#ExitExam
176 ሺሕ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናን ለመውሰድ መመዝገባቸው ተገለጸ
👉ፈተናው ከጥር 26 እስከ 30 ድረስ ይሰጣል
ጥር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የሚሰጠውን የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች የመውጫ ፈተና ለመውሰድ 176 ሺሕ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፈተናውን በድጋሚ የሚወስዱትን ጨምሮ በጠቅላላው 176 ሺሕ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዬች መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኤባ ሚጀና #ለአሐዱ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ የሚገኙ በሁሉም የኒቨርሲቲዎች ፈተናው የሚሰጥ ሲሆን፤ ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር ያልሆነው የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ጭምር በዚህ ፕሮግራም ተካታች መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የግል ኮሌጆችን በሚመለከት አሐዱ ላቀረበላቸው ጥያቄ ትምህርት ሚኒስቴር የግል ኮሌጆች ላይ ገብቶ ለመፈተን የሚያስችል መዋቅር እንደሌለው በማንሳት፤ ነገር ግን ተማሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የመንግስት ተቋም በኩል መፈተን እንደሚችሉ ገልፀዋል።
የፈተና ቀኑ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይተው ትምህርት የጀመሩትን ዩኒቨርሲቲዎች ታሳቢ ያደረገና በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው ከተረጋገጠ በኋላ መወሰኑን ተናግረዋል።
ፈተናውን ለመስጠት ታቅዶ የነበረው ጥር 14 እና 15 የነበረ ቢሆንም፤ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እኩል ትምህርት ባለመጀመራቸው ወደ ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. እንዲሸጋገር መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዚህ የፈተና ፕሮግራም ተንቀሻቃሽ ስልክና የወረቀት ፅሁፍ ይዞ መገኘት ፈፅሞ #የተከለከለ መሆኑን የገለጹት የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ "ተፈታኞች መታወቂያ መያዝና ከፈተና ፕሮግራሙ 30 ደቂቃ ቀድሞ ቦታው ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡ የወጣው ፈተናም ከተማሩት በመሆኑ ሳይጨነቁ በተረጋጋ መንፈስ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የዘንድሮው የዩኒቨርስቲዎች የመውጫ ፈተና ከዚህ በፊት ይሰጥ እንደነበረው ሙሉ ለሙሉ በኦንላይን የሚካሄድ ሲሆን፤ ከጥር 26 እስከ 30 ከሰኞ እስከ አርብ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
የተማሪዎች ፈተና እንደተጠናቀቀ ቅዳሜ ማለትም የካቲት 1 ቀን የመምህራንን ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ መምህራን ፈተና ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
✅ University News ✅
✅ University News ✅