"ሳይንስ ውጫዊውን ምስጢር ሲፈልግ ሃይማኖት ደግሞ ውስጣዊውን ምስጢር ይፈልጋል።"
ሊቅነት ይብቃ። ሊቅነት የማይረባ - ነገር ነው፤ በሳይንስና በሃይማኖት መካከል ድልድይ ሊሆን አይችልም፡፡ ቡድሃዎች እንጂ ስለ ቡድሃዎች የሚያውቁ አያስፈልጉንም፡፡ የሚያስፈልጉን ተመሳጮች፣ አፍቃሪዎች፣ የተግባር ሰዎች ናቸው። ቀኑ ደርሷል፡፡ ሳይንስና ሃይማኖት ተገናኝተው በመታገል ሊጣመሩ ይችላሉ፡፡ ያም ቀን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ቀን ይሆናል፤ በዚያ ዕለት የስብዕና መከፋፈል ይጠፋና ቀኑ የደስታ፣ ተነፃፃሪ የሌለው፣ የተለየ ይሆናል፡፡ ከዚያም ሳይንስና ሃይማኖት ተብለው የተከፈሉ ሁለት ነገሮች አይኖሩንም - አንድ ብቻ እንጂ፡፡
የሰው ልጅ ለውጭው ሳይንሳዊ ዘዴን ይጠቀማል፣ ለውስጡ ደግሞ ሃይማኖታዊ ዘዴን ይከተላል፡፡ «ሚስቱዝም» የሚለው ቃል ውብ ነውና ለሳይንስ ወይም ለሃይማኖት ሊያገለግል ይችላል፡፡ «ሚስቱዝም>> የሚለው ቃል የተዋበ መጠሪያ ይሆናል፡፡ ሳይንስ ውጫዊውን ምስጢር ሲፈልግ ሃይማኖት ውስጣዊውን ምስጢር ይፈልጋል፤ እነዚህ ሁለቱ የሚስቲዝም ሁለት ክንፎች ይሆናሉ፡፡ ሚስቲዝም የሁለቱ ውህድ ሊሆን ይችላል፡፡
ከዚህ ውህደት በኋላ ብዙ ውህደቶች ተከታትለው ይመጣሉ። ለምሳሌ፣ ሳይንስና ሃይማኖት በሚስቲዝም ከተዋሃዱ ምስራቅና ምዕራብ ይዋሃዳኑ፣ ወንድና ሴት ይዋሃዳሉ፣ ግጥምና ስድ ፅሁፍ ይወሃዳሉ፣ ሎጂክና ፍቅር ይዋሃዳሉ፣ አንድ ወሰን ከሌላኛው ይዋሃዳል። አንዴ ይህ ከሆነ ፍፁም፣ ምሉዕ፣ ሚዛናዊ ሰው እናገኛለን፡፡
ሳይንስ አሁን ባለበት ሁኔታ የተዛባ ነው፤ ከግምት የሚያስገባው ቁስ አካላዊ ነገሮችን ብቻ ነው፤ መንፈሳዊ ነገሮች ላይ አያተኩርም:: ይህ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው::
ሰው ቁስ አካል ብቻ ከሆነ ትርጉም ያለው ነገር በሙሉ ከህይወት ይጠፋል፡፡ ሰው ቁስ አካል ብቻ ከሆነ ሀይወት ምን ትርጉም ይኖራታል? ምን አይነት ቅኔ ይፈጠራል? ጥቅሙስ ምን ይሆናል? ሰው ቁስ ነው የሚለው ሃሳብ ሰውን ክብር ወደሌለው ሁኔታ ዝቅ ያደርገዋል:: ይህ ሳይንስ የሚባል ነገር የሰውን ልጅ ክብር ጠራርጎ ወስዷል፡፡ ለዛም ነው በመላው ዓለም የትርጉም አልባነት ስሜት የተንሰራፋው::
ሰዎች ፍፁም ባዶነት እየተሰማቸው ነው:: አዎ፣ የተሻሉ ማሽኖች፣ የተሻለ ቴክኖሎጂ፣ የተሻሉ ቤቶች፣ የተሻለ ምግብ አላቸው:: ይህ ሁሉ ሃብት፣ ይህ ሁሉ ቁስ አካላዊ ዕድገት ግን ከቁስ አካል፣ ከአካል፣ ከአዕምሮ የላቀ ዕይታ ከሌላችሁ፤ የወዲያኛውን ማጣጣም ካልቻላችሁ ምንም ዋጋ አይኖረውም፡፡ ሳይንስ ደግሞ የወዲያኛውን ዘንግቶታል።
