀ፣ እየደለለ የዛሬን ክፋት የሚያስረሳ አንድም ወደነገ የሚያደርስ አፉ የሚጣፍጥ ኩልትፍ ልጅ አይነት።

በጣም ያስገረመኝን ነገር ልንገራችሁ፤ ልጅቷ እነዚህ መልካም ሃሳቦች በድርብ ፅሁፍ እያደመቀች ትፅፋለች። ተራ የያዙበት ሰልፍ ተንቀሳቀሰ። እናት የልጇን እጅ አፈፍ አድርጋ ይዛ ወደፊት ተነሽ እያለች ትጎትታለች ታዳጊዋም እናቷንም መታዘዝ ፈልጋለች የጀመረቸውን ፊደል መጨረስም እንዲሁ "ፍ"ን ፅፋ አስውባለች "ቅ"ንም ወደመጨረሱ ላይ ነበረች "ር" ብላ እንደምንም እየተንጠራራች ጨርሳ ብድግ አለች።

ለመፃፍ የሄደችበት መንገድ እንዴት መሰላችሁ መንገድ ላይ አንጥፎ የሚነግድ "ሕገወጥ" ነጋዴ ደንብ አስከባሪ መጥቶበት እቃውን ሰብስቦ ሊሮጥ ሲል ከተሸከመው ላይ አንድ እቃ ጥሎ እሱን ለማንሳትና ላለመያዝ ያሚያደርገውን እግሬ አውጪኝ አይነት ሁነት ነው። ፍቅር የሁሉ ማሰሪያ ውል ነው ፍቅር ካለ ጤናውም ሰላሙም እውን ይሆናል። "ፍ" ቅር እንዳይላት የተጨነቀች የልጅ ነብስ፥ ከሚቀር ባይዋብም ብላ ሀሳቧን ቋጭታለች። ስለፍቅር ከእናቷ ክንድ ጋር ትግል ገጥማለች፤ ስለፍቅር በፍቅር ዋጋ ከፍላለች። ይህ የሷ አቅም ነው ግን እኛስ አውቆ አላዋቂዎቹ አናሳዝንም ወይ? ብዬ በቁጭትና በሀሳብ ጦዝኩ

በቃችሁ ቢለን ደግሞ ...

ሁሉም ቀን ደስ ይላል!




ዛሬ #ኀሙስ ነው!

መሽቷል ብለን ምናድበሰብሰው ሁሉ በብርሃን ራሱን ይገልጣል።

ያሬድ ጌታቸው(ጃጀ)

ስራን ወደነው፣ስራን የተሻለ እስክናገኝ፣ ስራን አማራጭ አጥተን፣ ስራን በተለያየ የሕይወት አመለካከት ውስጥ ሆነን ልንሰራው እንችላለን።

ፊዚክስ ስራን ተሰራ የሚለው የሆነ ጉልበትን ተጠቅመን አንድን ነገር ማንቀሳቀስ ወይም የጉልበቱን አቅጣጫ ተከትሎ ሲንቀሳቀስ ነው ይለናል። ይህንን ሁሉ ግን ማሰብ ይቀድመዋል ካላሰብን ማሰብ ካልቀደመ ነገርን እንዴት ለምን እንደምናደርገው ካላወቅን ስራ ሊሰራ አይችልም ሊሰራ ቢችልም ግን በተሳሳተ ወይም ልክ ባልሆነ መንገድ ሊሆን ይችላል።

ጡረታ ስራን አያቆመውም ሰው ስራ አቆመ የምለው ማሰብ ሲያቆም ነው። አንድ ዘመኑን ሲያገለግል የኖረን ሰው አስቡ እድሜ ገደብ ሆኖ ቢሰናበትም ስራ አያቆምም የአካልና የቅልጥፍና ጉዳይ ይሆናል እንጂ ሰዎች ከጡረታም በኋላ የተሻለ አቅምና የሕይወት ልምድ፣ እውቀትና ክህሎት ባለቤት ስለሚሆኑ በማማከር፣ በማሰልጠን፣ አልፎም አገርን እሰከመምራት ይደርሳሉ።

