የሐበሻ የጦርነት ጥበብ
THE ART OF WAR የተሰኘው እድሜ ጠገብ መፅሀፉ ከክርስቶስ ልደት በፊት ተፅፎ ከክርስቶስ ልደት በኋላም ላሉ ጦርነቶች መራሄ ሆኗል። በርግጥ መፅሀፉ ከጦርነት አልፎ ለበርካታ የቴክኖሎጂ
ካምፓኒዎችም መነሳትና መመንደግ አገልግሏል።
'ሳን ዙ በመፅሀፉ ያነሳቸው በርካታ ምክሮች የድል መንገድ ናቸው' እያሉ መመሪያውን የተጠቀሙ የጦር አበጋዞችም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ለብዙዎቹ የጦር አዛዦች መፅሀፉ ከሼልፋቸው ይልቅ
ለጠረንጴዛቸው ቅርብ ነው።
እኔ ግን እላችኋለሁ በእኛ በሀበሾች ሽለላ፣ ቀረርቶና ፉከራ (war song) ውስጥ ያሉ መልእክቶች ሳን ዙ ከፃፋቸው ሀሳቦች ጋር
አቻ ይሆናሉ።ስነቃሎቻችንን ስላልተረዳናቸ፤ ተረድተንም ስላልተነተናቸው ተንትነንም የሼልፍ ሸክም ከማድረግ ስላላሳለፍናቸው እንጂ ሀገር በቀል የጦርነት ጥበብ በነበረን፤ ለዚህኛው ትውልድም የነአድዋ
ድል ምክንያት ጭላንጭል በተገለጠልን ነበር።
ለአብነቱ ያህል ጥቂት የሳንዙን የጦርነት መርሆችን ከኛ ቃል ግጥሞች ጋር እያነፃፀርን እንይ፦
"ደረሰባቸው ሳይታጠቁ
እንደዝንጀሮ ፀሀይ ሲሞቁ፤"
ጠላት በተዘናጋበትና ባላሰበበት ቅፅበት ደርሶ የጠላትን ሰራዊት ሙትና ቁስለኛ ማድረግ የወገንን ጦር ኪሳራ ይቀንሳል። ድልንም አፍጥኖ ያስሞግሳል። በዚች የቃል ግጥም ውስጥ ጠላትህ እንደማትደርስበት አስቦ አንዴ ደረቱን አንዴ መቀመጫውን
እያገላበጠ ለፀሀይ በሰጠበት ጊዜ ደርሰህ አበራየው የሚል ምክርም አለ።
ሳን ዙም በምክሩ እንዲህ ይላል "...ጠላትህ ባልተዘጋጀበት ጊዜ
ውጋው..." (በርግጥአንድን ጠላት ታጥቂያለሁ ታጠቅ ሳይሉ መውጋት
በሀበሻ ልማድ ነውር ነው። ግን ታጥቂያለሁ ታጠቅ ከተባለ በኋላና ጦር ከተሳለ ጋሻ ከተራገፈ በኋላ እንዲያ ብሎ ነገር የለም)
ሳን ዙ በሌላ ምክሩ "...እሩቅ ሆነህ ሳለ ቅርብ፤ ቅርብ ሆነህ ሳለ እሩቅ ምሰል..." ይላል። የኛዎቹ ጦረኞችም ደጋ ሲባሉ ቆላ ቆላ ሲባሉ ደጋ ይገኙና ነው ድል የሚቀዳጁት።ለዚህ አይነቱ ሰው ደግም የመወድስ ፉከራ አለው።
"ቆላ ነው ሲሉት ደጋ እሚገለጥ፤
ጥላው ለጠላት የማይጨበጥ።"
የጦር ጠበብቱ ሳን ዙ ".... ስታጠቃ እንደመብረቅ ፍጠን..."
ይላል። ግሩም ምክር ናት። እሱም እንደሚለው በተለይ የጠላት ሀይል ብዙ ያንተ ደግም ትንሽ ከሆነ በብዙ አቅጣጫ በፍጥነት ማጥቃት ይመከራል። ይቺን ሀሳብ ሀበሻው በሁለት መስመር ግጥም እንዲህ ይገልፃታል።
"እነሱ ብዙ ማለት ምንድነው
ፈጥነን እንሂድ ድሉ የኛ ነው፤"
ሀበሻ ሲፈልገው ይቺንው ግጥም ቤት መድፊያ ስንኟን ብቻ"...እንግጠማቸው ድሉ የግዜር ነው..." ብሎ ይቀይርና በፈጣሪ መተማመኑንም ይነግርሀል።(ተለዋዋጭነት የስነቃል አንዱ ባህሪ መሆኑን ልብ ይሏል) በዚህ ብቻ አይበቃውም ሀበሻው
"የሌሊት አውሬ የቀን ጃውሳ
ጠዋት የሚያደርስ ያሞራ ምሳ"
ይልና ምሳን በቁርስ ሰአት የሚያደርስ ፈጣን ሁን ይልሀል።በዚችው ግጥሙ ቀንና ማታ የተለያየ አይነት ባህሪ ይኑርህ ብሎ "..በጦርነት ውስጥ አንድ አይነት አፈፃፀም የለም፤ እንደ ሁኔታው ይለዋወጣል።" የሚለውን የሳን ዙን የጦር መርህም ደርቦ
ይገልጣል።
"...ዛሬ ነገ እያልክ እድልህን አታባክን ..." ይላል ጠቢቡ ሰውዬ።እርግጥ ነው ዛሬ ነገ ማለት ውስጥ ላጥቃ አላጥቃ የሚል መወላወል አለና በዛ መሀል የልብ መፍረክረክ ይመጣል። ያ ብቻም ሳይሆን ጠላትም ጊዜ እንዲሸምትና እንዲደራጅ ወይም እንዲሸሽ ይረዳዋል። ለዛ ነው ሳን ዛሬ ነገ አትበል የማለው። ዛሬ ነገ ሲል ጠላቱ ያመለጠው ሀበሻስ ቁጭቱን እየገለጠ በተራዛማውም ሌላውን ሲመክር እንዲህ አይደል የሸለለው
"ያረባ ወንድ ልጅ እየወላወለ
ሰደደው ጠላቱን ዛሬ ነገ እያለ"
ጠቢቡ "ጠንካራ ሆነህ ሳለ ደካማ፤ ደካማ ሆነህ ሳለ ጠንካራ ምሰል" እያለ ይመክራል። ደካማ በሆንክበት ጊዜ ጠንካራ መስለህ ካልታየኸው በቀላሉ ትጠቃለህ። ጠንካራ በሆንክ ጊዜ ደግም ደካማ መስለሀው የመጣ ጠላትን በውስጡ ያሳደረው ንቀት አግዞህ ብዙ መሰዋት ሳትከፍል ካፈር ትቀላቅለዋለህ።
ይቺንው ሀሳብ ሀበሻ በቀረርቶው እንዲህ ብሎ የገልጣታል።
"አጭር ናቸው ብለው በኛ ላይ መጡብን
ቀጭን ናቸው ብለው በኛ ላይ መጡብን
መች አወቁንና አመል እንዳለብን"
"ጠላትህ ንዴት ካለበት ተንኩሰው፤ ከተረጋጋም እረፍት አትስጠው"
ይላል ሳን።
"ነካካየው ነካካቸው አትስጣቸው ጤና
ምንጊዜም ደህና ሰው አልተባልክምና"
ይላል ደግሞ ያገራችን ሸላይ።
©ታምሩ ከፍያለው
@ethel2011@truth00011 ታገኙኛላችሁ