#ቤንዚን🚨
🔴
" በክልሉ የቤንዚን ችግር የፀጥታ ጉዳይ ወደ መሆን ደርሷል " - የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
🔵 " በማደያዎች አከባቢ የሚነሱ ሕገ ወጥ ተግባራት ሕብረተሰቡ በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ እያደረገ ነዉ " - የሲዳማ ክልል ንግድ ቢሮበሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተለይም በመዲናዋ ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣዉን ቤንዚን ማግኘት ፈተናን ተከትሎ የተስተዋሉ ችግሮችን በተደጋጋሚ መዘጋባችን ይታወሳል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በትላንትናዉ ዕለት በሰጡት መመሪያ፥ በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የሚመራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ግብረ-ኃይሉ በዛሬው ዕለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሰፊ ዉይይት በማድረግ የዉሳኔ ሃሳቦችን ማስተላለፉን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ማወቅ ችሏል።
በዚህም መሰረት በተለያዩ ክልሎች የነዳጅ ምርት እጥረት ቢኖርም በሲዳማ ክልል በተለይም በሀዋሳ ከተማ ያለዉ የህገ-ወጥ ንግድ ህብረተሰቡን ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲዳርግ መቆየቱ ተጠቅሷል።
በማደያዎች፤ በንግድና ገበያ ልማት ባለሙያዎች ፤ ከፀጥታ አካላት በኩል ያሉ ክፍተቶች በመድረኩ ተነስቷል።
ማደያዎች በሌሊት ለቸርቻሪዎች ከመሸጥ እስከ ነዳጅ ቦቴዎችን መሰወር ድረስ ፤ የንግድና ገበያ ልማት ባለሙያዎች ደግሞ ከሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ጋር አብሮ መስራትን ጨምሮ ከማደያ ቀጂዎች ጋር በመመሳጠር ቤንዚን ማሸሽ ድረስ ተሳታፊ ነበሩ ተብሏል።
እንዲሁም የፀጥታ አካላት የሌሎችን ተሽከርካሪዎች የራሳቸዉ በማስመሰል ለህገወጥ ግብይቱ ምክንያት መሆን ጨምሮ ተገቢውን እርምጃ አልወሰዱም የሚል ግምገማም በመድረኩ ቀርቧል።
ግብረ-ኃይሉ ለእነዚህ እና ሌሎችም መሰል ችግሮች የመፍትሔ ኃሳቦች ናቸዉ ያላቸዉን አስቀምጧል።
አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊና የግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢ ምን አሉ ?በክልሉ የቤንዚን ችግር የፀጥታ ጉዳይ ወደ መሆን ደርሷል ያሉ ሲሆን፥ በዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ የተጀመረዉ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።
" መንግስት በከፍተኛ ድጎማ የሚያስገባውን ቤንዚን ማንም ከዚህ በኋላ ለግል መበልፀጊያ ማድረግ አይችልም ፤ ከዛሬ ጀምሮ የቤንዚ አቅርቦትና ስርጭት ሂደቱን ግብረሃይሉ ይመራዋል " ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም ከዚህ ቀደም ተሽከሪካሪ ተለይቶ ይደለደል የነበረዉ አሰራር ከነገ ጀምሮ አይኖርም ነው ያሉት።
ማደያ ለሌለባቸዉ አከባቢዎች ሲደረግ የነበረዉ አሰራር በሕግና ደንቡ መሠረት ብቻ ይከናወናልም ሲሉ አንስተዋል።
ማንኛዉም የፀጥታ መዋቅር አባላት ያሏቸዉ የቤንዚን ተሽከሪካሪዎች በየተቋሞቻቸዉ ተለይተዉ በሕጋዊ መንገድ በኩፖን ብቻ እንደሚስተናገዱ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ ተናግረዋል።
አክለውም "
ከነገ ቀን ጀምሮ በቤንዚን ሽያጭ ላይ በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች በተለይ ደግሞ ሀዋሳ ከተማ ላይ ይታይ የነበረዉን ሕገ-ወጥ ስርዓት አደብ እናስገዛለን " ብለዋል።
በተጨማሪም ፦
➡️ የፀጥታ መዋቅር አባላት ከየማደያዉ ጣልቃ ገቢነት እንደሚወጡ፤
➡️ ከነገ ጀምሮ ካሜራ ያልገጠሙ ማደያዎች አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።
የክልሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሠላማዊት መንገሻ ምን አሉ ?" በማደያዎች አከባቢ የሚነሱ ህገወጥ ተግባራት ሕብረተሰቡ በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ እያደረገ ነዉ " ሲሉ ተናግረዋል።
ኃላፊዋ፥ " እንደ ሀገር የአቅርቦት እጥረት ቢኖርም በሀዋሳ ከተማ በብዛት የሚስተዋለው ግን ሰዉ ሰራሽ ችግር ነዉ ፤ ይህም ችግር ዘርፈ ብዙ መሆኑን በጥናት አረጋግጠናል " ብለዋል።
" መንግስትንና ሕዝብን ለማጣላት የሚሰሩ ማደያዎችን ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ እርምጃው ይቀጥላል፤ ከኤልክትሮንክስ ግብይት ዉጪ ሽያጮችን የሚያካሂዱ ማደያዎችም በሕግ አግባብ ከመጠየቅ ባለፈ የነዳጅ ምርቶችን መግኘት አይችሉም " ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
አሁን ላይ ጣት ከመጠቋቆምና አንዱ በሌላዉ ከማማካኘት ይልቅ ሕዝብ በተማረረበት በዚህ የቤንዚን ጉዳይ አስቸኳይ እርምጃ መዉሰድ እንደሚያስፈልግም ወ/ሮ ሠላማዊት መንገሻ በመድረኩ አንስተዋል።
⚠️ከፍተኛ የቤንዚን ችግር ሲዳማ ክልል ውስጥ ብቻ ያለ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉት ሁሉም ክልሎች ላይ ተመሳሳይ ነው። ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ዜጎች ስራ ሰርተው መግባት መኖር ፤ ቤተሰብ ማስተዳደር ፍጹም አልቻሉም። ህዝቡ እጅግ ተማሯል። ማደያዎች ላይ " የለም " ይባላል ግን በጥቁር ገበያ እስከ 200 ብር ድረስ በግልጽ በአደባባይ ይቸበቸባል። አንዳንድ ከዋና ዋና ከተማ በወጡ ማደያዎች በትውውቅ በሊትር እስከ 200 ብርና ከዛ በላይ ይቸበቸባል። ቤንዚን ለሊት ላይ በድብቅ ከየማደያው እየተጫነ ከከተማ በህገወጥ መንገድ ይወጣል። ይህ ህገወጥ ተግባር መንግሥት እርከን ውስጥ ካሉ አካላት አንስቶ የማደያ ሰዎች፣ የጸጥታ ሰዎች ከላይ እስከ ታች ድረስ ረጅም ሰንሰለት ነው ያለው።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የክልሎች የቤንዚን ስርጭትን ጉዳይ አሁንም መከታተሉን ይቀጥላል።
#TIKVAHETHIOPIA
@tikvahethiopia