▪️#ሙሐረም_እና_የዐሹራ_ፆም🔻በሙስሊሞች አቆጣጠር የመጨረሻው ወር ዙልሒጃህ ሲሆን የአዲሱ አመት የመጀመርያ ወር ደግሞ ሙሐረም ይባላል። ሙሐረም ከተከበሩት ኣራቱ ወራቶች ማለትም (ዙልቂዕዳህ ፣ ዙልሒጃህ ፣ ሙሐረም እና ረጀብ) ውስጥ አንዱ ነው። የአሏህ ወርም በመባል ይጠራል። ወሩን መፆምም ተወዳጅ ነው። ከአቡሁረይራ ተይዞ እንደተወራው የአሏህ መልእክተኛ - ﷺ - እንዲህ ይላሉ ፦ [ ከረመዷን ወር በኋላ በላጩ ፆም ፤ የአሏህ ወር የሙሐረም ፆም ነው። ] (ሙስሊም ፥ 1163).
°
🔻የሙሐረም ወር ለየት ከሚያደርገው ውስጥ አንዱ በውስጡ የዐሹራ ቀንን መያዙ ነው። ይህም የዐሹራ ቀን የረመዷን ወር ፆም በሙስሊሞች ላይ ግዴታ ከመደረጉ በፊት በግዴታነት ይፆም ነበር። ይህን የሚያመላክት (ቡኻሪ ፥ 2001) ላይ የተዘገበ ሐዲስ አለ።
°
🔻በሱናነት መልኩ ይህንን ቀን መፆም ተገቢ ነው። ምክንያቱም አሏህ ነብዩሏህ ሙሳ - ዐለይሂሰላምን - እና ህዝቦቹን ከፊርዓውን በደልና ግፍ ያላቀቀበት ቀን ነው። ይህን በማስመልከትም ዐብደሏህ ኢብን ዐባስ - ረዲየሏሁ ዐንሁማ - [ ረሱል - ﷺ - የዐሹራን ቀን ፁመውታል ሰዎችም እንዲፆሙ አዘዋል። ] በማለት ተናግረዋል። (ቡኻሪ ፥ 2004 እና ሙስሊም ፥ 1130)
°
🔻የዐሹራን ቀን መፆም ያለፈውን አንድ አመት ወንጀል(ማለትም ትናንሹን) ያስምራል። የአሏህ መልእክተኛ - ﷺ - ስለዐሹራ ፆም ተጠይቀው እንዲህ ብለዋል ፦ [
የዐሹራን ቀን መፆም አላህ ዘንድ ከዚህ በፊት ያለውን አመት ወንጀል ያስምራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ] (መሰሊም ፥ 1162 ላይ ዘግቦታል). የዐሹራን ቀን መፆም እንጂ #እንደዒድ_አድርጎ_መያዝ ክልክል እና አዲስ መጤ የሆነ ተግባር ነው እና ልንርቀው ይገባል። ቢድዓ ሁሉ ጥሜት ነው።
°
🔻ከአስረኛው ቀን አብሮ 9ኛውንም ቀንም መፆም ተገቢ ነው። ምክንያቱም ረሱል - ﷺ - (ሙስሊም ፥ 1134) በዘገቡት ሐዲስ ላይ [ የሚቀጥለው አመት ብደርስ 9ኛውንም ቀን ፆመዋለው። ] ስላሉ ማለት ነው። በዚህም ምክንያት ከአይሁዶች ጋር መቃረን ይገኝበታል።
°
🔻ዘጠነኛውን ቀን መፆም ካልቻሉ 10ኛውን እና 11ኛውንም ቀን መፆም እንደሚቻል ዑለማዎች ተናግረዋል። ማስረጃቸውም ተከታዩ ሐዲስ ነው ፦ [ የዐሹራን ቀን ፁሙ የሁዳዎችንም ተቃረኑ ፤ ከሱ በፊት ያለውን ቀን ፁሙ ወይም ከሱ በኋላ ያለውን ቀን ፁሙ። ] (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ ፥ 2154 ላይ ተዘግቧል / አሕመድ ሻኪር ሐሰን ብለውታል).
