የደሴ ሙስሊሞች በበኩላቸው የጎዳና ላይ ኢፍጣርን ምክንያት በማድረግ፣ የሚናራ ቅርፅ ያለው ባለአራት ማእዘን በጣም ረጅም ነገር ሰርተው፣ ከፒያሳው አደባባይ ላይ ተክለዋል፡፡ አስገራሚው ነገር አደባባዩ ላይ የተተከለው የሚናራ ቅርፅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ከሚያካሂዱበት የሆጤ ሜዳ በኪሎ ሜትሮች የራቀ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ የሚናራ ቅርፁን የተከሉበት የፒያሳው አደባባይ፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በጥምቀት በአላቸው ወቅት፣ መስቀልና የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ስእላ ስእሎችን ለእይታ የሚተክሉበትና የሚያስቀምጡበት መሆኑ ጭምር ነው፡፡ በስሜት ፈረስ የሚታጀበው የቢድአ አውሎ ንፋስ እንዲህ ነው ጥርግ አድርጎ የሚወስድ፡፡ የተከተሉት አርአያ ምንኛ ከፋ! አሏህ እንዲህ ይለናል፡-
"ቅንን መንገድ ቢያዩ፣ መንገድ አድርገው አይዙትም፡፡ ግን የጥመትን መንገድ ቢያዩ መንገድ አድርገው ይይዙታል፡፡" (አል-አእራፍ፣ 146)
ከአዲስ አበባው ጋር ሲነፃፀር እርግጥ ነው፣ በአላባም ሆነ በደሴው የታየው ለውጥ የቅርፅ/የመልክ ብቻ ነው፡፡ የቢድአ አንዱ መገለጫው ይሄው ነው - ከተመሰረተ በኋላ ሲጀመር ያልነበረውን ቅርፅና መልክ ቀስ በቀስ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለውጥ የሚጀምረው ከቅርፁ ነው፡፡ አሁንም ክፍለ ሀገር ላይ የሆነውም ይሄው ነው፡፡ ቢድአው እድሜ እያገኘ በሄደና በተጠናከረ ቁጥር ደግሞ፣ ሁለተኛው መገለጫ ይከተላል - በቅርፅ የተጀመረው ለውጥ ወደ ይዘቱም ይሸጋገራል፡፡ የዚህን ጊዜ በዲን ላይ ያለው አደጋ እጅግ አስከፊ ይሆናል፡፡ የመውሊድም ታሪክ ሲጠና የተጓዘበት ደረጃ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
በጎዳና ላይ ኢፍጣር የተደረገው ስእላ ስእሎችንና ቅርፃ ቅርፆችን መስራት፣ አደባባይ ይዞ መውጣትና የቢድአው አጃቢ ማደረግ የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው? ነገ ከነገ ወዲያ፣ በዚህም ሆነ በሚቀጥለው ትውልድ በስእላ ስእሎቹና በቅርፃ ቅርፆቹ ምን እንደሚሰራ ወይም ወደ ምን አይነት ሌላ ቢድአ ሊሸጋገር እንደሚችሉ አሁን መተንበይ አይቻልም፡፡ ሆኖም ለሸሪአዊ አምልኮ በተጨባጭ የስጋት ምንጭ የመሆናቸው ጉዳይ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡
የኑህ ህዝቦች ሸርክ የጀመሩበትን ቢድአዊ ኢባዳ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ መልካም አስበውና አሏህን ለመገዛት ብለው የጀመሩት ቅርፃ ቅርፅ፣ መዳረሻው የለየለት ሽርክና በመጨረሻም ውሀ መሰጠም ነው የሆነው፡፡ የካእባን ምስል ያቆሙት የአላባዎቹ ሙስሊሞች ወይም ከእነሱ የኮረጁ የሌላ አካባቢ ሙስሊሞች ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ሀሳዊውን ካእባ መጦወፍ ሊጀምሩ የማይችሉበት መንገድ ዝግ አይደለም፡፡ ያኔ ማለቃቀሱ ግን ጥቅም አይኖረውም - ቢድአ እግሩን ከተከለ በኋላ ለመንቀል የሚደረገው ትግል ማገዶ ጨራሽ ነው፡፡ ያም ሆኖ ላይሳካም ይችላል፡፡
ሲጠቃለል፡-
ይህንን "የጎዳና ላይ ኢፍጣር" የሚባል አዲስ መጤ ቢድአ ስሙንና ግብሩን፣ በማንቆለጳጰስና የኢስላምን ካባ በማልበስ በድምቀት እያስከወኑትና ቀጣይ እንዲሆን ለማድረግ እየጣሩ ያሉት አካላት ዋናዎቹ ሶስት ናቸው - የጎዳና ላይ የኢፍጣር ዝግጅትና ክንውን በመኖሩ ያላቸውን ግላዊ ዝናና ታዋቂነት ለማስጠበቅ የሚሰሩ፣ የንግድ ገቢያቸውን የሚያሳልጡና የሰልጣን ወንበራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚፈልጉ አካላት፡፡
"ሸሪአዊ ነው" ካሉ ማስረጃቸውን ማቅረብ አለባቸው፤ ሀያሉ አሏህ በቁርአኑ እንዲህ ይላል፡-
"ከሃይማኖት አሏህ በእርሱ ያልፈቀደውን ለእነርሱ የደነገጉ ተጋሪዎች ለእነርሱ አልሏቸውን?" (አል-ሹራ፣ 21)
ሙስሊሙ ህብረተሰብ በባነርና በዲኮሬሽን ድምቀት፣ በመግለጫ ጋጋታና በተሳታፊ ቁጥር ብዛት የጎዳና ላይ ኢፍጣርን ለማስዋብና ለማስቆነጃጀት በሚደረገው ድራማ ሳይሸወድ፣ "የጎዳና ላይ ኢፍጣር ሸሪአዊ ከሆነ የቁርአንና የሀዲስ ማስረጃው ምንድነው? ሸሪአዊ ከሆነ ካለፉት ዘመናት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለምን አልተከናወነም?" በማለት ሊጠይቅና ከዚህ አዲስ መጤ የአምልኮ ተግባር ሊርቅ ይገባል - ልብ ያለው ልብ ይበል!
በዶ/ር ጀማል ሙሐመድ
የባህር ዳር አህለሱና መሻይኾች ገፅ
https://t.me/alateriqilhaqكن على بصيرة