ሳሙኤል አለሙ-Samuel alemu


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: not specified


ሌላ መገኛዬ...
facebook.com/samialemu

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
not specified
Statistics
Posts filter


እንባሽን ቋጥሬ
ጌጣጌጥሽን አንጥሬ
ካይኖችሽ ብርሐን አቅርሬ
ቀስተ ደመና መኃል ተንጋልዬ
እንደ ጎበዝ
ስቄ ተንፈራፍሬ
አልቀር ተቀብሬ!

[ሰለሞን ደሬሳ]



Enjoy your ሰንበት❤️
@Samuelalemuu


እንበልና...
በጨዋታሽ
መዳፍሽ የዋለች
ጎልያድን የጣለች
አንድ ጠጠር አለች

እንበልና...
ይች ጠጠር
አፍ አውጥታ ብትናገር
ትልቁ ታሪኳ ባጀብ የሚያስመካት
ጎልያድን መጣል ነው እጆችሸን መንካት?

[ HEnock Bekele ]


@Samuelalemuu


|
መልክሽ ላይ....
ፊትሽ ላይ......
በተጣለ ድንኳን....
(በተቀለሰ ዳስ...)
ሳቅ የሚታደመው ---- ደስታ ተደግሶ፤
ና ብለን ሳንጠራው--- ለምን መጣ ለቅሶ?!
|
ለምን ታለቅሺያለሽ?
(እየሳቅሽ አልነበር!?)
ደስ ብሎሻል አይደል....?
(ሆድሽም ጥርስሽም--- ሳቅ ነው ያረገዘው)
ለምን እንባሽ መጣ--- ልብሽ ሳይጋብዘው?!
|
አየሽው ዓለሜ....?
እንባሽ ቀላዋጭ ነው....
(ድንኳን ሰባሪ ነው....)
ሳይጠሩት ይመጣል፣
(በደስታሽ ወንበር ላይ....)
ከሳቅሽ አጠገብ ---አብሮ ይቀመጣል።
|
እየሳቅሽ አልነበር....?!
እየሳቅሽ አልነበር....?!
(እንባሽ ከየት መጣ?)
በሳቅሽ መካከል -- ለምን ታለቅሺያለሽ?
(ምናልባት ማን ያውቃል...)
ደስታሽ የከለለው --- ድብቅ ሀዘን አለሽ....

[ በቃሉ ሹምዬ ]


@Samuelalemuu


------------
የአንዲትን ሴት ዕድሜ
ወንድ ተሸክሞት
ወደ የትም ሄዶ ፣ ሲመለስ ወደ አንቺ ፣
ለምን መጣ ብለሽ
ለምን ሄደ ብለሽ ፣ ተይ አትመልከቺ ፣
.
ከብዙ ትዝታ
አንዷን አንጓ መርጠሽ

ብቻሽን መብሰልሰል
ብቻሽን መተከዝ
ብቻሽን መከፋት ፣
መሄድ ያረጠበው
ሽራፊ ሳቅ መልቀም ፣ ዘለላ እንባ መድፋት ፣

ተይው እባክሽን
.
የቆመሽበት አንጓ
ትዝታ እንዳቀፈ
ያለፈ ሕይወትሽ ፣ ከዛሬ ታሪክሽ እንደተኳረፈ ፣
.
አንድ ዘፈን መርጠሽ
የአንዱን አንገት አንቀሽ ፣
ምን እንደሚጠላ
ምን እንደሚያፈቅር ፣ ሁሉንም ጠይቀሽ ፣
.
አብረሽው እደሪ
ትናንት አለ ላንቺ ዛሬን ተበደሪ ።

ያለፈውን እርሽው
በአሁን ሳቅ ተርኩሽው

' ቅድም እንጃለቱ '
' ትላንት እንጃለቱ '
' ነገም እንጃለቱ '
.
ተስፋ አለኝ አትበይኝ
ሰው አለኝ አትበይኝ
ሁሉን እቅፍ ልመጅ ፣ ሁሉን እቅፍ ናቂ ፣
ከመጣው ተስማሚ ፣ ከሄደው ራቂ ፣
.
ከዛ ተመልከችው
ተመልከች ዓለሙን
ተመልከች ደመና
.
ሁሉን እርግፍ አርገሽ
የሃዘንሽን ክፍተት ፣ በአሁን ደስታ መርገሽ ፣