°
🔻በመሆኑም የዐሹራ ፆም ደረጃዎች ጠቅለል ሲደረጉ እንደሚከተለው ይሆናል ፦
1ኛ ደረጃ ፡ 9ነኛው እና 10ኛውን ቀን መፆም
2ኛ ደረጃ ፡ 10ኛው እና 11ኛውን ቀን መፆም
3ኛ ደረጃ ፡ 10ኛውን የዐሹራን ቀን ብቻ መፆም ነው ፤ በእርግጥ አንዳንድ ዑለማዎች 10ኛውን ቀን ብቻ መፆምን ጠልተውታል ምክንያቱም ነብዩ - ﷺ - አይሁዶችን በመቃረን ስላዘዙ ይላሉ ሌሎች ደግሞ ችግር የለውም ብለዋል።
°
🔻እነዚህን ሶስት ደረጃዎች ሸይኽ ኢብኑ ዑሰይሚን (ሸርሕ ሪያዱሷሊሒን ፥ 3/463) ላይ አስቀምጠውታል። ❶. ኢብኑልቀይዪም (ዛዱል መዓድ ፥ 2/75) ላይ ደግሞ 9 ፣ 10 እና 11ኛውን ሶስቱንም ቀን መፆም የመጀመሪያ ደረጃ ነው በማለት ተናግረዋል። ሌሎቹ ደግሞ ኢብኑልቀይም ይህን ያሉት ደከም ያለ ሐዲስ ላይ ተንተርሰው ነውና በላጩ ደረጃ 9ኝ እና 10ኛውን ቀን መፆም ነው ብለዋል። ወሏሁ አዕለም።
°
🔻ሌላው የሚነሳው ነጥብ #ቀዷእ_ያለበት_ሰው የዐሹራን ፆም መፆም ቢፆም አጅሩን ያገኛል ወይስ አያገኝም የሚለው ነው። እዚህ ላይ አንዳንድ ዑለማዎች የቀዷእ ፆም ግዴታ ስለሆነ ለብቻው መፆም አለበት ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ አብሮ ነይቶ ቢፆምም በአሏህ ፍቃድ የሁለቱንም አጅር ያገኛል የሚሉ አሉ።
°
🔻ሸይኽ ኢብኑ ዑሰይሚን (ፈታዋ-ሲያም ፥ 438) ላይ የሚከተለውን ብለዋል ፦ |" የረመዷን ቀዷእ እያለበት የዐረፋን ወይም የዐሹራን ቀን ፆም ቢፆም ፆሙ ትክክል ነው ፤ ነገር ግን ይህን ቀን ለቀዷኡም አብሮ ቢነይት የሁለቱንም አጅር ያገኛል። "|. ሸይኽ ኢብንባዝም በተመሳሳይ በአሏህ ፍቃድ የሁለቱንም ምንዳ ያገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን በማለት ተናግረዋል።
ንግግራቸውን በዚህ ሊንክ ማዳመት ትችላላችሁ ፦ bit.ly/2YkwxpA
የቀዷእ ፆማችንን ቶሎ በማውጣት ላይ ልንተጋ ይገባናል።
°
🔻#በተጨማሪም በየወሩ ሶስት ቀን መፆም ያስለመደ ሰው 9ነኛው 10ኛውን እና 11ኛውን ቀን ለሁለቱም ነይቶ ቢፆም የዐሹራውንም እና በየወሩ ሶስት ቀን የመፆምን የሁለቱንም አጅር ያገኛል። ምክንያቱም በየወሩ ሶስት ቀን መፆም ግዴታ "#አያመል-#ቢድ" ላይ ብቻ አይገደብም። ማስረጃውም (ሙስሊም ፥ 1160) በተዘገበ ሐዲስ ላይ ነብዩ - ﷺ - ከየወሩ ሶስት ቀን እንደሚፆሙና ቀናቶችን በተመለከተ ደግሞ መጀመሪያም ላይ ይሁን መካከለኛም ላይ ይሁን መጨረሻ ቀናቶች ላይ እንደተመቻቸው ይፆሙ እንደነበረ ተገልጿልና ነው።
°
🔻9ነኛውን እና 10ኛውን ቀን ፁሞ በተጨማሪም "አያመል-ቢድ" የተባሉት 13 ፣ 14 እና 15 ቀናቶችን ቢፆም ደግሞ በአሏህ ፍቃድ ምንዳው የበለጠ ይሆናል። ምክንያቱም 1ኛ. አያመል-ቢድን መፆም ለብቻው ትሩፋት እንዳለው በተለያዩ ሐዲሶች ላይ መዘገቡ 2ኛ ደግሞ ወሩ ሙሐረም በሙሆኑ ከላይ ባሳለፍነው ሐዲስ መሰረት ፆም ማብዛት ተወዳጅ ስለሆነ ነው።
°
🔻#በመጨረሻም የዐሹራ ቀን ከቅዳሜ ቀን ጋር ከተገጣጠመ ቅዳሜን መፆምን የሚከለክል ሐዲስ ስላለ እንዴት እናድርግ? የሚለው ላይ ሸይኽ ኢብኑዑሰይሚን (መጅሙዓል ፈታዋ ወረሳኢል ፥ 20/57) ላይ የዐረፋ የዓሹራ እና መሰል ፆሞች የቅዳሜን ቀን ቢገጥሙ መፆም ችግር የለውም ምክንያቱም አንድ ሰው እነዚህን ቀናቶች የሚፆመው መፆማቸው የተደነገጉ ፆሞች ስለሆኑ ነው በማለት አስቀምጠዋል። የዐሹራ ቀን የጁሙዓ ቀንን ቢገጥምም ተመሳሳይ ብይን እንደሚሰጠው ዑለማዎች ተናግረዋል።
°
🔻ስለዚህም ወንድሞቼ እና እህቶቼ አሏሁ ተዓላ ለኛ የሚፈጥርልን የኸይር አጋጣሚዎች ችላ በማለት ልናሳልፍ አይገባንም። ራሳችንም ፁመን ሰዎችንም ማነሳሳት ይጠበቅብናል። ወሏሁ አዕለም.
_❶.ሸይኽ ኢብኑ ዑሰይሚን በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ የመጀመሪያው ደረጃ 3ቱንም ቀን መፆም ነው በማለት የኢብኑልቀይዪምን ንግግር የሚያጠናክር አባባል አላቸው። ያሉበትን ንግግር ለመስማት ፦
https://youtu.be/HGouMgc7oLg_✍️ አቡልዓባስ አሕመድ ኢብን የሕያ @ Ibn Yahya Ahmed.
📆ሐሙስ ሙሐረም 1/1442ሂ. # ነኀሴ 14/ 2012 # Aug 20/2020.
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
📣ጆይን ያድርጉ፦
https://telegram.me/ibnyahya777✅ላይክ ያድርጉ፦ https://m.facebook.com/ibnyahya7777