✍️ የሰጠኸኝ ሴት እግዚአብሔር አዳምን "አትብላ ካልሁህ ዛፍ በላህን?" ብሎ ጠየቀው:: አዳምም :- ከእኔ ጋር እንድትሆን የሠጠኸኝ ሴት ከዛፉ ሠጠችኝና በላሁ አለ::
የሰጠኸኝ ሴት! በጣም ይገርማል:: ሚስቴ አላለም:: አዳምና ሔዋን የተገናኙ ቀን አዳም ያለውን አስታውሱ "ይህች አጥንት ከአጥንቴ ይህች ሥጋ ከሥጋዬ" ብሎአት ነበር:: ምንም እንክዋን አዳም ወላጆች ባይኖሩትም ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ብሎም ነበር:: ራቁታቸውን ቢሆኑም አይተፋፈሩም ነበር::
አሁን በራቁቱ ብቻ ሳይሆን በሔዋንም አፈረባት:: እናትና አባቱን ይተዋል እንዳላለ ሔዋንን ራስዋን ተዋት:: ከሚስቱ ጋር መተባበር ቀርቶ ክስ ጀመረ::
አካሌ አጥንቴ ሥጋዬ ማለቱ ቀረና የሠጠኸኝ ሴት አለ:: የጫጉላው ጊዜ አለፈና ከሚስትነትዋ ሴትነትዋ ብቻ ታየው::
በጋብቻ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሠጠንን ነገር ሁሉ ቀድመን የራሳችን እናደርጋለን ነገሮች ሲበላሹ ግን ባለቤትነቱን ወደ እርሱ እንመልሰዋለን::
የሠጠኸኝ ሥራ
የሠጠኸኝ ወላጆች
የሠጠኸኝ ሰፈር
የሠጠኸኝ ሀገር
የሠጠኸኝ መሪ
የሠጠኸኝ ጉዋደኞች
የሠጠኸኝ ደካማ ሥጋ
የሠጠኸኝ ዓይን
ትናንት ሲሠጠን ዘምረን የተቀበልነውን ሥጦታ ዛሬ ለምሬት እንጠቅሰዋለን:: የሠጠኸኝ የሠጠኸኝ .... ሠጠኝና በላሁ ብለን ቀርጥፈን ለበላነው ዕፀ በለስ ፈጣሪን እንከስሰዋለን::
(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)