ባለፈ ዘላለም ሳታቀረቅሪ
ወደ ትናንት ሳትሄጅ ከነገ ሳትቀሪ

ፀሃይን ተመልከች
ተመልከች ሰማዮን
.
ብርሃን እንዳ'ይሰጥ ፣ እንደሸፈነው ጉም ፣
ምን አልባት ከገባሽ
አሁን ብቻ መኖር ፣ የሚሰጠው ትርጉም ።

[ ሶሎሞን ሽፈራው ]


@Samuelalemuu


… ጊዜ ይፍታሽ ብለህ…
ዕድሜ ይፍታሽ ብለህ…
ስትሰናበተኝ ተሰናበትኳቸው ፣ ምግባሮቼን ሁሉ
ፍቅር የ‘ግዚአብሔር ነው፤
በጣም ማፍቀር ደግሞ ፣ የሰይጣን ተንኮሉ!

                          [ መዘክር ግርማ ]

@Samuelalemuu


ባንተ ስም ተጠራሁ
በድፍረትህ ኮራሁ
ግን ልትለየኝ ነው
ብቻዬን ነኝ ፈራሁ ።

ለካ እንዲህ ብርቅ ነው
የአንድ ለሊት እንቅልፍ
ለካ እንዲህ ይሞቃል
የክንዶችህ እቅፍ
አይ የጦርነት ግፍ !

ምን ላ'ገር ቢዘምቱ ፤ ጠላትን ቢመቱ
ለሰንደቅ አላማ በክብር ቢሞቱ
ነገር ሁሉ ከንቱ !
የልብ አያደርስም
የአፍቃሪን ጥያቄ ፥ ጦር ሜዳ አይመልስም ።

መቼስ ልትሄድ ነው
ዝመት የአባትህ ነው
ኢትዮጲያዊ ሆነህ የተለመደ ነው
ግን "እንጋባለን" ብለሀል ለግንቦት
ነገርኩህ ! እንዳትሞት !


ሐብታሙ ሃደራ


@Samuelalemuu


እንደምትወዳት ንገራት,

(በእውቀቱ ስዩም)
ሕይወት የብድር በሬ፥መቼ ሁሌ ይጠመዳል
ለጊዜው ብቻ የመጣ፥ ጊዜው ሲደርስ ይሄዳል
የተሰጠህ ጸጋ ሁሉ፥ ደሞ ካንተ ይወሰዳል::

ቀለበት፥ አምባር አይደሉም
እጅህ ላይ ሁልጊዜ የሉም
-ቀናት ሳምንታት ወራት
ዛሬውኑ ፥አሁኑኑ፥ እንደምትወዳት ንገራት::

አበቦች ሁሉ ሳይረግፉ
ምኡዝ ሽታዎች ሳይጠፉ
ያጸድ በሮች ሳይቆለፉ
በንቦች ጎዳና ላይ፥ተርቦች ሳይሰለፉ
በንፋስ ክንፍ ሳይመታ
ሕይወት የላምባ መብራት
አሁንኑ ዛሬውኑ ፥እንደምትወዳት ንገራት፤

ርቃ ሳትገሰግስ
ገና ስንቋን ስትደግስ
እንዲሁ እንዳማረባት
ቀልብህ እንደቀረባት
መቃብር በመዳፉ
እንደጠጠር ሳይቀልባት
አፈሩን ሳትዛመድ
ወደማትቀባው አመድ
ወደማትስበው አየር
ሳትቀየር
አንትም አንደበት ሳለህ፥ እሷም ጆሮ ሳያጥራት
ዛሬውኑ! አሁኑኑ! እንደምትወዳት ንገራት።

@Samuelalemuu


"ክንፋም_ከዋክብት" በሚለው ከ50 ገጣሚያን ጋ በቅርብ ቀን የታተመው የግጥም መድብሌ ቀሪ መፅሃፍት እጄ ላይ ስላሉ መግዛት የምትፈልጉት:-
@samuelalemu5
ልታወሩኝ ትችላላቹ! አመሰግናለሁ🙏


@Samuelalemuu


የነካካችኝን
ያስነካካችኝን
'ካንድ ከ'ሷ በቀር ሌላ ሰው ማን ያውቃል
ዕድሜ ካነደደው
ከሴት ገላ በልጦ ፎቶዋ ይሞቃል

ይሞቃል
ይደንቃል
ምስሏ ጎኔ ሲያድር
ልቤን እንደ ክብሪት
እሳት ትላንት አዝሎ እየተረኮሰው
እጅ አለው ፍሬሙ ያቅፈኛል እንደሰው

እጅ አለው ፍሬሙ
መነካካት ያውቃል
አይዞህ ማለት ያውቃል
በተለመደ አይነት ሲያዩት መመልከቱን
ብቻ አይናገርም የሄደችበቱን

መኖር ጉደ ብዙ
ደብር እንዳጣ ካህን
ዜማ እና ውዳሴ እንዳንሰፈሰፈው
እንደከዱት ወዳጅ
''ይሁን ይሁን'' ብሎ ሁሉን እንደሚያልፈው

እያብሰለሰለኝ
እያመናተለኝ
ሰው ለምዶ ሰው ማጣት
በቀን እዬቀጣኝ እዬናደው ቤቴን
ናፍቆት እሳት ሆኖ በላው ሰውነቴን

ከተራራው ማዶ
ሌላ አለ ተራራ
ዘመድ እዬሰራ
ወዳጅ እያፈራ
መልዕክት ይላላካል በንፋስ ደብዳቤ
ወቅት እዬጠበቀ
ሰማይ ይታጠናል በምድር እጣን ከርቤ

የሰማይ አሞራ
ምን ሲበር ቢውል
አያድርም ሌላ አገር
መንገድ ቀናኝ ብሎ አይከርምም በቆዬው
ወዳጅ ትቷል'ና
እመጣለሁ ብሎ ስሞ የተለዬው

ይሄን ሁሉ ምስጢር
አታውቅም አልልም ምንድነው ትርጉሙ
ብቻ ግን ብች ግን
ይቀናታል መሰል
ቀን ሃሳብ አርግዞ በሌት መታመሙ

''እከሳለሁ እንጂ እመነምናለሁ
ፍቅር ማንን ገሎ እሞትልሻለሁ''

እንደሚሉት አይነት
አልሞትኩም አልልም
አለሁም አልልም
እንደቆዬ ህመም እን'ዳደረ ግርሻ
ጠርዝ ላይ ሲቀጥሩት
ከመሃል መቅረት ነው ያፍቃሪ ሰው ድርሻ ።

#Amare_zewdu

@Samuelalemuu


ሳይኮሎጂስቶች እንደሚሉት ሐዘን (grief ) አምስት ደረጃዎች አሉት ። የመጀመሪያው ደረጃ denial ይባላል ። የተፈጠረውን ነገር አልተፈጠረም ብለን የምንክድበት ደረጃ ነው ። ሁለተኛው ደረጃ anger ይባላል ።  "ለምን ? ምን በደልኩ ?" እያልን የምንተክዝበት እና ከመሬት ተነስተን በሁሉም ነገር የምንነጫነጭበት ደረጃ ነው ። ሶስተኛው ደረጃ bargaining ይባላል ። እስከዛሬ ከሸሸነው ነገር ጋር ፊትለፊት የምንጋፈጥበት ደረጃ ነው ። አራተኛው ደረጃ depression ይባላል ። የተፈጠረውን ነገር አምነን የምናዝንበትና የምናለቅስበት ደረጃ ነው ። አምስተኛውና የመጨረሻው ደረጃ Acceptance ይባላል ። እዚህኛው ደረጃ ላይ ሐዘኑን ሙሉ ለሙሉ ተቀብለን እና "ለበጎ ነው" በማለት ተጽናንተን ወደፊት የምንጓዝበት ደረጃ ነው ።

ብቻ ምን ልል ነው እነዚህን ደረጃዎች ሳይኮሎጂስቱና ባለቅኔው በውቀቱ ስዩም በሚያምር አማርኛና አገላለጽ በውስን መስመር እንዴት እንደገለጻቸው ተመልከቱ ለማለት ነው

አዎ !
ለጊዜውም ቢሆን ፤ ግፍ ያደነዝዛል (denial)
በደል ያስተክዛል (anger)
ጊዜም ጠብን ሽሮ ፤ ወደፊት ይጓዛል
በልብ ሰሌዳ ላይ ፤ ቂም ይደበዝዛል (bargaining )
በነገ ያመነ
ልጁን ቀብሮ መጥቶ ፤ ሚስቱን ያስረግዛል ። (depression & acceptance)

Cc habtamu hadra


@Samuelalemuu


ጉባዔ ዳር የበራች ጧፍ ፣
ወይን አምባ ላይ የታሰረች
ባለ ድባብ የወሎ ሰው ፣
የጌታ ልጅ የነበረች

ዝናብ መሃል ምጠልቅ ጸሃይ ፣
የሴት ልቧን እያባባት
በ'ጇቿ አፈር እየጫረች ፣
ጭንቅ ሃሳቧ እንዲቀላት

እጥፍ ኩርምት ፣ ካለችበት
ነበር ገጥሟት ፣ እንደዘበት
አፈር በ እጇ ፣ እየጫረች

[ ይህን አለች ... ]

« ከእጆቼ የተወው ቁስል ፣ አልነበረም
ለጎኔም ክፍተት ፣ አላስቀረም
ያዘነልኝ አባት ፣ ፈውሶኛል
ስለዚህ...
ነበር ማለት ተስኖኛል ።

የእጄን ቁስል መልስልኝ
ለጎኔም ሽንቁር አበጅልኝ

መበርታቴን ላሳይበት
ጠባሳዬን አትከልክለኝ ፤
ቀን ወጣልኝ እንድልበት

እፎይ ብለው ፣ እንዳረፉ
ጭንቅን ጥለው ፣ እንዳለፉ
ለጠባሳም ይደከማል
[ ለምን ? ]
ማሸነፍን አለመንገር ፣
ከመሸነፍ እኩል ያማል »

[ ይህች ነፍስ ... ]

ወይን አምባ ላይ የታሰረች
የጌታ ልጅ የነበረች
ወሎዬዋ ቅን አምሰልሳይ
ዝናብ መሃል ጀምበር መሳይ

እጥፍ ኩርምት ካለችበት
የመጣችው መንገድ ደክሟት
በ'ጇ አፈር ስትጭርበት

የሴት ልቧን ቢያባባትም
እትም ቁስል ባይኖራትም
ብዙ አልፋለች እንደዘበት ።

[ ቶማስ ትዕግስቱ ]

@Samuelalemuu


እሺ ግን ጥላኝ ብትበርስ ?



[ Habtamu hadera ]

@Samuelalemuu


በመኖር አጸድ ውስጥ
(በእውቀቱ ስዩም)

ጊዜ ከሰው መሀል- መርጦ ሲያቀማጥል
ማጣት አለ ደሞ፥
የወለዱትን ልጅ፥ ጉድፍ ላይ የሚያስጥል
በተፈሰከ ቀን፥ ጾምን የሚያስቀጥል::

እድልና ትግል በሚጫወቱበት
በደልዳላው ስፍራ
አለቃና ጭፍራ-
-ቃል ሲለዋወጡ፥ ውልና መሀላ
“አብረን እናድጋለን” ቢባል ለይስሙላ
ወንዙን ሳያጎድል ፥ሐይቁ መች ሊሞላ፤

ጸሐይ ብትወጣ
ፍጥረት በጠቅላላው ጸጋዋን ቢቀበል
የደመናም ጠበል፥
ለሁሉ ቢደርስም
አንደኛው አያድግም፥ አንዱን ሳያከስም::


@Samuelalemuu


በቀን እንደሞትኩ...
(ሳሙኤል አለሙ)

ካፈሩ ላይ አፈሩን አራግፈነው
ከሰማዩቱ ሰማያቱን አልፈነው
ሄድን ሄድንና...
ከፈጣሪ የፍርድ መንበሩ ጋር ደረስን፤
ተረኛ ነበርና...
ደጃፉ ላይ ወንበር ስበን ተቀመጥን።
ተረኛ እስኪጠራ ፥ እስኪገባ ፈጣሪው ጋ
ትዝ ይለኛል ፥ ባንዲት ርዕስ ስናወጋ።

ሞትኩኝ...
የሚላስ የሚቀመስ አጥቼ
ሞትኩኝ...
"ትን" ብሎኝ ብፌ አሰናድቼ
ሞትኩኝ...
አልጋ ላይ ላመታት እንዳልነበርኩ ማቅቄ
ሞትኩኝ...
ስዝናና ውዬ ስመለስ ደክሞኝ መሪ ለቅቄ
ሞትኩኝ...
በተኛኹበት ወዳጄ ባልኩት በሰው ታንቄ
ሞትኩኝ...
ሞትኩኝ ሲሉ ፥ ኹሉ ኹሉም በየተራው
በቀኑ እንደሞተ ፥ ኹሉ ሰው ሚያወራው።

እኔ ግን...
እኔ ግን...
በቅጡ መኖሬን
በቅጡ መሞቴን ስላላወኩ
በቀኔ ሳይሆን በቀን እንደ ሞትኩ
አስታውሼ ነበር ፥ የተናገርኩ!

@Samuelalemuu


እፈራለሁ
[ ]

ቆይ፥
መንፈስ ብትሆኚስ?
ለእኔ ብቻ የሚታይ ፥ ከህልም የተሰራ፥
'ዴልዩዥን' ብትሆኚስ?
የምኞት መዶሻ ፥ ጠራርቦ ያቆመሽ ፥ የልቤ ፈጠራ፤

ከጨዋታ መሐል ፥ ድንገት ብትጠፊብኝ፤
'የታለች?' ስላቸው፥
'ማን ናት ደሞ?' ብለው ፥ ሰዎች ቢስቁብኝ፤

ህልም ብትሆኚስ?
ስነቃ ብትቀሪስ?
ቆይ አሁን፥
ጭራሹን ባትኖሪስ?

ሞልተሽኝ በእቅፌ፥
እጆቼን ቀንፌ፥
ደስታዬ እንደድመት ፥ ልቤን እየላሰው፥
ሳቅ ሆዴን ሲያምሰው፥
ባዶዬን ቢሆንስ፥
ብቻዬን እንደእብድ ፥ የምታየው ለሰው?
እንደንፋስ ነክቶኝ ፥ ሲያልፍ ሰቀቀኔ፥
ከተዳከምሁበት ፥ ከውብ ሰመመኔ፥
'ቢሆንስ?' እያልሁኝ፥
ድንገት እየባነንሁ ፥ እፈራለሁ እኔ፥

መቼም፥
ነፍሱን መርጦ አጥቦ ፥ ውድ አካል ቢያለብሰው፥
ምን ያህል ቢወደድ ፥ ፍቅር ቢያንተርሰው፥
እንዲህ ሁሉ አምሮለት፥
በስጋና በደም ፥ አይገለጥም ሰው።

#ሚካኤል_ምናሴ

@Samuelalemuu


የወደድሽኝ
የማትሸሺኝ
"ሀብ ይሙት" ካልሽ የማትዋሺኝ
ይመስለኝ ነበር እኮ...

የህይወት ትርጉም የገባሽ
ፍቅርን ከኑሮ ያግባባሽ
በእምነት ፥ በስክነት የሰባሽ
ይመስለኝ ነበር እኮ ...

እግዜር ከእንከን ያጠለለሽ
ከክፋት አይን የከለለሽ
እንኳን የራስሽ እግር ፥ የራስሽ መንገድ ያለሽ
ይመስለኝ ነበር እኮ ...

ለካ ሰው ነሽ
ለካ ሴት ነሽ
ልቤ ነበር ያገዘፈሽ
ላባ ገጥሞ ያከነፈሽ

ለካ ሰው ነሽ ... ያውም ተራ
ምስኪን አይቶ የማይራራ
በድን ገድለሽ የምትፎክሪ
በነውርሽ የምታቅራሪ
ፈሪ !

ለካ ሰው ነሽ ...
አለሁ ብለሽ የምትሄጂ
ቃል ሳይከብድሽ የምትከጂ
ነፍስሽን በልተሽ ጨርሰሽ
ዖና ስጋሽን የምትጎትቺ !

ለካ ሰው ነሽ ... እንደ ማንም
ሲገርም !

