ጾመ ነነዌ፤ ከየካቲት 3-5 (ከሰኞ-ረቡዕ)
#ነነዌ
በጤግሮስ ወንዝ ምሥራቃዊ ቆሬ፥ ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 350 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የነበረች ታላቅ ከተማ ነች፡፡
ነነዌን በመጀመሪያ የቆረቆራት ናምሩድ ነው፡፡ /ዘፍ. 10፥11/
በጣም ሰፊ ነበረች “የቅጥሯም ዙሪያ በእግር የሦስት ቀን መንገድ ያህል ነበረ” /ዮና. 3፥3/
እግዚአብሔር አምላካችን ነነዌን “ታላቂቱ ከተማ” በሚል ቅጽል ጠርቷል፤ /ዮናስ 3፥2፤ 4፥11/
ስለ መጥፋቷ ነቢዩ ሶፎንያስ “...ነነዌንም ባድማ እንደ በረሃም ደረቅ ያደርጋታል” በማለት ትንቢት ተናግሮባታል፡፡ /ትን. ሶፎ 2፥13/፡፡ እንደ ነቢያቱ ትንቢት ታላቋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በኋላ ጠፍታለች፡፡
የነነዌ ሰዎች በስብከተ ዮናስ አምነው፥ ንስሐ ገብተው ድነዋል፤ በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ ስለ ንስሓቸውና ስለ እምነታቸው /‹‹...የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፡፡›› በማለት አመስግኗቸዋል፡፡ ማቴ 12፥41/
#ዮናስ_ነቢየ_አሕዛብ_ወሕዝብ
ዮናስ ማለት ርግብ፥ የዋኅ ማለት ነው፡፡
በዳግማዊ ኢዮርብአም ዘመነ መንግሥት /825-784 ቅ.ል.ክ./ በሰማርያ የነበረ ነው፡፡ /2ነገሥ. 14፥25/፡፡
ቊጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው፡፡
ነገዱ ከነገደ ይሳኮር ወገን ሲሆን፤ #አባቱ_አማቴ_እናቱም_ሶና(የሰራፕታዋ ደግ ሴት የሆነችውና ቅዱስ ኤልያስን በዚያ በረሃብ ዘመን የመገበችው ናት)፡፡
ኤልያስ በረሃቡ ዘመን ወደ ሰራፕታዋ መበለት ቤት በመሄድ "ውኃ አጠጪኝ ጥቂት ቁራሽም አምጪልኝ" አላት፡፡ ‹‹ሕያው እግዚአብሔርን እፍኝ ዱቄት አለችኝ ጋግሬያት አንተም እኔም ልጄም (ዮናስ) በልተናት እንሞታለን›› አለችው፡፡ ኤልያስም "የረሀቡ ዘመን እስኪያልፍ ይበርክት" አላት፤ ከቤቷ ብትገባ ዱቄቱ በማድጋው፣ ዘይቱ በማሰሮው መልቶ አገኘች፡፡ ከጥቂት ጊዜም በኋላ ልጇ ዮናስ ታሞ ሞተ፡፡ እናቱም ሄዳ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስን "ሳይገባኝ ከቤቴ ገብተህ ኀጢአቴን ተመራምረህ ልጄን ትገድልብኝ?" አለችው፡፡ ነቢዩ ኤልያስም ወደ አምላኩ ሰባት ጊዜ ጸሎት አድርሶ ዮናስን ከሞተ በኋላ አስነሥቶታል፡፡
ዮናስ ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከነቢያት ጓደኞቹ አብድዩና ኤልሳዕ ጋር ሆነው የታላቁ ነቢይ የኤልያስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ፡፡ /1ነገ.17፥1-24፤ 18፥10-24/ ነቢዩ ኤልያስ ካረገ በኋላ ደግሞ ሁሉም በተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተው እግዚአቤሔርን አገለገሉ፡፡ ነቢዩ ዮናስ አርባ ዓመት ሲሞላው ሀብተ ትንቢት ተሰጥቶት ማስተማር ጀመረ፡፡
የሰማርያውን ንጉሥ ኢዮርብአምን ጠቃሚ ምክር በመለገስ የእሥራኤልን ድንበር ከሔማት እስከ ዐረብ ባሕር ድረስ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ /2ነገሥ. 14፥25/፡፡
ነቢዩ ዮናስ ምንም እንኳን የእስራኤል ነቢይ ቢኾንም ከምድረ እስራኤል ውጪ በነነዌ ስላስተማረ #ነቢየ አሕዛብ ወሕዝብ ይባላል፡፡ የትንቢት መጽሐፉም ዋና መልእክት እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይሆን የአሕዛብም አምላክ እንደሆነና በንስሐ ወደ እርሱ የተመለሱትን ሁሉ በምሕረት እንደሚጐበኝ ማሳየት ነው፡፡
#ዮናስና_ነነዌ_
የነነዌ ሰዎች ኀጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ፤ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ “ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የክፋታቸውም ጩኸት ወደ ፊቴ ወጥቷልና ለእነርሱ ስበክ” አለው፤ ዮናስ ግን የፈጣሪው መሐሪነት፥ ቸርነት መስፈርት እንደሌለው ያውቃልና፤ እርሱ ቢምራቸው ማን ለቃሉና ለትንቢቱ ይገዛል፤ እኔም ሐሰተኛ ነቢይ ልባል አይደለምን? ብሎ አልሔድም አለ፤ እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን ዮናስ የዋሕ ነበረና እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል ብሎ ከፊቱ ለመሰወር ወደ ተርሴስ በመርከብ ኮበለለ፡፡
