መዝሙር፡6
ለመዘምራን፡አለቃ፡በበገናዎች፡ስለ፡ስምንተኛ፤የዳዊት፡መዝሙር።
1፤አቤቱ፥በቍጣኽ፡አትቅሠፈኝ፥በመዓትኽም፡አትገሥጸኝ።
2፤ድውይ፡ነኝና፡አቤቱ፥ማረኝ፤ዐጥንቶቼ፡ታውከዋልና፥ፈውሰኝ።
3፤ነፍሴም፡እጅግ፡ታወከች፤አንተም፡አቤቱ፥እስከ፡መቼ፡ድረስ፡ነው፧
4፤አቤቱ፥ተመለስ፡ነፍሴንም፡አድናት፥ስለ፡ቸርነትኽም፡አድነኝ።
5፤በሞት፡የሚያስብኽ፡የለምና፥በሲኦልም፡የሚያመሰግንኽ፡ማን፡ነው፧
6፤በጭንቀቴ፡ደክሜያለኹ፤ሌሊቱን፡ዅሉ፡ዐልጋዬን፡ዐጥባለኹ፥በዕንባዬም፡መኝታዬን፡አርሳለኹ።
7፤ዐይኔ፡ከቍጡ፡ዕንባ፡የተነሣ፡ታወከች፤ከጠላቶቼ፡ዅሉ፡የተነሣ፡አረጀኹ።
8፤ዐመፃን፡የምታደርጉ፡ዅሉ፥ከእኔ፡ራቁ፥እግዚአብሔር፡የልቅሶዬን፡ቃል፡ሰምቷልና።
9፤እግዚአብሔር፡ልመናዬን፡ሰማኝ፤እግዚአብሔር፡ጸሎቴን፡ተቀበለ።
10፤ጠላቶቼ፡ዅሉ፡ይፈሩ፡እጅግም፡ይጐስቍሉ፤ወደ፡ዃላቸው፡ይመለሱ፥በፍጥነትም፡ይፈሩ።
@delikamedia@sebat_kutr