#ልጅሽ_ወደ_ሕይወት_ወደ_ክብር_መንግሥት_ይጠራሻል
#የከበረች_እመቤታችን በ49 ዓ.ም ጥር 21 እሑድ ቀን 64 ዓመት ሲሆናት ልጇ ወዳጇ መጥቶ እናቴ ከዚህም ዓለም ድካም የምትለይበት የምታርፊበት ቀን ቀርቧል አላት ያንጊዜ እመቤታችን ደነገጠች።
መደንገጧ ሞትን ፈርታ የዚህ ዓለም ኑሮ አጓጉቷት አይደለም እንዴት የሕይወት እናት ሆኜ እሞታለሁ? የትንሣኤ እናት ሆኜ እንዴት እቀበራለሁ? ሕይወትንንና ትንሣኤን ያዩ ዐይኖቼ እንዴት በሞት ያሸልባሉ ?
ሕይወትንና ትንሣኤን ያቀፉ እጆቼ እንዴት ይገነዛሉ ? አካለ መለኮትን የተሸከመች ጀርባዬ ከመቃብር አፈር ላይ እንዴት ትተኛለች ? ገጸ መለኮትህን የሳሙ ከንፈሮቼ እንዴት በሞት ይዘጋሉ ? በፍጹም አልሞትም ስትለው ነው፡፡
ጌታ ግን አልሞትም ስትለው አልተሟገታትም ያለፈቃዷ ምንም ምን ማድረግ አልፈለገም ምክንያቱም እናቱ ናትና ይወዳታልና ሌላ ማሳመኛ ዘዴ አዘጋጀ ይህውም ልቧን ያውቃል የኀጥአን ነገር እንደማይሆንላት ርኅራኄዋን ስለሚያውቅ መላእክትን ወስዳችሁ በስቃይ ቦታ የሚቃጠሉ ነፍሳትን አሳይዋት ብሎ አዘዛቸው።
እነርሱም ለሰይጣንና በእርሱ ጎዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደ ተዘጋጀ ወደ ጨለማው ዳርቻ አደረሷት ከዚያ ነፍሳት ሲቃጠሉ አየችና አለቀሰች እንዲህም አለች ‹‹ ልጄ ወዳጄ ዛሬ በሲዖል ሲቃጠሉ በራዕይ ያየኋቸውን ነፍሳት እባክህን ማርልኝ አለችው››።
ጌታም ‹‹ እናቴ ! እኔ ዐምስት ሺ ዐምስት መቶ ዘመን በሲዖል ሲቃጠሉ የኖሩትን ነፍሳት ያዳንኳቸው ሞቼላቸው ነው አንቺም እንዲድኑ ከወደደሽ ሙቺላቸው አላት››።
እመቤታችንም ‹‹ አይደለም አንድ ጊዜ ቀርቶ ሰባት ጊዜ ልሙት አለችው ›› ይህንን ቃሏን ምክንያት አድርጎ እርሷም ለነፍሳት ልትሞትላቸው እርሱም ነፍሳትን ሊያድንላት ተስማሙ።
ወዲያው ከደብረ ዘይት ደናግል መጡ የቅርብ አገልጋይዋ ዮሐንስ ከሀገረ ስብከቱ ከኤፌሶን በደመና ተጭኖ መጣ ሐዋርያትም ከየሀገረ ስብከታቸው በመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ በደመና ተጭነው ወደ እመቤታችን ተሰበሰቡ።
ሁሉም በኅብረት ‹‹ የጌታችን እናት ጸጋን የተመላሽ ደስ ይበልሽ ›› እያሉ እየሰገዱ አመሰገኗት ሐዋርያትን እንዲህ አለቻቸው ‹‹ ዕጣን አምጥታችሁ እያጠናችሁ የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ጥሩ ›› አለቻቸው እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ ።
በዚህ ጊዜ ጌታችንም ከሰማይ ከጌትነቱ ዙፋን አባቷ ዳዊትን የነቢያትንና የመላእክትን ማኅበር አስከትሎ እንደ ግድግዳ ከበውት ወደ እርሷ መጣና አረጋጋት ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት።
የክብር ባለቤት ጌታችንም ‹‹ እንግዲህ ሥጋሽን ተድላ ወዳለበት ገነት አፈልሰዋለሁ ዳግመኛም ሥጋሽን ከነፍስሽ ጋር አዋኅጄ አስነሥቼ መላእክት የሚያመሰግኑበት ተመሳሳይ በሌለው ተድላ ደስታ ባለበት ማደሪያ አኖርሻለሁ›› አላት።
ከሥጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሐዋርያትና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት እጅዋን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው።
በይባቤ መላእክት በመዐዛ ገነት እነሄኖክ እነእዝራ በበገና በመሰንቆ እያመሰገኗት ንጽሕት ነፍሷን ከንጹሕ ሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጎናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት ።
ቅዱሳን ሐዋርያት ሥጋዋን እንደሚገባ ገንዘው ወደ ጌቴሴማኒ ተሸክመው እንዲወስዷት አዘዛቸው ሐዋርያትም በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሄዱ። ከዚህ በኋላ መልአኩ እመቤታችንን ከዮሐንስ ጋራ በደመና ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት እግር አኑሯታል።
ማርያም ሆይ ስለሁላችን የነፍስ ይቅርታ ከልጅሽ ከወዳጅሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምኚልን🙏
#ይኽ_ትምህርት_ለሁሉም_የተዳረሰ_ይሆን_ዘንድ_ሼር_ላይክ_ኮመንት_እናድርገዉ_ቻናሉንም_ለብዙዎች_ተደራሽ_እያደረግን_የሚሰጡ_ትምህርቶችን_በማዳረስ_ሐዋርያዊ_አገልግሎት_እንስጥ!
አምኀ ተዋሕዶ ዘክርስቶስ በYoutube Sador Sisay on YoutubeSador Sisay on InstagramSador Sisay on FacebookSador Sisay on Tiktok#You_tube #Instagram #Facebook_pages subscribe እና share እያደረጋችሁ አገልግሎታችንን ተደራሽ በማድረግ አግዙ🙏🙏🙏