ኒካሕና ቃዲ
~
እንደሚታወቀው በኢስላም የትኛዋም ሴት ያለ ወሊይ ፈፅሞ ልታገባ አይፈቅድላትም። ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል:–
أَيُّمَا امْرَأَةٍ نُكِحَتْ بِغَيْرِ إِذْنِ وَلِيِّهَا فَنِكَاحُهَا بَاطِلٌ، فَنِكَاحُهَا بَاطِلٌ، فَنِكَاحُهَا بَاطِلٌ
"ያለ ወሊዩዋ ይሁንታ የተገባች የትኛዋም ሴት ጋብቻዋ ውድቅ ነው! ጋብቻዋ ውድቅ ነው! ጋብቻዋ ውድቅ ነው!" [አቡ ዳውድና ቲርሚዚ ዘግበውታል።]
ወሊይ ከሌለስ? በዚህን ጊዜ ኒካሑ በቃዲ ይታሰራል። ስለዚህ ኒካሕ ለማሰር ቃዲ የሚያስፈልገው ወሊይ ለሌላት ሴት ነው ማለት ነው። ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
َ (فالسلطان ولي من لا ولي له)
"አስተዳዳሪ ወሊይ ለሌለው ወሊይ ነው።" [አልባኒይ ሶሒሕ ብለውታል]
በተጨማሪም ወሊዮች ያለ ተጨባጭ ምክንያት ለመዳር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ከቀሩ ኒካሑ በቃዲ ይታሰራል። ከዚህ ውጭ አባት ወይም ሌላ ወሊይ ወይም ወኪል ካለ ኒካሑን የሚያስሩት እነሱ እንጂ ቃዲዎች አይደሉም። ወሊይ ወይም ወኪሉ "ሰጥቻለሁ" ካለ፣ አግቢው ወይም ተወካዩ "ተቀብያለሁ" ካለ ኒካሕ ታስሯል። ኹጥባውን (ሸርጥ ካለመሆኑም ጋር) ወሊይ ወይም ሌላ ቦታው ላይ የተገኘ ሰው ሊያደርገው ይችላል።
ኒካሕ ለማሰር የተለየ ውስብስብ መስፈርት የለም። የዐረብኛ ቃላት መጠቀምም አይጠበቅም። መስፈርቶች እስከተሟሉ ድረስ በየትኛውም ቋንቋ ቢሆን መስጠትና መቀበል ከተገኘ ኒካሕ ታስሯል። ስለዚህ በሃገራችን በሰፊው እንደሚደረገው ወሊይ እያለ ቃዲ መጥራት አይጠበቅም። ቃዲዎች ወሊይ ባለበት ሁኔታ ኒካሕ ለማሰር አትቀደሙ። ያለ ስልጣናችሁ ጣልቃ አትግቡ።
ወሊይ የሆናችሁ ሰዎች ደግሞ ቃዲዎችን ለሰርግ ከጠራችሁ እንደማንኛውም እድምተኛ ተስተናግደው ይመለሱ እንጂ እዚያው ተቀምጣችሁ ለነሱ ውክልና አትስጡ። "ልጄን እከሊትን ድሬሃለሁ" ማለት ያቅታችኋል? ምንም የተለየ የተቀመጠ ቃል የለምኮ። እሱም "ተቀብያለሁ" ካለ፣ ቦታው ላይ ሁለት ታማኝ ምስክሮች ከኖሩ ኒካሑ ታስሯል አለቀ። ባገር እያለህ፣ ዐቅልህ ጤነኛ ሆኖ ሳለ እንዴት ከፊትህ ለሚፈፀም ጉዳይ ውክልና ትሰጣለህ? ምንም የሚያስፈራ ነገር የለምና እራስህ ፈፅመው። ሁሉም ነገር በቃዲ በኩል እንዲያልፍ መደረጉ አንዳንድ መረን የለቀቁ ባለስልጣናት በማያገባቸው የእምነታችን ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ በር እየከፈተ ነው። አንዳንድ ቃዲዎችም ጉዳዩን ያላግባብ የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ።
=
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor