ክፍል_ 3⃣1⃣
🖋📚 ተከታታይ ጽሁፍ፦ የሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያን ወሳኝ የህይወት ታሪክና ገድል የሚዳስሰው "#ኢብኑ_ተይሚያ_የሱናው_አንበሳ" የተሰኘው መጽሀፍ
[ለ] ከአሕመዲያ ሱፊዮች ጋር ክርክር
ከክ/ል 30የቀጠለ፦
ሪፋዒያዎቹ ብዙ ሆነው ተገኝተዋል። እራሳቸውንና አካላቸውን እያወዛወዙ የተለያዩ ሸይጧናዊ ትእይንቶቻቸውን ማሳየት ጀመሩ። እጅግ ሰፊ ህዝብ ነው የታደመው። ሌላው ሸይኻቸው ዳግም እርቅ ቢወርድ እንደሚሻልና ካለፈው ጥፋት ተውበት ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ ከቢድዐዎቻቸው ተመልሰው ሸሪዐውን ለመከተል ፍቃደኛ እንደሆኑ ተናገረ። ሌላኛው ተነሳና አንገታቸው ላይ ስለሚለብሱት ሰንሰለት ሲከላከል ኢብኑ ተይሚያ ጠንካራ መልስ ሰጡት።
ሪፋዒዩ ሸይኽ፦ የአራቱንም መዝሀብ ቃዲዎች እንድትሰበስብልን እንፈልጋለን። እኛ ሻፊዒዮች ነን።
ኢብኑ ተይሚያ፦ ይሄ በየትኛውም ዓሊም ዘንድ አግባብ አይደለም። እንዲያውም ሁሉም ከዚህ አይነቱ ዒባዳ ይከለክላሉ። እንደ ቢድዐ ነው የሚቆጥሩት። ይሄው ሸይኽ ከማሉዲን ኢብኑ ዘምለካኒ አለ። የሻፍዕያ ሙፍቲ ነው።
“ከማሉዲን! በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ትላለህ?!”
ከማሉዲን ዘምለካኒ፦ ቢድዐ ነው አይወደድም። እንዲያውም የተጠላ ነው።
ሪፋዒዩ፦ “እኛ ዟሂር የሆነውን ሸሪዐ የሚከተሉ ሰዎች የማይቋቋሙት ሁኔታዎችና ማንም የማይገታቸው ስውር ነገሮች አሉን” አለ እየጮኸ።
ኢብኑ ተይሚያ፦ ዟሂር፣ ስውር... የለም! ሁሉም ወደ አላህ ኪታብና ወደ መልዕክተኛው ﷺ ሱንና መመለስ አለበት እንጂ ወደ ሸይኾች ወደ ሱፍዮች፣ ወደ ንጉሶች፣ ወደ አሚሮች፣ ወደ ዑለማዎች፣ ወደ ዳኞች ወይም ወደ ማንም ሊመለስ አይገባም። ይልቁንም ሁሉም ፍጡር አላህንና መልእክተኛውን ﷺ መታዘዝ ግዴታቸው ነው። አምባረቁበት።
ሪፋዒዩ፦ “እኛ ከራማዎች እና እሳት ውስጥ መግባትን የመሰሉ ማንም ጋር የሌሉ ነገሮች አሉን። ስለዚህ ለኛ እጅ መስጠት ይገባል” ብሎ ጮኸ።
ኢብኑ ተይሚያ፦ እኔ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የሚገኝ እያንዳንዱን ሪፋዒ እወራረዳለሁ! የትኛውንም እነሱ በእሳት ላይ የሚሰሩትን ለመስራት ዝግጁ ነኝ። የተቃጠለ ተሸናፊ ነው። ባይሆን በቅድሚያ አካላችንን በኮምጣጤና በሙቅ ውሃ ከታጠብን በኋላ ነው! (በቁጣ ተናገሩ።)
ሪፋዒዩ፦ እሳት ውስጥ መግባት እንደሚችል ተናገረ።
ኢብኑ ተይሚያ፦ “ተነስ” አሉት ደጋግው።
ሪፋዒዩ፦ ቀሚሱን ሊያወልቅ እጁን አነሳ።
ኢብኑ ተይሚያ፦ በጭራሽ! በቅድሚያ በሙቅ ውሃና በኮምጣጤ መታጠብ አለብህ!
ሪፋዒዩ፦ “አሚሩን የሚወድ እንጨት ያቅርብ” እያለ እንዳልሰማ ሆኖ ቀጠለ።
ኢብኑ ተይሚያ፦ ይሄ ነገር ማራዘም፣ ሰውንም መበተን ነው። አላማችንም አይሳካም። ጧፍ ይቃጠልና ከታጠብን በኋላ እኔም እናንተም ጣታችንን እናስገባ። ጣቱ የተቃጠለ የአላህ እርግማን በሱ ላይ ይሁን።
ሪፋዒዩ፦ ፊቱ ተለዋወጠ፣ ተዋረደ።
ኢብኑ ተይሚያ፦ ከዚህም ጋር እሳት ገብታችሁ በሰላም ብትወጡም፣ በአየር ላይ ብትበሩም፣ በውሃ ላይ ብትራመዱም፣ የፈለጋችሁትን ብትሰሩም ሸሪዐን ለመፃረርና ለማፍረስ የምትሰሩትን ስራ ልክ አያደርግላችሁም። ምክንያቱም ትልቁ ደጃልም ሰማይን ”አዝንቢ” ሲላት ታዘንባለች። ምድርን “አብቅይ” ሲላት ታበቅላለች። ፍርስራሽ ምድርን “የተቀበረ ሀብትሽን አውጪ” ሲላት ወጥቶ ይከተለዋል። አንድን ሰው ገድሎ ለሁለት ከፍሎ ከጣለው በኋላ “ተነስ” ሲለው ይነሳል። ይህ ሁሉ ከመሆኑም ጋር ግን ቀጣፊ፣ ውሸታምና እርጉም ነው። የአላህ እርግማን በሱ ላይ የሆነ።
ይህን ማለታቸው በታዳሚው ልቦና ላይ ትልቅ ተፅእኖ አሳድሯል። መሻይኾቻቸው እርቅ ፍለጋ አሚሩን መማፀን ቀጥለዋል። ኢብኑ ተይሚያ ግን ሰዎቹ በእሳት ሊያሳዩ የተጎረሩትን ነገር ያሳዩ ዘንድ ደጋግመው እየወተወቱ ነው። በሃገር ያሉ መሻይኾቻቸው እንዳለ ተገኝተዋል። በጣም ብዙ ናቸው። አደባባዩ በህዝብ ጩኸት እየተናጠ ነው። ህዝቡ እንዲህ እያለ ያስተጋባል፦
{فَوَقَعَ الْحَقُّ وَبَطَلَ مَا كَانُوا يَعْمَلُونَ (١١٨) فَغُلِبُوا هُنَالِكَ وَانقَلَبُوا صَاغِرِينَ (١١٩)}
“እውነቱ ተገለፅ! ይሰሩት የነበሩትም (ድግምት) ከንቱ ሆነ!! እዚያ ጋ ተሸነፉ!! ወራዶችም ኾነው ተመለሱ!!” [አልአዕራፍ፡ 118-119]
ሪፋዒዮቹ፦ እጅጉን ተሸማቀቁ። ትላንት ሲያረግድላቸው የነበረው ህዝብ ፊት ተዋርደው እየተሳለቀባቸው ነው። አለመቻላቸውና አጭበርባሪነታቸው ሲደግፏቸው ለነበሩት አሚሮች ጭምር ይፋ ሲሆን ጊዜ አፈገፈጉ። ስላለፈው ሁሉ ተውበት ጠየቁ።
አሚሩ፦ ከነሱ ምን ትፈልጋለህ?
ኢብኑ ተይሚያ፦ ቁርኣንና ሱንናን መከተል። ከመፃረርም መመለስ። ለምሳሌ ቁርኣንና ሐዲሥን መከተል በነሱ ላይ ግዴታ እንዳልሆነ ከማመን መመለስ። ለማንም ከቁርኣንና ከሱንና የመውጣት መብት እንደሌለው እንዲታመን።
ሪፋዒዮቹ፦ በቃ ቁርኣንና ሱንናን አጥበቀን ይዘናል። አንገታችን ላይ ከምናጠልቀው ሰንሰለት ውጭ በኛ ላይ የምትቃወመው ነገር አለህን? ይሄው እናወጣለን!
ኢብኑ ተይሚያ፦ እነዚህም ይሁኑ ሌላ ባጠቃላይ ሁሉም ሙስሊም ለአላህና ለመልእክተኛው ﷺ ትእዛዝ ታዛዥ የመሆን ግዴታ አለበት።
አሚሩ፦ ምንድን ነው ከቁርኣንና ከሱንና የሚጠበቅባቸው?
ኢብኑ ተይሚያ፦ ከቁርኣንና የሱንና ህግ ብዙ ነውና በዚህ መድረክ ላይ መዘርዘር አይቻልም። ነገር ግን የተፈለገው ባጠቃላይ ለዚህ ተገዥ እንዲሆኑ ነው። ከዚህ የወጣ አንገቱ ይቀላ።
አሚሩ፦ በጣቱ ወደ ህዝቡ እያመላከተ አፅንኦት ሰጠው። አላማው ህጉ ሁሉንም ህዝብ የሚመለከት ነው ለማለት ነው።
የሰዎች ሞራል የተነቃቃበት ትልቅ ጉባኤ ነበር። አማካሪዎች፣ ዑለማዎች፣ አሚሮች፣ ባሉበት ከቁርኣንና ከሱንና ያፈነገጠ በሰይፍ አንገቱ ሊቀላ ተወሰነ። “ይቀጥላል!”
___
📖ኢብኑ ተይሚያ የሱናው አንበሳ ከገፅ 88 እስከ 91
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
~~~ #በአላህ_ፍቃድ_ይቀጥላል~~~
✍️ዐብዱልከሪም ሰዒድ
📆[እሑድ] #ሶፈር 9 1442 ሂ. #መስከረም 17 2012 ዓል #Sep 27 2020 GC.
📕ዝግጅት፦ ሙሐመድ አሕመድ ሙነወር
📝#ሼር በማድረግ ሌሎችን ያስነብቡ!
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
📣የቴሌግራም ቻናላችንን ጆይን ያድርጉ፦
https://t.me/AbubilalIbnuseid