ያለንበትን ስራ ወይም የስራ ኃላፊነት ለእኛ የተገባ አይደለም ብለን ልናስብ እንችል ይሆናል ግን እስካለንበት ድረስ ግዴታውንና ኃለፊነቱን መወጣት የክፍያ ብቻ ሳይሆን የህሊናም ጉዳይ ነው መሽቷል ብለን ምናድበሰብሰው ሁሉ በብርሃን ራሱን ይገልጣል። ይህ ደሞ ያለፈን ዞረው ሲያዩ ደስ የማይል ገፅ አለው ፀፀትም የኅሊና ወቀሳንም ሊያሰከትል የሚችል። የዛሬ ስራን በአግባቡ መወጣት አማራጭ ላልከው ሃሳብ ለምታቅደው የራስ ዕቅድ የነገ ክፍያ ነው። ሚቀናንም እንደዚያ ሲሆን ነው።

የተነሳሁበትን ሀሳብ የሚደግፍ አንድ ታሪክ ላጋራችሁና ልቋጭ።

የበርካታ ዓመታት ልምድ ያካበተ ሽማግሌ አናፂ ጡረታ ለመውጣት በዝግጅት ላይ እያለ ቀጣሪውን ከቤት ግንባታ ስራው ለቅቆ የጡረተኝነት ዘመኑን የተረጋጋ ሕይወት ከሚስቱና ከቤተሰቡ ጋር ማሳለፍ እንደሚፈልግ ይነግረዋል።

ቀጣሪውም ጎበዝና ብዙ ልምድ ያለው አናፂው ስራውን ሊለቅ መሆኑ ትንሽ በስጨት አድርጎታል። ነገር ግን አንድ ተጨማሪ ቤት እንዲገነባለት ይጠይቀዋል።

አናፂውም በአሰሪው ሀሳብ ይስማማል። ይሁን እንጂ እንደከዚህ ቀደሙ በስራው ከልቡ አልነበረም። እናም ቤቱን ለመገንባት ሙያዊ ጥበብ በጎደለውና በተጣመመና በማይረባ ግብዓት የመጨረሻ የሆነውን ሥራ በሚያሳዘን ሁኔታ ያከናውናል።

አናፂውም ስራውን አጠናቅቆ ቀጣሪው ቤቱን ለመመልከት መጣ ዙሪያ ገባውን ከተመመከተ በኋላ፣ ቤቱን ከመዝጋቱ በፊት የዋናውን በር ቁልፍ ለአናፂው ይሰጠዋል። "ይኽ ያንተ ቤት ነው ፤ ላንተ የምሰጥህ ስጦታዬ" ። ይህ ለአናፂው ያልጠበቀውና ያልገመተው ድንገተኛ ነገር ነበር።

ምንም እንኳን እጅግ በጣም ጥሩ አይነት ድንገቴ ደስታን የሚያጭር ሊሆን የተገባ ቢሆንም፥ አናፂው ከጥሩ ስሜት ይልቅ ሀፍረት ነው የተሰማው የርሱ ቤት መሆኑን ቢያውቅ ኖሮ ልዩ አድርጎ ይሰራው ነበር ። እናም አሁን በጥሩ ሁኔታ ባልተገነባ ቤት ውስጥ ሊኖር ግድ ሆነ።

የዛሬው አመለካከትህ ወይንም ምርጫህ ነገህን ሚወስን ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ነገን በብልሃት መገንባት ግድ ይላል።

የሰራንበት

ሁሉም ቀን ደስ ይላል!






ዛሬ ኀሙስ ነው!

ስልክሽን?

ያሬድ ጌታቸው (ጃጆ)

ቁጭ ባልኩበት ዓመታትን የኋሊት ተንደረደርኩ፤ ወደኋላ ስሄዴ ከምንም በላይ መልካሞቹ ትዝታዎች ይጎሉብኛል። መልካም ያልሆኑትን ሁነቶች ላስታውስ እችላለሁ ግን ዛሬን እንዳዲስ ከተመምኩበት ግን የትላንት ህመሜ ላይ ነኝ አልዳንኩምም ያለፈው ጊዜዬ ይቅርታ ወይ ፀፀት (አምኛለሁ፤ ልክ አልነበርኩም ብሎ የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅና ለአዲስ ሕይወት ራስን መግራት)እንደጎደለው ስለሚሰማኝ።

መዳረሻዬ ዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት አያለሁ የነበረኝ ውብ ጊዜ ላይ አረፈ። አቤል የሚባል ወዳጅ ነበረኝ፤ ሁለት በምልክት ቋንቋ የሚግባቡ ጓደኛሞችን አይቶ ሰፈራችን የሆነውን ልንገርህ ብሎ ያጫወተኝን እውነተኛ ገጠመኙን አስታውሳለሁ።

ልጅቷ ሲበዛ ቆንጆ ናት ሁሌም ባለታሪኩና ሌሎች ጓደኞቹ በሚቀመጡበት መንገድ ከትምህርት ስትመለስ ይተያያሉ ከመተያየት አልፈው የግንባር ሰላምታ መሰጣጠት ይጀምራሉ። ለልጅቷ ያለውን መሻት የተረዱ ጓደኞቹ የርቀቱን ሰላምታ ወደ አካላዊ ሰላምታ እንዲለውጠውና ተግባቦቱን ከፍ እንዲያደርግ ግፊት ያደርጉበታል።

የሆነ ቀን ስትመጣ ከተቀመጠበት ተነስቶ ወደ ልጅቷ አመራ። አላሰፈረችውም እጇን ለሰላምታ ዘረጋችለት ተጨባብጠው ትከሻቸውን አሳሳሙ። ሁለቱም በምልክት ቋንቋ እንደመጀመሪያ ቀን ያህል አፉን ያለድምፅ እና እጆቹን እያንቀሳቀሰ ተግባቡ።

መቼም አንድን የሚመኟትን ሴት በጠበሳ ሂደት ወስጥ ስልክ ጠይቆ መቀበል በ90ዎቹ የቁጥሩን ያህል ፐርሰንት እንደመጓዝ የሚቆጠር ስኬት ነበር።

ዘመኑ " በስልክ አነጋግሪኝ በቀጭኑ ሽቦ " የሚባልበት የቤት ሰልክ ዘመንም አይደል😃 እናም ይህ ፍርሃትና ፍቅር ያደናበሩት ወጣት አውራጣቱን ወደጆሮው፣ ትንሿ ጣቱን ወደ አፉ ቀስሮ በምልክት ስልክ ቁጥሯን ጠየቃት። እሷና ገፋፍተው የላኩት ጓደኞቹ እኩል ሳቁ እሱ ግራ ተጋብቷል፥ ምን እንዳሳቃቸው የገባው ዘግይቶ ሳቃቸው ሲያባራ ነው። ፀጉሩን እያሻሻ በሀፍረት ፈገግታ ተመለሰ ጓደኞቹም እንዳዲስ በሳቅ ተቀበሉት።

አስባችሁታል የቤት ስልክ ተሰጥቶት ደውሎ መስማት የተሳናትን ልጅ ስም ጠርቶ አቅርቡልኝ ሲል። 😃

ዘመን ግን ስህተትን ያርማል፤ አንዳንድ ስህተቶችን ዛሬ ላይ ልክ ያደርጋቸዋል። መስማትና መናገር የተሳናትን ልጅ በምልክት ቋንቋ ስልክ የጠየቀው በዛሬ ማዕዘን እይታ፥ ሞባይል ባለበት ዘመን ቢሆን በምስልም በቃላትም በከፊል መግባባቱን እውን አድርጎት ልክ አያደርገውም ነበርን? በጊዜ ውስጥ መልስ አለ።

የትናንትን ድክመት ዛሬ ላይ አምጥተን ብትነታረክበት ለትናንት ልኩ አይደልም የትናንትን ክፍተት ግን በዛሬ ብንሞላው ትናንትን ሙሉ ከማድረግ ባለፈ ዛሬን አቁሞ ለነገ መደላድል ይሆናል።

ሁሉም ቀን ደስ ይላል!


ዛሬ ኀሙስ ነው!

ያሬድ ጌታቸው (ጃጆ)

በሰዎች የሚደረግ፣ የሚነገር በጎ ቃል፥ መልካም ሃሳብ ሁሉ የፈጣሪ መልኩ ነው ።

አንድ የፌስቡክ ወዳጄ በውስጥ መስመር እንዲህ አለችኝ ...

