በሥጋ መጣ
ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መጣ ማለት በሥጋ ሳይመጣ በፊት ያለ ሥጋ ነበረ፤ ኋላ ግን በሥጋ መጣ ማለት ነው። በሥጋ ሳይመጣ በፊት ያለ ሥጋ ነበረ፤ ቃል ነበረ፤ መለኮት ነበረ። በሥጋ ሲመጣ ደግሞ መለኮትን ሳይተው ሥጋን ጨመረ።
ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ሲመጣ፥ ካለመኖር ወደ መኖር አይደለም የመጣው። ከመኖር ወደ መኖር ነው የመጣው። መለኮት ብቻ ሆኖ ከቀድሞው ለዘላለም መኖር፥ መለኮትም ሰውም ሆኖ በአንድ አካል ከመጣበት ወዲህ ለዘላለም ወደ መኖር ነው የመጣው።
ይህንን በሥጋ መምጣቱን የማይቀበል፥ የማያምን፥ የማይታመን ሁሉ፥ ኢየሱስ መለኮት አይደለም፤ ሰው ብቻ ነው፤ የሚል ሁሉ፥ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ እርሱ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው።
የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። 1ዮሐ. 4፥2-3
ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው። 2ዮሐ. 7