+++ሥዕለ እረፍታ ለማርያም+++
በሠዓሊ ኃይለ ማርያም ሽመልስ (በቅዱሳት ሥዕላት ዙርያ አማካሪ፣ ጥናትና ሒስ አድራጊ) 0913 05 2824
++++++++++===+++++++++++
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእረፍት በዓል አደረሳችሁ። ከሥር የእመቤታችን የእረፍትና የግንዘት ታሪክን መሠረት በማድረግ ትውፊቱን ጠብቀው የተሣሉ ጥንታዊያን የብራና፣ የእንጨት ገበታ (ኢቆና)፣ እና የግድግዳ ቤተ መቅደስ ሥዕሎች ቀርበዋል።
የእመቤታችን የእረፍት ሥዕል እንደተሣለበት መደብ እና ያለው የቦታ ስፋት የሚጨመሩ ወይም የሚቀነሱ አካላት አሉበት።
በአጠቃላይ ሲሣል የእመቤታችን ቅዱስ ሥጋ በክብር አልጋ ላይ ሆና (ተቀምጣ / ጋደም እንዳለች)፤
ቅዱስ ነፍሷን ጌታችን በእልፍ አእላፍ መላእክት ተከቦ ሲቀበላት፤
ቅዱሳን ሐዋርያት እያዘኑ ከበዋት መብራት አብርተው፣ መጽሐፍ እያነበቡ እና እያጠኑ፣
ቅዱሳን መላእክት እያጠኑ እና አበባ ይዘው፣
ቅዱሳን ደናግል አዝነው፣
ቅዱስ ዳዊት በገና እየደረደረ፣ ቅዱስ እዝራ በመሰንቆ እያመሰገነ በአጠቃላይ በአስደናቂ መንፈሳዊ ደስታ ይሣላል።
ማስታወሻ፥ የእመቤታችን የእረፍት ሥዕል ላይ ታውፋንያን አስገብቶ መሣል ጸያፍና ተገቢ ያልሆነ ነው። ምክንያቱም ስንክሳር፣ ተአምረ ማርያም ሆነ ሌሎች አዋልድ መጻሕፍት እንደሚነግሩን ታውፋንያ በዚህ በተቀደሰ መንፈሳዊ ስፍራ አስቀድሞ አልነበረም።
ይልቁኑም ወደ መቃብር ስፍራ ቅዱስ ሥጋዋን ሐዋርያት ገንዘውና በከብር በአልጋ ላይ አድርገው እየሔዱ ሳለ በመንገድ የተገናኛቸው። ከዚያም ታውፋንያ ጉዳት አደርሳለሁ ሲል ተቀሰፈ። በእመቤታችን አማላጅነት ደግሞ ካገኘው መከራ ዳነ። በመሆኑም ይህ ተአምር ራሱን ችሎ ከእረፍቷ ሥዕል ቀጥሎ የሚሣል ታሪክ እንጂ የእረፍቷ ታሪክ ላይ አይጨመርም።
ይልቁንም ታውፋንያን የሚያስገባ ተጨማሪ ቦታ ካለ በዚያ ስፍራ በቦታ እጦት የማይሳሉት ቅዱሳን/ት ጨምሮ መሣል ይገባል።
የቤተ ክርስቲያን የሆኑት ቅዱሳት ሥዕላት እንወቅ፣ እንመልከት እና እንጸልባቸው። በስጦታ ይሁን ወይም በስእለት ለቤተ ክርስቲያንም እንስጥ።
ጥንታዊ ቅዱሳት ሥዕላት ለማየት ለማውረድ፣ ለሌሎች ለማጋራት ከፈለጉ
@ethioicons ቤተሰብ ይሁኑ።