ዮናስ ወደ መርከብ ገብቶ ጕዞ ከተጀመረ በኋላ በእርሱ ምክንያት ታላቅ ማዕበል ተነሳ፤ በመርከቡ ውስጥ የተሣፈሩትም ሊያልቁ ሆነ፤ ሌሎች እንዲያ እየተናወጡ እርሱ ግን የእምነት ሰው፥ የዋሕና ቅን ስለሆነ ተረጋግቶ በመርከቡ ውስጥ ተኝቶ ነበር፡፡ መርከበኞቹም እጅግ ሲጨንቃቸው እያንዳንዳቸው ወደ አምላካቸው ጮሁ፤ መርከቢቱም እንድትቀልላቸው በውስጧ የነበረውን ዕቃ ሁሉ እያወጡ ወደ ባሕር ጣሉ፡፡ ባሕሩ ጸጥ ሊል ስላልቻለ ዮናስንም ቀስቅሰው “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ፤ ኑ ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ፡፡” /ዮናስ 1፥7/፡፡ እጣ ቢጥሉ በዮናስ ላይ ወጣ፤ ዮናስም በራሱ ተጠያቂነት፤ ‹‹የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ›› አላቸው፡፡ መርከበኞች ግን ዮናስን ለመታደግ የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ፡፡ መርከቢቱ ወደ ምድር ትጠጋላቸው ዘንድ አብዝተው ቀዘፉ፤ የእርሱ ወደ ባሕር መጣል ፈቃደ እግዚአብሔር ስለሆነ ልፋታቸው ሁሉ ከንቱ ሆነ፡፡ ሁሉም አንድ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ “አቤቱ! አንተ እንደ ወደድህ አድርገሃልና ስለዚህ ሰው ነፍስ አታጥፋን፤ ንጹሕ ደምንም አታድርግብን፡፡” በማለት እያዘኑ በሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም ከመናወጥ ጸጥ አለ፡፡
ነቢዩ ወደ ባሕር ቢጣልም የእግዚአብሔር ጥበቃ አልተለየውምና ዮናስን ይውጠው ዘንድ ታላቅ ዓሣ አንበሪን አዘዘለት፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ ዐወቅሁ›› እንዳለ /መዝ. 19፥6/ የመረጠውን ነቢይ ለማዳን ዓሣ አንበሪን አዘጋጀለት፡፡
*ዮናስም በአሣ አንበሪ ሆድና በማዕበል ውስጥ ሆኖ ለ3 ቀናት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ በመጽሐፍ ቅዱስም በዓሣ ሆድ ተጕዞ ያስተማረ፥ ትንቢትም የተናገረ የመጀመሪያ ነቢይ ሆነ፡፡ ዓሣ አንበሪው ዮናስን በሆዱ ቋጥሮ የሦስት ቀን ጎዳና በባሕር ውስጥ ገስግሶ በ3ኛው ቀን ነነዌ ዳር ደረቅ መሬት ላይ አራግፎ ተፋው፡፡ /ዮናስ 1፥4-16፤ 2፥1-11፣ መዝ. 138፥7-10/፡፡
ዮናስ በግዙፉ አሣ አነበሪ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም፥ በጸሎትና በምስጋና ለ3 ቀናት መቆየቱ ለክርስቶስ ትንሣኤ ምሳሌ ነው፤ ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን 3 ሌሊት ኑሮ፥ ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ አዳምና ልጆቹን ለማዳን የመጣው ጌታችንም 3 መዓልትና 3 ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ከሙታን ተለይቶ የመነሣቱ ምሳሌ ነው፡፡ ለዚህም ራሱ ጌታችን በወንጌል ‹‹ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፡፡ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀንና 3 ሌሊት እንደ ነበረ፤ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ 3 ቀንና 3 ሌሊት ይኖራል፡፡ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፡፡ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፡፡ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡›› /ማቴ. 12፥39/
**እግዚአብሔር አምላክም ለሁለተኛ ጊዜ ዮናስን ወደ ነነዌ እንዲሄድ አዘዘው፤ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የነገርሁህንም የመጀመሪያውን ስብከት ስበክላት” አለው፡፡ ዮናስም እንቀድሞው ሳያንገራግር ወደዚህች ከተማ ገብቶ እንዲህ እያለ ‹‹እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዐባይ ሃገር›› (እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች) ንስሐን ሰበከ፥ አስተማረ፡፡
@zemariian