ፍትሕ ለአክሱም ሙስሊሞች‼
«
የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ቅሬታከ 12 ሰዓታት በፊትከ 12 ሰዓታት በፊት
በአክሱም ከተማ የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከሒጃብ መልበስ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው እንደሚገኙ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ስታወቀ። ይህን ለመፍታት ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር ንግግር ላይ መሆኑም የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ለዶቼቬለ ገልጿል።
ከአክሱም ያናገርናቸው ሴት ተማሪዎች ሒጃብ ለብሳችሁ ወደ ትምህርት ቤት አትገቡም ተብለው ከአንድ ሳምንት በላይ ከትምህርት መገለላቸው ገልፀዋል። በጉዳዩ ላይ ከትግራይ ትምህርት ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
በዚህ ዓመት ከሒጃብ መልበስ ጋር በተገናኘ በአክሱም በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውዝግቦች መታየት የጀመሩት ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከአክሱም ከተማ የተለያዩ ምንጮች እንደሰማነው፥ በከተማዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሒጃብ የለበሱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተከትሎ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቃቸው ተገልጿል።
በከተማዋ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መታየቱ ተከትሎ ባለፈው ኅዳር ወር መጀመርያ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ለትግራይ ትምህርት ቢሮ ቅሬታ መጻፉን የገለፁት የክልሉ እስልምና ጉዳይ ምክርቤት ጸሐፊ ሓጂ መሓመድ ካሕሳይ፥ በክልሉ በኩል አወንታዊ ምላሽ ቢኖርም እስካሁን ግን ማስተካከያዎች እንዳልተደረጉ ተናግረዋል።
ከአክሱም ከተማ ያነጋገርናት እና ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች የአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ፥ እርሷን ጨምሮ ሌሎች፥ ሒጃብ ለብሰው መግባት እንደማችሉ በትምህርት ቤቱ ሐላፊዎች ተከልክለው ከአንድ ሳምንት በላይ ከትምህርት ውጭ መሆናቸውን ትናግራለች።
ተመሳሳይ ውዝግብ እና ችግር ከዚህ በፊትም ቢሆን በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች ታይቶ እንደነበረ የሚያነሱት የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ጸሐፊ ሓጂ መሓመድ ካሕሳይ፥ ችግሩ በወቅቱ በንግግር መፈታቱን ያስታውሳሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ዋና ፀሐፊው፥ አሁን በአክሱም እየታየ ያለው የሴት ሙስሊም ተማሪዎቹ ጉዳይ ባለው ሕግ መሠረት በአጭር ጊዜ ይፈታል ተብሎ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል። በቅሬታ አቅራቢዎቹ ስለተነሱ ጉዳዮች ከአክሱም ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት እና ከትግራይ ትምህርት ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።»
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ
©: DW Amharic