ሳይንስ ህይወትን በሁለት ከፍሎ ያያል፤ የታወቀውና ያልታወቀው፡፡ ሃይማኖተኝነት ህይወትን በሶስት ከፍሉ ይመለከታል፤ የታወቀው፣ ያልታወቀው እና የማይታወቀው:: ትርጉም የሚመነጨው ከማይታወቀው ነው:: የታወቀው ትናንት አይታወቅ የነበረው ነው፡፡ ያልታወቀው ደግሞ ነገ የሚታወቀው ነው:: በታወቀውና ባልታወቀው መካከል ምንም የባህርይ ልዩነት የለም-የጊዜ ጥያቄ ወይም ጉዳይ ነው።
የማይታወቀው በባህርዩ ከታወቀው/ካልታወቀው ዓለም ይለያል፡፡ የማይታወቅ ማለት ሚስጥር አለ ማለት ነው፤ የፈለገ በጥልቀት ብትገቡበት ምስጢሩን ልትፈቱ አይቻላችሁም:: በጥልቅት በገባችሁ ልክ ምስጢሩም የበለጠ ጥልቅ ይሆናል፡፡ ይህ አይነቱ ምስጢር ፈላጊ በፍለጋው ሊገፋ በማለዳ ፀሃይ እንደሚጠፋ ጤዛ ህይወቱም እንዲያ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። ይሄኔ ምስጢሩ ብቻ ይቀራል፡፡ ይህ የእርካታ ጫፍ ነው፤ ሰውየው ቤቱ ደርሷል ማለት ነው። ይህንንም እግዚአብሄር፣ ኒርቫና ወይም የፈለጋችሁትን ልትሉት ትችላላችሁ::
እኔ ሳይንስን አልቃረንም - አቀራረቤ በመሰረቱ ሳይንሳዊ ነው። ነገር ግን ሳይንስ ውሱንነቶች አሉበት። እኔ ሳይንስ በቆመበት አልቆምም፤ ከዚያ አልፌ ርቄ እሄዳለሁ።
ሳይንስን ተጠቀሙበት እንጂ መጠቀሚያው አትሁኑ:: ትልቅ ቴክኖሎጂ መያዝ መልካም ነገር ነው፡፡ እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ካላስፈላጊ ስራ፣ ካላስፈላጊ ጭቆና ያወጣሉ፡፡ ቴክኖሎጂ ለሰውም ለእንስሳትም ሊጠቅም ይችላል፡፡ እንስሳት እየተጠቀምንባቸው ስለሆነ ስቃይ ውስጥ ናቸው፡፡ ማሽኖች እነዚህን እንስሳት ተክተው ሁሉን ስራ ሊሰሩ ይችላሉ. .. ሰውና እንስሳት ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ::
የሰው ዘር በሙሉ ከስራ ነፃ እንዲሆን እፈልጋለሁ - ምክንያቱም - ከስራ ነፃ ስትሆኑ በስነ - ውበት፣ ስሜታዊነት፣ መዝናናት፣ ተመስጦ ረገድ ማደግ ትጀምራላችሁ፡፡ የበለጠ ጥበበኛና መንፈሳዊ ትሆናላችሁ- ምክንያቱም በቂ ጊዜና ሃይል ይኖራችኋል፡፡
እኔ ሳይንስን ተቃዋሚ አይደለሁም፤ ፍፁም ሳይንስን አልፃረርም፡፡ ሰው ለትልቅ ነገር ዝግጁ እንዲሆን፣ አንድ ምስኪን ሊያገኘው የማይችል ትልቅ ነገር፣ ዓለም በብዛት ከሳይንስ ተቋዳሽ እንድትሆን እፈልጋለሁ፡፡
ሃይማኖት የድሎት መጨረሻ ነው፡፡ ድሃው ሰው ስለ ቁራሽ ዳቦ እንዲያስብ ተገድዷል፡፡ ማግኘት ስላልቻላቸው መጠለያ፣ ልብሶች ሊያስብ የግድ ነው:: መላ ህይወቱ ዋጋ ቢስ በሆነ ነገር የተጨናንቀ በመሆኑ ለአምላኩ የሚሆን ጊዜና ስፍራ አይኖረውም።
ምንጭ ፦ ህያውነት ፫ (ኦሾ)
ትርጉም ፦ ሀብታሙ ተስፋዬና
ተስፋሁን ምትኩ
@Zephilosophy@Zephilosophy