"ሀሳብህ ከሀዘን መልሶኛል ፈጣሪ ጥበብን ይጨምርልህ"

ከዛማ አሜን አልኩ ጥበብ ያለው ሰው እንዴት ፈጣሪውን እንዲፈራ፣ እንዴት በማስተዋል እንዲራመድ ያውቃል፤ እንዴት በእውቀት በሕይወት መንገድ እንዲራመድ ... ምኑ ተዘርዝሮ ያልቃል ጥበብ ሲጨመርልህ እንዴት በኑረት ውስጥ ያሉ ሰዋዊ መስተጋብሮችን፣ ትናንትንና ዛሬን እንደምን ከነገ ጋር በእውቀት በማስተዋል አስታርቆ መሄድ እንዲቻል ፣ ፈተናንም ተቋቁሞ እንዴት እንዲታለፍ መንገዱ፥ ዘዴው ይብዛልህ እንደማለት እኮ ነው። ይኼ ሁሉ የጎደለውና ያነሰው ሰው ታድያ እነዚህ ሁሉ ይብዙልህ ተብሎ መመረቅ የት ይገኛል ?

ምንም እንኳ ሀዘን የሕይወት አንዱ መልኳ ቢሆንም ከሀዘን መንገድ መመለስ፣ ከሀዘን መፅናናት፣ መበርታት፥ብርታትን ሊበረታ ሊጠገን ራሱን ያዘጋጀ ልብና አበርቺ ቃልን ይፈልጋል። በሰዎች የሚደረግ፣ የሚነገር በጎ ቃል፣ መልካም ሃሳብ የፈጣሪ መልኩ ነው። በዛው ልክ ተቃርኖውን ስናደርግ ደግሞ ከሰይጣን ምድራዊ ተልዕኮ እዝ ስር እንደሆንን ነው።

የዛሬ ሳምንት በፃፍኩት የ"ዛሬ ኀሙስ ነው!" ሀሳብ፥ ከሀዘኗ መመለሷን ስትነግረኝ የምር ደስ አለኝ። ለራስ የተመከረ ምክር ከራስ አልፎ ሌሎች ገንዘባቸው ሲያደርጉት ወደ ደስታ ተለውጦ ማየት ልብን ያሞቃል።

ሐዘን፥ለእንባም ለመብሰልሰልም ልክ ካልተበጀለት የት ይዞን እንዲሄድ አናውቅም ከዚያ አድካሚ መንገድ መመለስ ድብቁን አቅም መጠቀምና የአይቻልምን መንፈስ ድል ማድረግ ነው።

የበረታንበት ...
ሁሉም ቀን ደስ ይላል!




ዛሬ ኀሙስ ነው!

ያሬድ ጌታቸው (ጃጆ)

ሰው የአቅሙ ልክ ነው፤ ሰው መሆን የሚችለው በሰውነት ልክ ነው ።

በቤተመንግስት ወይንም ክልክል በሆነ ቅጥር አጠገብ ስታልፍ ... ተመለስ!፣ ተሻገር!፣ ቁም! ብሎ እንደሚያባንን አይነት ጩኸት የቀላቀለ ድምፅ ሁሉ የሕይወት ውጣ ውረድ ፈተናዎች ሕይወት በደመነፍስ በለመደችው ተመሳሳይ መስመር እንዳትጓዝ እንደ ማንቂያ ደወልም ናቸው።

የተለመደ አይነት የሕይወት ዘዬ እንደአቀባበላችን አሰልቺ ሊሆን ድብርት በእኛነታችን ላይ የሰርክ ዳሱን ሊጥል ይችላል። ብዙ ሰው እስከአዕምሮ ሕመም የሚያደርስ ጭንቅ ድብርት ውስጥ የሚገባው በሕይወቱ አዲስ ነገር ማጣትና የነገሮች ድግግሞሽ፣ ደገጋግሞ በሕይወት መፈተን፣ ድንገቴዎችን መቋቋም አለመቻል፣ ስኬት ላይ አለመድረስ  እንደ ሰው መድከም አቅም ማጣት ሊሆን ይችላል።