By Habtamu Hadera

@Samuelalemuu


ጥለሽኝ ስቴጂ
ጩአት እሪታዬን እንደምን ላምቀው?
አስጩኦ አይደለም ወይ?
ሰይጣን የሚለቀው?

#Rediet aseffa

@Samuelalemuu


ሲኖር የሚገርመኝ
አይደለም እንደ ሟች
ይሄ ሁሉ ተጓዥ ፣ ይሄ ሁሉ ዘማች ፤
ሁሉም ጥሬ አሳሽ ፣ ስብስብ ነው የዶሮ
አነር ያድነዋል ፣ እንደ ዱር መንጥሮ።
ከስብስቡ መኃል ፣ ባለቀን ሲነጠቅ
ሌላው ዶሮ ይጮኃል ፣ ፈርቶ በመሳቀቅ።
ሲሞላ ግን አፍታ
እየው አበክረህ
ወንድሙን የሸኘ
ያን አልቃሻ ዶሮ
ጥሬ ይናጠቃል
ዛሬም እንደ ዱሮ።
አይገርምም ?
አይደንቅም?
የሞት ማግስት ወጉ
አነርን ይረሳል የዶሮ ዝንጉ።
🐓

(ሚካኤል አ)

@Samuelalemuu


ገነቴ
የልጅነቴ
ደስ የምትለኝ ፍርሃቴ
የምታሳደኝ ልክፍቴ
ገነቴ የኔዋ ገነት
የሰፈራችን እመቤት
አባዬ
ሊገርፈኝ
ለበጥ
ሲቆርጥ
በርሬ ወደ'ሷ ምሮጥ ።
በቀሚሷ የምትሸሽገኝ
በእቅፏ የምትከልለኝ
«በሞቴ» እያለች «በሞቴ»
ገነቴ
የልጅነቴ
እንደ ጥላ
እንደ ቡችላ
የማልጠፋ ከኋላዋ
«ማነው ?» «ምንሽ ነው ?» ሲሏት
ገልመጥ አድርጋኝ በኩራት
«ባሌ ነው» ምትል «የኔ ባል»
ያውም በሰዎች መሐል !
ድንብር - ድንብርብር ብዬ
ሮጬ የምሸሸጋት
ተሸሽጌ የምፈልጋት
እየወደድኩ የምሰጋት
ገነቴ
የልጅነቴ
የምታሳደኝ ልክፍቴ
የሆነ 'ለት
አንድ ጠዋት
ካለች ብዬ
እንደ ሁልጊዜዬ
( ሳላንኳኳ )
በሩን ከፈትኩ - የቤቷን
አየሁት - ጡቷን ክፍተቷን
ደንግጬ ሮጥኩኝ ወደ ቤቴ ...
ከዚያማ ...
ከዚያ ኋላማ ገነቴ
ገነቴ የልጅነቴ
እንደ ምትሃት
እንደ አስማት
ሐኪም የማያውቃት
ቃልቻ ዱዓ ያላስለቀቃት
ሳልወድ የግዴን የምታመናት
የሌት አድባሬ ፥ የህልሜ ዛር ናት ።

By Habtamu Hadera

@Samuelalemuu


...እና፣ ትላንት እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ፣ ከ50 ገጣሚያን ጋ የተሳተፍኩበት #ክንፋም_ከዋክብት እንደዚህ ባማረ መልኩ አለፈ።

በዚህ ግጥም ላይ ለደከማቹት #Seifu_worku እና #getachew_alemu ላቅ ያለውን ምስጋና ቶስዳላቹ፤ በተጨማሪ በግጥሜ ላይ በርታ፣ ይኼን አርመው ስትሉኝ ለነበረ በሙሉ ምስጋዬ የላቀ ነው።

በዝግጅቱ ላይ ትልቅ ሃላፊነት ከአንጋፋዎቹ አርቲስቶች፦
#አርቲስት_አዜብ_ወርቁ #ጋሽ_ስዩም_ተፈራ #ገጣሚ_ዮሐንስ_ሞላ ፣ #ጋሽ_ሀይለመለኮት_መዋዕለ እና ሌሎች ተጭኖብኛል። ከፈጣሪ ጋ እንግዲህ ጥሩ ነገሮችን ይዤ እመጣለሁ። አመሰግናለሁ!!


@Samuelalemuu

20 last posts shown.