የጌታን እናት ማርያምን የሚመለከት ውዝግብ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ተነሥቶ እንደ ነበር ይታወሳል። የጉዳዩ ምንጭ ወዳጄ ዘላለም መንግስቱ ሲሆን፣ ይኸውም ማርያም ወላዲተ አምላክ አይደለችም የሚል ነው። ብዘገይም እንኳን አንዳች ነገር ማለት እንዳለብኝ አስቤያለሁ። በአጭሩ ለመናገር፣ ይህ ሙልጭ ያለ ስሕተት ነው። አዲስ አስተምህሮን በ21ኛው መቶ ክ/ዘ ለማምጣት ካልሆነ በቀር የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ይህን ትምህርት አታውቀውም።
የማርያም ወላዲተ አምላክነት በጥንት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጥያቄ አስነሥቶ ተገቢ ማብራሪያና ውሳኔ ተሰጥቶበታል። በርግጥ ጉዳዩ የተነሣው ስለ ኢየሱስ እንጂ ስለ ማርያም ተብሎ አልነበረም። ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት ማለት፣ ኢየሱስ አምላክ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ አምላክ ሆኖ፣ እናቱ ወላዲተ አምላክ ካልሆነች፣ ኢየሱስ አምላክ የሆነው ከተወለደ በኋላ ነው ማለት ይሆናል። ኢየሱስ ግን አምላክ ያልነበረበት ቅጽበት አልነበረም፤ ከዘላለምም።
እግዚአብሔር ወልድ በድንግል ማርያም ማሕፀን ያደረው አምላክነቱን ሳይተው ነው። እናም ማርያም አምላክም ሰውም የሆነውን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ወልዳለች። ስለዚህ እምዬ ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት። አምላክ በሥጋ ሲወለድ ወልዳዋለችና። ይህ እንግዲህ የኢየሱስን አምላክነት በሚመለከት የሚነሣ ጉዳይ ነው።
የኢየሱስ ሰው-ነት ሲነሣ ደግሞ፣ ሰው መሆኑን ለማስረዳት ማርያም ወላዲተ ሰው መሆኗን መናገር ይቻላል። ወላዲተ አምላክ-ሰው፣ ወላዲተ ክርስቶስ ልንላትም እንችላለን። እነዚህን ሁሉ ስንናገር ግን ወላዲተ አምላክ መሆኗን ሳንክድ መሆን አለበት።
(ዘላለም ያነሣውን ጉዳይ ከሰሞኑ እንደምመለስበት በማሰብ ወደ ሌላ አጠቃላይ ጉዳይ ልለፍ።)
* * *
ለመሆኑ፣ ሰዎች በቅዱሱ መጽሐፍም በቤተ ክርስቲያን ጉባኤም ተነግሮ ያለቀለትን ነገር ለምን ይክዳሉ?
አንድም፣ ባለማወቅ ነው። አላዋቂው ለመማር የተዘጋጅ ልቡና ካለው ይህ ዕዳው ገብስ ነው። በማስተማር መፍትሔ ማግኘት ይቻላል።
አንድም፣ ትኩረትን ፍለጋ ነው። እንዲህ ዐይነቱን ትኩረት የተጠማ ችላ ከማለት በቀር ሌላ መፍትሔ ለጊዜው አልታየኝም።
አንድም፣ አንድን ጽንፍ ለመቃወም፣ ሌላ ጽንፍ መርገጥ ነው። ከኦርቶዶክስ ወገኖች የሚመጣ ቅድስት ማርያምን የሚመለከት ስሁት አስተምህሮ አለ። ከዚህም የተነሣ ወንጌላውያን ያን ስሕተት ሽሽት ሌላ ስህተት ውስጥ የሚገቡባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ፣ “የተሰቀለው የማርያም ሥጋ ነው” የሚል ትምህርት ሲገጥማቸው፣ “ኢየሱስ ከድንግል ማርያም ሥጋ አልነሣም (የሰውነትን ባሕርይ ከማርያም አልተካፈለም)” ሲሉ ኖረዋል። ስሕተትን በስሕተት ማረም ግን ከቶ የሚቻል አይደለም፤ ሁለት ስህተት አንድ እውነት አይሆንምና! ጌታ ኢየሱስ የሰውነትን ባህርይ የተካፈለው ከእናቱ ስለ መሆኑ በቅዱስ መጽሐፍም በቤተ ክርስቲያን ትውፊትም የተረጋገጠ ነው። በተጨማሪም፣ የእኔ ሥጋ የእኔ እንጂ የእናቴ እንዳልሆነ ሁሉ፣ የኢየሱስም ሥጋ የኢየሱስ እንጂ የማርያም አይደለም። ስለዚህ የተሰቀለው የማርያም ሥጋ ሊሆን አይችልም። ለነገሩማ፣ የተሰቀለው ኢየሱስ እንጂ ሥጋው አይደለም።
ስለዚህ ማርያምን የአምላክ ምንጭ፣ መገኛ፣ እርሷ ባትኖር ኖሮ አምላክ እንደማይኖር የሚናገር ጤና ቢስ አስተምህሮን ሽሽት፣ ማርያም ወላዲተ አምላከ መሆኗን መካድም ስሕተትን በስህተት ለማረም የሚደረግ የማያዋጣ ሙከራ ነው። በአንዳንድ ዐቃብያነ እምነት ዘንድ፣ የሚቃወሙትን አሳብ ለመርታት እስካገዘ ድረስ ለልከኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጓሜና ለትክክለኛ ትውፊት ግድ አለመሰኘት መስተዋል ከጀመረ ግን ከራራመ። እንዲህ ዐይነቱ አካሄድ በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በመጻሕፍት ላይ፣ ከዊልያም ሌን ክሬይግ እስከ እኛዎቹ እነ እንቶኔ ድረስ እየተስተዋለ ነው።
ዕቅበተ እምነት ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ከልከኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጓሜ ይልቅ እንዴትም ብለው ወደረኞቻቸውን ለማሽነፍ ቅድሚያ በመስጠት ከቀጠሉ፣ ርቱዕ አስተምህሮን በሚመለከት የእነርሱን ምልከታ ወደማንቀበልበት እንዳንደርስ እሠጋለሁ።
https://www.facebook.com/PaulsPulpit/posts/652743893948488