፪
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ እውነተኛ ጾም፤ ስለ ሐሜት...በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ፦
እየተናገርሁ ያለሁትም ስለ እውነተኛ ጾም ነው እንጂ ብዙዎች እንደሚጾሙት ያለውን ጾም አይደለም፡፡ እየተናገርሁ ያለሁት ከኃጣውእም ጭምር ስለ መከልከል ነው እንጂ ከጥሉላት ብቻ ስለ መከልከል አይደለም፡፡ የጾም ጠባይዋ እንደዚህ ነውና፤ “በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢኾን እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል የድሉን አክሊል አያገኝም" እንደ ተባለ እንደሚገባው አድርገው ካልጾሙ በቀር የሚተገብሯትን አታድናቸውም (2ኛ ጢሞ.2፡5)፡፡
በመጾም እየደከምን ሳለ የጾም አክሊልን ካላገኘን እንዴትና በምን ዓይነት አኳኋን ይህን ልንፈጽመው እንደሚገባው ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡ ፈሪሳዊዉም ጾሞ ነበርና፤ ከዚያ በኋላ ግን ወደ ቤቱ የኼደው ባዶ እጁንና የጾሙን ፍሬ ሳያገኝ ነውና (ሉቃ.18፥12)፡፡ ቀራጩ ደግሞ በአንጻሩ አልጾመም ነበር፤ ነገር ግን ከጾመው ፈሪሳዊ ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው እርሱ ነው፡፡ ይህም የኾነበት ምክንያት [ቀራጩ ባይጾምም ተጠቀመ፤ በመፃዒ ሕይወቱም ጾም አላሻውም ለማለት ሳይኾን ከተአምኖ ኃጣውእ ጋር] ሌሎች ግብራት ካልተከተሏት በቀር ጾም ረብ ጥቅም እንደሌላት [እና ትሕትና የጾም አጣማጅ መኾኑን/ የምትሠምረው ከትሕትና ጋር መኾኑን] እንድታውቅ ነው፡፡
የነነዌ ሰዎች ጾመዋል፤ የእግዚአብሔር ምሕረትንም አግኝተዋል (ዮና.3፥10)፡፡ እስራኤላውያንም ጾመው ነበር፤ ነገርግን እያጉረመረሙ ተመለሱ እንጂ በመጾማቸው አንዳች ጠቀሜታን አላገኙም (ኢሳ.58፥3-7፣ 1ኛ ቆሮ.9፥26)፡፡ ስለዚህ እንዴት መጾም እንዳለባቸው ለማያውቁ ሰዎች የጾም ጉዳቱ ትልቅ ነውና በጥርጣሬ እንዳንኼድ፣ እንዲሁ አየርን እንዳንደልቅ፣ እንዲሁ ከጨለማ ጋር እንዳንጋደል ይህን የምናከናውንባቸውን ሕጎች ልንማር ያስፈልገናል፡፡
ጾም መድኃኒት ናት፡፡ አወሳስድዋን በትክክል ላላወቁ ግን ጥቅም የላትም፡፡ ይህችን መድኃኒት የሚወስድ ሰው በየስንት ሰዓቱና በምን ያህል መጠን እንደምትወሰድ፣ ለምን ዓይነት በሽታ እንደምትጠቅም፣ በየትኛው አከባቢና የአየር ኹናቴ እንደምትወሰድ፣ ከእርሷ ጋር የሚኼዱና የማይኼዱ ምግቦችን እንዲሁም ከእርሷ ጋር የማይስማሙ ሌሎች ነገሮችን ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብቶ የማይወስዳት ሰው ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ታመዝንበታለች፡፡ አንድ በሐኪም የታዘዘልንን የደዌ ዘሥጋ መድኃኒት እንዲያሽለን ስንፈልግ በጥንቃቄ ልንወስደው ያስፈልጋል፤ የነፍሳችንን ደዌና በአእምሮአችን ውስጥ ያሉ ቁስሎችን ለመፈወስ ብለን በምንወስደው መድኃኒት ደግሞ ከዚህ የበለጠ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ይቀጥላል....
(ትምህርት በእንተ ምክንያተ ሐውልታት፣ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ገጽ 79-96 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)