የፈጠረን አምላክ እኛን ሊረዳ ሊያግዘን በድካማችን ምርኩዝ ሊሆነን ግድ የሚለው አምላክ ነው። አንዳንድ ፈተናዎች ግን አቅማቸው ራስ ላይ እስከማሰጨከን ይደርሳሉ። ግን አንድ እውነት አለ ሰው የአቅሙ ልክ ነው። ሰው ፈጣሪውን መምሰል እንጂ መሆን ልኩ አይደለም። ሰው የአቅሙ ልክ ነው፤ ሰው መሆን የሚችለውም በሰውነት ልክ ነው። እኛ ብለን ብለን ያቃተንን የሕይወት ፈተና በቃ እኔ አልቻልኩም ብለን ሊረዳን ይችላል ብለን ለምናምነው ሰው ከሌለም ሰው አቅም በላይ ሲሆን፥ አልያም ምስጢር ይሁን ብለን  ውስጣችን የቀበረነው እውነት ከሆነ፣ አምነን ሁሉ ገሀዱ ለሆነው ፈጣሪ አሳልፎ መስጠት ተገቢ እንደሆነ ይሰማኛል።   

የራሴን ልምድ ልንገራችሁ ፍፁም በነገሮች ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሰልችቼ፣ ተደብሬ አውቃለሁ  ፈተናዎች ሰዋዊ አቅሜን ሲፈታተኑኝ ግን በእኔ አቅም እንደማልመልሰው ሳውቅ ሁኔታዎችን ተቀብዬ ምፀልየው አንድ ፀሎት አለ።
 
"ፈጣሪዬ የምችልበትን  አቅም ብቻ ስጠኝ!" የሚል ነው።

ሰው ያጣውን ይጣ፣ መንፈሱ ከፍና ዝቅ ይበል፣ ሰው ራሱን ግን ማጣት እንደሌለበት የተገባ ነው። ሰው የራሱ ብቻ አይደለም ሰው የፈጠረው፣ ሰው የሚኖርለት፣ የሚኖርበት ሁሉ ነው። በራስ ላይ ሲከፋ በሞት አርፋለሁ ብሎ የከፋው ድካም ውስጥ መገኘት ሲያልፍም ለሌሎችም የቁም ሕመም መብሰልሰልም ጥሎ ሊያልፍ ይችላል።

ሰው  የመጣበትን አላማ ከዳር ማድረስ ባይችል በሙከራ ውስጥ ማለፍ ሌላው አሸናፊነት ነው። እናም ለጊዜው ድብርትም መሰላቸቱም አሸናፊ መሰሎ ቢታይ እንጂ ፈተና ሁሉ እንዲያባራ ዝናብ ነው።

ሕይወት መንታ መንገድ ላይ አቁማ ግራ ብታጋባህም ውሳኔ ትፈልጋለች። ውሳኔው  ግን ራስን በማትረፍ ውስጥ ለሌሎችም መትረፍ አንተነትን ለነገ አሳልፎ በማኖር ላይ የተቃኘ ሊሆን ይገባል ።

አንድ ትልቁ ነገር፥ ሰው እንደአማኝ ፈጣሪ መኖሩን ለሚቀበል ሰው በራሱ ላይ ስልጣን እንደሌለው አምኖ መቀበል ይፈልጋል። ያኔ ፈጣሪው እንዲረዳው አምኗል ማለት ነው።  

ፈተና ሲመጣ ከመጋፈጥ በላይ ቀድሞ በሕይወት ሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎችን ቀድሞ ማሰብ ደግሞ አርቆ መፃይ ሁነቶችን የመረዳት ሌላኛው አቅም ነው። ፈተና መፈተኑ ባይቀርም ለተዘጋጀ ማንነት ግን  እንግድነቱ እምብዛም ነው። ሰው በምድር ምልልሱ ብዙ ሆኗል በሌሎች የፈተናን ጥግ በሚመስል ደረጃ በመንፈሳዊ አስተምህሮት እንዲሁም በሕይወት  የቀሰምነው ልምድ እኛ ለሚገጥመን ፈተና የማለፊያ ጥበብም ጭምር ነው።

በፈተና ውስጥ በትዕግስትና በጥበብ ልናልፍ የተገባ ነው። ይኽ ምክር አሁን ላይ ላለሁበት የስሜት ከፍ ዝቅ ለእኔም ጭምር ነው!

ደግሞም ...

“ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።”
  — 1ኛ ቆሮንቶስ 10፥13

ሁሉም ቀን ደስ ይላል!



20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.

248

obunachilar
Kanal statistikasi