"ተቃጠልን'ኮ ባለቤት"
~
ሰውየው እንግዳ ሆኖ ከሰው ቤት ያርፋል። ሚስት የእንግዳው መኖር እንኳ ሳይከብዳት ባለቤቷን ከፍ ዝቅ አድርጋ ታዋርደዋለች። ባል ዋጥ አድርጎ ዝም ይላል። አቶ እንግዳ ግን ራሱን መቆጣጠር አልቻለም። ተነስቶ ሚስትን ከባሏ ፊት ጠፍጥፎ ጠፍጥፎ ለቀቃት። ባለቤት በገዛ ቤቱ ገላጋይ ሆነ።
"ምነው እንግዳ?" አለው ግራ ቢገባው።
"ተቃጠልን'ኮ ባለቤት!" አለ እንግዳው።
.
.
.
አሁን ይህንን ምን አስታወሰኝ? ባንክ ቤት ገብቼ ቁጭ ብያለሁ። አንዷ ልጇን ይዛ ገባች። ልጁ በጣጣጣም የተንቀዠቀዠ ነው። ቤቱን ባንድ እግሩ አቆመው። ሁሉን ነገር አተራመሰው። እናት ወረቀት አንስታ ልትፅፍ ስትል እጇ ላይ ያለውንም ጠረጴዛው ያለውንም በሙሉ መሬት ላይ በተነው። የወደቀውን እንኳ ሳታነሳ ወደሌላሁ ጥግ ሄደች። እዚያም በተመሳሳይ በተነው። እንዲሁ ላመል ያህል "ተው" ትለዋለች። እሱም አይተው፣ እሷም ጠንከር አትል። ከባንኩ ሰራተኛ ዘንድ ሆና አቀፍ አድርጋ ለመፃፍ እየሞከረች ነው። ልጁ አሁንም እየታገለ ነው። ግርርርም አለኝ። ልናገራት አፌ እያደረስኩ ዝም አልኩ።
እኔ ምለው "እኔ በሶፍት እየታሰርኩ በፓስታ እየተገረፍኩ ነው ያደግኩት" የሚሉትኮ ቀልድ ነበር የሚመስለኝ። ይሄ ነገር እውነት ነው እንዴ? እንዴዴዴ! ልጆቻችሁን ቆንጥጡ እንጂ። ይሄን ያህል ጨው አይደሉ! አይሟሙ! አዎ ልጅን ጨካኝ አያያዝ መያዝ አይገባም። ግን ደግሞ አሪፍና ዘመናዊ አስተዳደግ ማለት ልጅን ማጨማለቅ ማለት አይደለም። ኧረ ከፈረንጅና ከዐረብ የምትቀዱትን እየለያችሁ! ይሄ አስተዳደጋቸውን ሁሉ ማበላሸት ነው።
ደግሞም "እንዲህ ሆኜ" "እንዲህ ተደርጌ" ሲሏችሁም ያሉትን ሁሉ አትመኑ። የልጅ ወሬ ይዛችሁ ከሰው ጋር አትጣሉ። አንዱ "ልጄ ተበደለብኝ" ብሎ አስተማሪ ላይ ሽጉጥ እንዳወጣ ሰምቼ በጣም ገርሞኛል። እዚህ ላይ "ከልጁ በፊት አባትን ነበር መቅጣት" ያስብላል። ልጆች የጠየቁትን ሁሉ አትስጡ። ያሉትን ሁሉ አታድርጉ። "አይሆንምን"ም ይወቁ። ህይወት ብዙ "አይሆንም" አላት። እናንተ ብታቀብጧቸው ነገ ብዙ ልትፈትናቸው ትችላለች። ሁሉን የለመደ ትንንሹን ሁሉ እንደ በደል ይቆጥራል። በአንድ ወቅት አንድ ወንድሜ የሚገርም ነገር ነገረኝ። ልጅ እናቱን መኪና እንድትገዛለት ጠየቀ። ገዛችለች። ትንሽ ቆይቶ ሌላ ሞዴል (እንደዛ ነው ኣ የሚባለው?) ጠየቀ። "ይገዛልሃል ግን ትንሽ ቆይ" አለችው፡፡ "አሁን ካልሆነ" ብሎ ፍርጥም አለ። እሷ "አይሆንም" አለች። ገብቶ ራሱን አጠፋ። በቃ! እንደተበደለ ነው የተሰማው።
እና ልጆቻችሁን ለማዘን እንኳ የማይመቹ አታድርጓቸው።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor