Репост из: የእምነት ጥበብ
የሚገርም ወይም የማይታመን ምን አለ፣ መንፈስን የሚሰጥ ጌታ ራሱ በመንፈስ እንደተቀባ እዚህ ሲነገር፣ አስፈላጊ ሁኖ በተገኘበት ጊዜ፣ ስለ ሰውነቱ ራሱን ከመንፈስ ያነሰ ብሎ ከመናገር አልተቃወመም? አይሁዶች በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣል ስላሉት፣ እርሱ ስድባቸውን ለማጋለጥ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፣ "እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ" እነሆ፣ የመንፈስ ሰጪ እዚህ በመንፈስ አጋንንትን እንዳወጣ ይናገራል፤ ይህ ግን ከሥጋው የተነሣ ካልሆነ በቀር አይባልም። የሰው ተፈጥሮ ራሱ አጋንንትን ለማውጣት በቂ ስላልሆነ፣ በመንፈስ ኃይል ብቻ እንጂ፣ እንደ ሰው "እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ" አለ። እርግጥ ነው፣ ለመንፈስ ቅዱስ የሚቀርብ ስድብ ከሰውነቱ ላይ ከሚቀርበው እንደሚበልጥም አመልክቷል፣ "በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤" እንደ "ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን?" ያሉት ዓይነት፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደቡና የቃሉን ሥራ ለዲያብሎስ የሚያስቡ፣ የማይቀር ቅጣት ይደርስባቸዋል። ይህ ጌታ ለ አይሁዶች እንደ ሰው የተናገረው ነው፤ ለደቀ መዛሙርቱ ግን መለኮቱንና ግርማውን እያሳየ፣ ከመንፈስ ያነሰ ሳይሆን እኩል እንደሆነ እየጠቆመ፣ መንፈስን ሰጣቸውና፣ "መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ" አለ፣ ደግሞም "እኔ እልከዋለሁ"፣ "እርሱም ያከብረኛል"፣ "የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል" አለ። እንግዲህ በዚህ ስፍራ ራሱ ጌታ፣ የመንፈስ ሰጪ፣ በመንፈስ አማካኝነት አጋንንትን እንደ ሰው እንዳወጣ ለመናገር አልተቃወመም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ እርሱ ራሱ የመንፈስ ሰጪ፣ "የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ እርሱ ቀብቶኛልና ኢሳይያስ 61:1" ብሎ ከመናገር አልተቃወመም፣ ዮሐንስ እንደተናገረው ሥጋ በመሆኑ፤ በነዚህ በሁለቱም ሁኔታዎች፣ እኛ በመቀደሳችን የመንፈስ ጸጋ እንደሚያስፈልገን፣ ደግሞም ያለ መንፈስ ኃይል አጋንንትን ማውጣት እንደማንችል እንዲታይ ነው። እንግዲህ መንፈስ የሚሰጠው በማን በኩልና ከማን ነው? መንፈሱ ደግሞ የእርሱ ከሆነ ከልጁ በቀር? መቼስ እንቀበለው ዘንድ ተቻልን? ቃል ሥጋ በሆነ ጊዜ ካልሆነ? ሐዋርያው እንደገለጸው፣ በእግዚአብሔር መልክ ያለው እርሱ የባሪያን መልክ ካልወሰደ እኛ ባልተቤዠንም ከፍ ከፍ ባልተደረግን ነበር፤ ስለዚህም ዳዊትም ደግሞ፣ የመንፈስ ሰጪ ራሱ ቃል፣ ስለ እኛ በመንፈስ እንደተቀባ ስለተናገረ፣ ያለ እርሱ በመንፈስ ተካፋዮችና የተቀደሱ ልንሆን እንደማንችል ያሳያል። ስለዚህም በሥጋ እንደተቀባ ስለተባለ በጽኑ ተቀብለነዋል፤ ሥጋው በእርሱ በመጀመሪያ ስለተቀደሰ፣ እርሱም እንደ ሰው ስለ እርሱ እንደተቀበለ ስለተባለ፣ "ከሙላቱ ተቀበልን ዮሐንስ 1:16" የሚለውን የመንፈስ ጸጋ ተከትሎናል።( st Athanasius, Discourse 1 Against the Arians number 50)