የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ 7 ተከሳሾች በሙስና ወንጀል ጥፍተኛ ተባሉ
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታን (ዶ/ር) ጨምሮ ሰባት ተከሳሾች በቀረበባቸው ከባድ የሙስና ወንጀል ጥፍተኛ ተባሉ።
ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች በቀረበባቸው ሁለት ከባድ የሙስና ወንጀል ጥፍተኛ የተባሉ ሲሆን÷ 7ኛ ተከሳሽ ደግሞ በቀረበበት አንድ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ጥፋተኛ መባሉ ተመላክቷል፡፡
ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር)፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ታምሩ ኦኖሌ (ዶ/ር)፣ የአስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ሮባ ደንቢ (ዶ/ር)፣ የቢዝነስና ተቋማዊ ልማት ም/ፕሬዚዳንት አብርሐም ባያብል (ኢ/ር)፣ የግዢ ዳይሬክተር አቶ ሊበይ ገልገሎ፣ የፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ ቦሩ ህርቦዬ፣ የዩኒቨርሲቲው መምህርና የቢኤች ዩ አማካሪ ለታ ድሪባን ናቸው፡፡
በዚህም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር ያሉት ተከሳሾች የዩኒቨርሲቲው አመራርና የማኔጅመንት አባል በመሆን ሲሰሩ የመንግስት ግዢ አዋጅን በመተላለፍ በ2012 ዓ.ም በያዙት ቃለ ጉባዔ መሰረት ሕግን ባልተከተለ መልኩ ያለአግባብ ቢኤች ዩ ለተባለ አማካሪ ግዢው በቀጥታ እንዲፈጸም በማኔጅመንት ውሳኔ ማስተላለፋቸው ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ውል ሲዋዋል ዩኒቨርሲቲውን በመወከል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት 1ኛ ተከሳሽ ውል ሰጪ ሆነው 7ኛ ተከሳሽ ውሉን በመፈረም በ5ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ መሰረት በ1ኛ ተከሳሽ ስም ለተመዘገበው አማካሪ ድርጅት ያለአግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጉን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በመንግስት ላይ ከ196 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ከባድ የሙስና ክስ ቀርቦባቸው ነበር፡፡
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ከሕግ ውጭ በሚሊየን በሚቆጠር ከደረሰው ጉዳት ውስጥ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተመላክቷል፡፡
2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በተመሳሳይ ከ500 ሺህ ብር በላይ ለግል ጥቅም ማዋላቸው የተመላከተ ሲሆን÷ 4ኛ ተከሳሽ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ፣ 5ኛ ተከሳሽ ከ99 ሺህ ብር በላይ፣ 6ኛ ተከሳሽ ከ400 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ በአጠቃላይ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በክሱ ተብራርቷል።
ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች በሁለት ክሶች የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡
በተጨማሪም 7ኛ ተከሳሽ በአንድ ክስ ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን÷ ፍርድ ቤቱ ከ8ኛ እስከ 17ኛ ያሉ ተከሳሾች ላይ ደግሞ በሌሉበት የጥፋተኝነት ውሳኔ በማስተላለፍ የቅጣት አስተያየት ለመቀበል ለመጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የትምህርት በቤቴ ቴሌግራም ገፃችንን JOIN እና ሼር ያድርጉ!
https://t.me/temhert_bebete
https://t.me/temhert_bebete