የመውሊድ በዓል በሚዛን ላይ
""""""""""""""""""""""""
ነሲሓ መጽሔት ቅጽ Vol2 ቁጥር 1
ምስጋና ለአለማት ጌታ ለአላህ የተገባ ነው ፡፡ ሰላት እና ሰላም ለዐለማት እዝነት በተላኩት በነቢያችን ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በሰሃባዎቻቸው እና እነርሱን በመልካም በተከተሉት ሁሉ ላይ እስከ እለተ ቂያማ (ትንሳኤ) ድረስ ይውረድ፡፡
ቁርዓን እና ሐዲስን እንዲሁም ዝርዝር የሸሪዓ ህግጋትን በትክክል መረዳት ለሁሉም ሙስሊም በእጅጉ አስፈላጊ ቢሆንም ቀላል ግን አይደለም።
አላህ ለዚህ ኡማ ታላቅ ውለታ በመዋል ኡለማዎችን ሰጥቶን ያላቸውን ታላቅ ክብር ገልፆልናል፡፡ የሙስሊሞችን እምነት፣ የአምልኮ ‘ዒባዳ’ አተገባበር እና የስነምግባር እሴቶችን ማረም የዑለሞች ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ከሰሀቦችና እነሱን ከተከተሉ ታቢዒዮች መካከል ታላለቅ ዑለማዎች እና የፊቅህ ጠበብቶች ቁርዓንን በተገቢው መልኩ በመረዳት እና ዕድሜያቸውን ሙሉ በማስተማር ሀላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ሰሃባዎች ከማንም በበለጠ በዕውቀት የበለፀጉ ከመሆናቸው ባሻገር የመልእክተኛውን ﷺ ንግግር እና ሱና በመተግበር ፋና ወጊዎች እንደነበሩ አያጠያይቅም።
አብደላህ ኢብን መስዑድ አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና በአንድ ወቅት ስለሰሃባዎች እንዲህ ብለው ነበር፤ "ከዚህ ከነቢዩ ዑመት ከማንም በበለጠ፤ ቅን ልቦና፣ የጠለቀ እውቀት፣ የተቃና ፈለግ እና ያማረ ስብዕና ባለቤት ነበሩ። እነሱ ማለት አላህ ለነብዩ ጓደኝነት የመረጣቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ክብራቸውን እወቁላቸው። ፋናቸውንም ተከተሉ። እነሱ ቀጥተኛው መንገድ ላይ ነበሩ።" ኢብኑ ዐብደል በር / ጃሚዑል በያኒል ዒልም በሚባለው ኪታባቸው ቅጽ 2/946-947 ሰሃባዎች በሐቅ ላይ አንድነታቸውን ለመጠበቅ የተለያዩ ሸሪዓዊ አጀንዳዎች ላይ ይመካከሩና ይተራረሙ ነበር፡፡ ያልደረሳቸውን መረጃ ሲያገኙም ወደ ሐቅ ከመመለስ የሚያግዳቸው ነገር አልነበረም። ለሐቅ ተገዢ ስለነበሩ እርምት ለሰጣቸው አካል ምስጋና እና ክብራቸው ከመጨመሩ ባሻገር በመካከላቸው የነበረው ወዳጅነት አልጎዳም። ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ብለዋል "ሰሃባዎች፣ ታቢዒዮች እና ከእነርሱ በኋላ የመጡት ዑለማዎች በመካከላቸው አለመግባባት በተፈጠረ ጊዜ የአላህን ትዕዛዝ ይከተሉ ነበር፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል «በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትሆኑ የተከራከራችሁበትን ነገር ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፡፡ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው፡፡» ሱረቱ ኒሳዕ : 59 በተለያዩ የዲን አጀንዳዎች ላይ በምክክር መልክ ይወያያሉ፡፡ አልፎ አልፎ የዒልምና እና የተግባር ጉዳዮች ላይ የአቋም ልዩነት ሲኖር መዋደድን፣ መተሳሰርን እና ኢስላማዊ ወንድማማችነትን በጠበቀ ሁኔታ ይተራረማሉ።" መጅሙዑል ፈታዋ 24/172
በየዓመቱ የረቢዐል አወል ወር በገባ ቁጥር የነቢያችንን የልደት በዓል መውሊድን የማክበር ጉዳይ ሰዎችን ሲያወዛግብና መነጋገሪያ ሲሆን ይታያል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሙእሚኖችን በመሰረታዊም ይሁን በቅርንጫፋዊ የዲን ጉዳዮች ላይ አለመግባባት ቢፈጠሩ ጉዳያቸውን ወደ ቁርዓንና ሐዲስ በመመለስ መፍትሄ እንዲፈልጉ በሚከተለው የቁርዓን አንቀጽ አዟል፡፡
فَإِن تَنَازَعْتُمْ فِي شَيْءٍ فَرُدُّوهُ إِلَى اللَّهِ وَالرَّسُولِ إِن كُنتُمْ تُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ ذَٰلِكَ خَيْرٌ وَأَحْسَنُ تَأْوِيلًا ٤:٥٩
«በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ የተከራከራችሁበትን ነገር ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፡፡ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው» ሱረቱ ኒሳዕ : 59
ከዚህ ቁርአናዊ መመሪያ በመነሳት ለአንባቢዎቻችን ነሲሓ ይሆን ዘንድ ትክክለኛውን አቋም እናመላክታለን። አላህ ሀቁን አይተው ከሚከተሉት ሰዎች ያድርገን። ይህ በዓል በሸሪዓ መሰረት የሌለውና ሰዎች በዲን ውስጥ የጨመሩት አዲስ ነገር ከመሆኑ ባሻገር አላህና መልእክተኛው ያልደነገጉትን ተግባር በቀን የተገደበ ወደ አላህ መቃረቢያ አምልኮ ማድረግ መሆኑ ዋነኞቹ የመውሊድ ችግሮች ሲሆኑ፤ በተጨማሪም ክርስቲያኖችን በመፎካከር የመጣ መሆኑ ከእነሱ ጋር መመሳሰል ነው። በተጨማሪ በዚህ በዓል ውስጥ በሸሪዓ የተወገዙ በርካታ ተግባራት ይፈፀማሉ። መውሊድ አንድን ስራ ቢድዓ የሚያሰኙ ምክንያቶች ሁሉ እንዳሉበት አያጠራጥርም። ይህም በሚከተሉት ሶስት ነጥቦች ይብራራል፤
1) አዲስ ነገር መፍጠር (ኢሕዳስ)
ካለ ሸሪዓዊ ማስረጃ፤ ማንኛውንም ቀን ወይም ወር ልዩ ሀይማኖታዊ ክንውን የሚፈፀምበት እንደሆነ በማሰብ በዋጂብነት ወይም ሱናነት ሰዎችን የምናበረታታበት ከሆነ በዲን ውስጥ አዲስ ነገር መፍጠር ነውና ሀራም ነው።
አሏህ እንዲህ ብሏል:-
أَمْ لَهُمْ شُرَكَاءُ شَرَعُوا لَهُمْ مِنَ الدِّينِ مَا لَمْ يَأْذَنْ بِهِ اللَّهُ
«ከሀይማኖት አላህ በእርሱ ያልፈቀደውን ለእነሱ የደነገጉ ተጋሪዎች ለእነርሱ አሏቸውን?» ሱረቱ ሹራ ቁጥር 21
ቡኻሪ እና ሙስሊም በዘገቡት የተረጋገጠ ሰሂህ ሐዲስ ነቢያችን ﷺ ብለዋል፤
مَنْ أحْدَثَ في أمْرِنَا هَذَا مَا لَيْسَ مِنْهُ فَهُوَ رَدٌّ
«በዲናችን ውስጥ ከእርሱ ያልሆነን ነገር የፈጠረ ስራው ተመላሽ ይደረግበታል» ብለዋል።
ይህ ማለት በሸሪዓ ያልተደነገገን ነገር ፈጥሮ ቢፈፅም ተቀባይነት አያገኝም ማለት ነው።
እንደሚታወቀው፤ መውሊድን ረሱል ﷺ የተከበሩት ኸሊፋዎች እና ሌሎችም ሰሀባዎች አላከበሩትም። እንደዚሁ በተከበረው ዘመን ውስጥ የኖሩት ሰሀባዎችን በመልካም ሲከተሉ የነበሩ ታቢዒዮች አልሰሩትም። እነሱ ደግሞ ከማንም በላይ የሱና አዋቂዎችና ለነቢያችን የነበራቸው ውዴታም ከማንም በላይ እንደነበር እሙን ነው። የነብዩን ፈለግ በሚገባ በመከተልም የማይታሙ እንደ ነበሩ ለማንም ግልፅ ነው። ለኛ አርአያ መሆናቸውም ተነግሮናል። ምንም ሳንጨምር መንገዳቸውን አጥብቀን እንድንይዝ የአላህ መልዕክተኛ አደራ ብለውናል፤
عَلَيْكُمْ بِسُنَّتِي وَسُنَّةِ الْخُلَفَاءِ الرَّاشِدِينَ الْمَهْدِيِّينَ، وَعَضُّوا عَلَيْهَا بِالنَّوَاجِذِ، وَإِيَّاكُمْ وَمُحْدَثَاتِ الْأُمُورِ، فَإِنَّ كُلَّ مُحْدَثَةٍ بِدْعَةٌ، وَكُلَّ بِدْعَةٍ ضَلَالَةٌ
«የእኔን እና የቅን ምትኮቼን ሱና አደራ! በጥርሶችችሁ አጥብቃችሁ ያዙ! አዳዲስ ፈጠራዎችን ተጠንቀቁ (ተከልከሉ)፣ በዲን ውስጥ የተጨመረ ፈጠራ ሁሉ ጥመት ነው» ኢማሙ አህመድ ዘግበውታል
መውሊድ በቀደምቶቹ ዘመን እንዳልነበረ እና ኃላ የተፈጠረ (ሙህደስ) ለመሆኑ መውሊድ አክባሪዎች ሁሉ የማይክዱት እውነታ ነው። መውሊድ ማክበርን ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመሩት ከአራተኛው
ክ/ዘመን በኋላ እራሳቸውን ፋጢሚዮች ብለው ይጠሩ የነበሩት ኡበይዲዩች ግብፅን በ362 ዓመተ ሂጅራ የወራሩ ጊዜ ነበር።
ቀጣዩን ያንብቡ👇
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1336321059824881&id=1003047829818874