👉 የኢኽዋን መሪዮች የመጅሊስ እንጂ የሀገር መሪዮች አይደሉም ።
የሀገራችን የኢኽዋን መሪዮች የስልጣን ጥማት በቀን ቁጭ ባሉበት እንዲቃዡ አድርጓቸዋል ። ቅዠቱ በርግጥ በውስጣቸው ሲያልሙት የነበረ መሆኑን ያመላክታል ። የእነዚህ አካላት የቀን ቅዠት ልክ እንደ አንድ በረንዳ አዳሪ ነው ። በቀን ጎዳና ላይ ቁጭ ብሎ እርጥብ እሳት ( ጫት) እየበላ የምርቃናው ሙቀት በሁለመናው ሲሰራጭ በምናቡ የመዋኛ ቦታ ፣ ሜዳ ቴኒስ ፣ የልጆች መጫወቻ ባለው በተንጣለለ ጊቢ ላይ በተሰራ ቪላ ውስጥ ራሱን አስቀምጦ በሐሴት ማእበል ሲናወጥ ምርቃናው እንደጠፋበት አምሳያ ነው ።
እነዚህ የሀገራችን የኢኽዋን መሪዮች ለስንት አመት ሲመኙት የነበረውን የመጅሊስ ስልጣን ላይ ሲወጡ የተሰማቸው ሙቀት የሰራ አካላታቸውን ሲቆጣጠረው ቁጭ ብለው የሀገር መሪ ሲሆኑ በቀን በተቀመጡበት በምናብ ዐለም ማየት ጀምረዋል ። የሚገርመው ይህ ህዋ ላይ የሚያንሳፍፋቸው ቅዠት ወደ መሬት ለማውረድ ቆርጠው ተነስተው ማስፈራራት ጀምረዋል ።
ከዚህ በፊት ሐረር ላይ በነበራቸው ጉባኤ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በሱ " የስልጣን ግዛት " ውስጥ ሰለፍይ የሚባል ነገር መስማት እንደማይፈልግ በመግለፅ ሰለፍዮች ወደዱም ጠሉም በአሁኑ ሳአት እዚህ ሀገር ላይ ( ኢትዮዽያ ላይ ) የሙስሊሙ መንግስት እሱ መሆኑን አውጇል ።‼
ገርሞ ገርሞ ይገርማል ። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንደሚሉት ወይም ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ነው ነገሩ ። ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ፣ የሙስሊሞች መሪ ፣ ከዶ/ር አብይ አሕመድ ደግሞ የክርስቲያኖች መሪ እንዲሆኑና ኢትዮዽያ በሁለት መንግስታት እንድትመራ የተስማሙ ይመስል ። ይህን የሐጂ የቀን ቅዠት በተለይ ኦሮምኛ የምትሰሙ በሚከተለው ሊንክ ገብታችሁ አድምጡ :–
https://drive.google.com/file/d/1VZSVRvGK0tOrUTiP4z7vJXz_Mx28Qqi4/view?usp=drivesdk በዚህ ቅዠቱ ላይ በሚገርም መልኩ ሰለፍዮችን ያስፈራራል ። ውሀ ዝም ብሎ ሲሄድ የተኛ ይመስላል እንደሚበላ ሰው አያውቅም የሚል ምሳሌ አምጥቶ ዝም ስላልኩ የማላውቅ አይምሰላችሁ አጠፋችሇለሁ ይላል ። ‼
እኛ የምንለው መጀመሪያ ዙፋኑን አረጋግጥና ከዛ በኋላ ዛቻውን አምጣ ነው ። አሁንም የምንለው አንተ የአንድ ተቋም መሪ እንጂ የሀገር መሪ አይደለህም ነው ። እንደሙስሊም በቁርኣንና በሐዲስ በሶሓቦች አረዳድ እንደ ሀገር ደግሞ በህገ መንግስቱ ነው የምንመራው ። አንተም እኛም በህገመንግስቱ እኩል ነን ።
ከኢስላም ሊቃውንቶች ጥበበኛ ንግግር አንዱ " ልኩን ያወቀን አላህ ይዘንለት " የሚል ነው ።
ይህ የቀን ቅዠት በሱ ላይ ብቻ አላበቃም ዶ/ር ጀይላንም የአሕባሽ ሱፍይና ኢኽዋን ጥምር የሆነው የዑለማእ ፈታዋ ያልተቀበለ ኻሪጅይ ነው ( በመንግስት ላይ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ የወጣ ) ነው ብሎ የጓደኛውን የማይጨበጥ ምናብ አጠናክሯል ።
👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆
🔹 ይህ ከላይ ያለው ፁሑፍ ግንቦት 2016 ላይ ተፅፎ የነበር ሲሆን ኢኽዋኖችን በተለይ የመጅሊሱን አመራሮች ያበሳጨ ነበር ። አሁንም የምንለው የኢኽዋን ( የመጅሊስ ) አመራሮች የሙስሊሙ መንግስት አይደሉም ። ኢትዮዽያም በሁለት መንግስት እየተመራች አይደለም ። ነገር ግን ከመንግስት ጋር ሲጠጉ እውነተኛ የሀገር ተቆርቋሪ የህዝቡን ሰላም አስጠባቂ መስለው ከመንግስት ጋር ሲጋጩ ወይም መንግስት ፊት ሲነሳቸው ለግል ጥቅማቸው ህዝቡን ከዳር እስከዳር ቀስቅሰው ሀገር እንዲታመስ የሚያደርጉ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባዮች መሆናቸውን መግለፅ በተለይ ለምስኪኑ ተከታይ በጣም አስፈላጊ ነው ። ታዲያ ከላይ የተጠቀሰውን የሀገር መሪነት የምናብ ስካርና ሰለፍዮችን የማሸማቀቅ ጥማታቸው በፊት ለፊት ሳይሆን በመሰሪ አካሄድ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቆፉሩት ጉድጓድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ። ለዚህ ዋነኛ መሳሪያቸው ሰለፍዮችን የሀገር ስጋት የሰላም ፀር እንደሆኑ አደርገው ለመንግስት ባለስልጣናት በማቅረብ ወደ አላማቸው መድረስ ትልቁ ስራቸው አድርገው ይዘውታል ። ይሁን እንጂ ደመናው በፀሀይ እንደሚገፈፈው ሁሉ እነዚህ አካላት በሰለፍዮች ላይ የሚለጥፉት የስም ማጥፋት ታፔላ ተነስቶ እውነታው ፍንትው ማለቱ አይቀርም ።
ስሙን ለሰው አወረሰው እንዲሉ ኢኽዋኖች የራሳቸውን ማንነት ለሰለፍዮች በመስጠት ስማቸውን ለማጠልሸት መሞከር በምንም መልኩ የእነርሱን እኛ የሙስሊሙ መንግስት ነን የሚለውን ምኞት አያሳካም ። ለጊዜው ለመንግስት የተሳሳተ ምስል በመስጠት የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስድ ሊያደርጉ ይችላሉ ። ነገር ግን ይህ ማለት መንግስትን አዘዙ ወይም ከመንግስት በላይ ሆኑ ማለት አይደለም ። ይልቁንም ማንነታቸውና ድብቅ አጀንዳቸውን እንዲረዳ ነው የሚያደርጉት ። እንኳን ሀገር የሚመራ መንግስት አንድ የቤት አባ ወራም ቢሆን እገሌ እኮ በጣም አደገኛ ነው ካልከው ከሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ቆም አድርጎ በራሱ መንገድ ማንነቱን ያጣራል ። በመጨረሻም ታማኝነቱና እውነትኝነቱን ሲያረጋግጥ በተቃራኒው ያንተን ድብቅ ፍላጎት ለማወቅ ፊቱን ማዞሩ አይቀርም ።
በመሆኑም የኢኽዋኖች ሰለፍዮችን የማጠልሸት እንቅስቃሴ ለሰለፍዮች ክብርን እንጂ አይጨምርላቸውም ። ሌላው ኢኽዋኖችና የእንጀራ ልጆቻቸው ሊያውቁት የምንፈልገው ሰለፍዮች በመለኮታዊ ቃል የሚመሩ መሆናቸውና ከማንም ምንም ነገር ቢደርስባቸው በመለኮታዊው የሕይወት መመሪያ የአላህ ቃልና በነብዩ ንግግር መዝነው ተግባራዊ የሚያደርጉት መሆኑን ነው ። በስሜት ፈረስ እየጋለቡ ለግል ጥቃማቸው ወጣቱን ከጎናቸው አሰልፈው ሀገር የሚያምሱ አይደሉም ። ስለዚህ አትድከሙ ህልማችሁ አይሳካም የአላህ ቃል የበላይ ይሆናል እንላቸዋለን ።
https://t.me/bahruteka