የፍቅር ቀን ወይም የአደይ ቀንReposted
"…እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የፍቅር ጀግና ለማድረግ በአገራችን ቫለንታይንስ ደይ እየተባለ የሚከበረውን የፈረንጆች በዓል ተውሰን እንደ አገራችን ፀባይ ለማክበር እቅድ አውጥተን ነበር፡፡
የጦር ጀግኖች ብቻ ሳይሆን የፍቅር ጀግኖች ያስፈልጉናል፡፡
ቫለንታይን ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡ ክፋት የለበትም፡፡ ተቃቅፈው የሚሄዱ ፍቅረኞች ማየት ደስ ይላል፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘው በመንገድ የሚሄዱ ወጣቶች ትዕይንት የሚናፍቅ ነው፡፡ እኔ ወጣት በነበርኩበት ዘመን እንዲህ ማድረግ ያሳፍረን ነበር፡፡ ልጆቻችን በፍቅር እንዲያፍሩ አልፈልግም፡፡ ፍቅርን ከብልግና አምታተናል፡፡
ይሄን ቫለንታይን ቀን በዓል ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ሦስት ነገሮች ማሟላት አስበን ነበር፡፡
አንደኛ ከየትኛውም የአገራችን ክፍል አስገራሚ የፍቅር ታሪኮችን መሰብሰብና ለብሔራዊ በዓል የሚያገለግለንን ነቅሰን ማውጣት፤
ሁለተኛ ምሳሌ የሚሆኑንን የአበባ አይነትና የአበባ ቀለም መምረጥ፤
ሦስተኛ በታዋቂ ገጣሚ፤ ሙዚቀኛና ኮርዮግራፈር በአሉን የሚዘክር በቀላሉ አድማጭ ሊያንጎራጉረው የሚችል ዜማ መስራት ነበሩ፡፡
ከነዚህ ውስጥ ኮሚቴው ለብቻው የሚወስናቸው የበዓሉን ቀን፣ የአበባው ዓይነትና የአበባ ቀለም ሲሆኑ፣ የተቀሩት ዐላማዎች ግን በጥናትና በህብረት ውሳኔ ይፀድቃሉ፡፡
አገራችንን ከአደይ የበለጠ ምን አይነት አበባ ሊወክላት ይችላል?
ከመስከረም ወር የበለጠ ምን የሚያምር ወር አለ?
ቢጫ ቀለምስ ውብ አይደለም?
የአገራችን ስም ከተሰራባቸው ቀለማት አንዱ ዮጵ ትርጓሜው ቢጫ ወርቅ ማለት ነው፡፡
ቢጫ የፀሐይ ብርሃን ነው፡፡ ፀሐይ ከሌለ ሕይወት የለም፡፡ እንደ ፍቅረኞች ፊት የምታበራው ፀሐይ አይደለችም? የተፋቀሩ ሁሉ እየተንቦገቦጉ አይደለ የሚውሉትና የሚያድሩት?
በዚህ ዕለት በአገራችን ያልተለመደ ስርዓት ለማምጣት ሀሳብ አለን፡፡
በዛን በፍቅር ቀን ወይም በአደይ ቀን (ስሙንም በሕብረት እንወስናለን ብለን ነበር) መሳሳም እንዲፈቀድ ከሃይማኖት መሪዎች ከሕግ አዋቂዎች ከወጣቶች ጋር የመነጋገር ሃሳብ ነበረን፡፡ ፍቅረኞች በመንገድ ላይ እዚህ አገር ሲሳሳሙ ታይተዋል? በዛን ቀን መሳሳም አሳፋሪ አይሆንም፡፡
ዓላማችን ወሩ መስከረም ሲሆን ቀኑ በመስከረም አንድ እና በመስከረም ሰባት መሃል ይሆናል፡፡ በዚያን ቀን ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ መልበስና ቢጫ አበባ መያዝ ደንብ እናስደርጋለን፡፡ ቢጫው የተለያየ ቢጫ ሊሆን ይችላል፡፡ በበዓሉ ምሽት ቢጫ ርችቶች በሰፈሮቻችን የምሽት ሰማይ ላይ ይፈካሉ፡፡
ፍቅርን ማክበር ብልግና የለውም፡፡ ፍቅረኞች ቢሳሳሙ ብልግና የለውም፡፡ እየሆነና እየተደረገ መደባበቅ ጨዋ አያደርግም፡፡
በአደባባይ ሰዎች የተጋደሉባቸው ከተሞቻችን መፋቀርን የሚያሳዩ ምልክቶችን ለምን አሳፋሪ እንዳደረጉት አይገባኝም፡፡
ቦንብ ይዘው በሚንጎራደዱበት ከተማ ምናለ አደይ ይዘው ቢተቃቀፉ?
ለምን የፍቅር ዘፈን ሌላ ሰው ሲዘፍንልን ብቻ እንሰማለን? ለምን እኛ ድርጊቱ ውስጥ በአደባባይ አናወጣውም? ላፈቀረን ለፍቅረኛችን ዘፈን ከምንመርጥለት ለምን ባንችልበትም ራሳችን አናንጎራጉርለትም? ያፈቀርነውንስ ይዘን በአደባባይ ለምን ይሄው እዩን አንልም?
ጥላቻን ሳናፍር ያሳየን መውደድ ለምን ያሳፍረናል?"
📖 የስንብት ቀለማት፤ ገፅ 812
@AdamuReta @isrik