፬
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ እውነተኛ ጾም፤ ስለ ሐሜት...በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ፦እየጾምክ ነውን? እንግዲያውስ መጾምህን በተግባር አሳየኝ! "እንዴት አድርጌ ላሳይህ?" ነው ያልከኝ? ድኻው እርዳታህን ፈልጎ እንደ ኾነ ቸርነትን አድርግለት! የጠላኸውን ሰው ስታየው ፈጥነህ ታረቀው! ባልንጀራህ ክብርን አግኝቶ ስታይ አትቅና! መልከ መልካም ሴትን ስታይ ለዝሙት ሳትመኛት እንዲሁ አልፈሃት ኺድ! አፋችን ብቻ ሳይኾን ዓይናችንም፣ ጆሮአችንም፣ እግራችንም፣ እጃችንም፤ በአጠቃላይ የሰውነታችን ሕዋሳት በሙሉ ሊጾሙ ይገባልና፡፡
እጆች ከንጥቂያና ከንፉግነት ይጹሙ፡፡ እግሮች የኃጢአት ትርኢቶችን ለማየት ከመፋጠን ይጹሙ፡፡ ዓይኖች በውጫዊ ውበት ላይከመተከል ወይም እንግዳ በኾነ መልኮች ምክንያት ከመቅበዝበዝ ይጹሙ፡፡ ማየት የዓይኖች ምግብ ነውና፤ እናም የሚታየው ነገር ክፉ ወይም ሥርዓት የለሽ ከኾነ ጾምን ያረክሳል፤ ነፍስንም ያውካል፡፡ የሚታየው ነገር በጎ ከኾነ ግን ጾምን የሰመረች ያደርጋታል፡፡ በጾም ምክንያት ነውር ከሌለባቸው ምግቦች ተከልክለን ሳለ በዓይኖቻችን ነውር የኾኑትን ነገሮች የምንነካ ከኾነ እጅግ ሞኝነት ነው፡፡ ሥጋን ከመብላት ተከልክለሃልን? እንግዲያውስ በዓይኖችህ አድርገህ አመንዝራነትን ሴሰኝነትን አትብላ፡፡ ጆሮም ይጹም፡፡ የጆሮ ጾምም “ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል" እንዲል ሐሰተኛ ወሬንና ሐሜትን አለመስማት ነው (ዘጸ.23፡1)፡፡
አንደበትም ከከንቱ ንግግሮችና ከዘለፋ ይጹም፡፡ አዕዋፋትንና™ ዓሦችን ከመብላት ተከልክለን ሳለ ወንድሞቻችንን ግን የምንነክሳቸውና የምንበላቸው ከኾነ ምን ጥቅም አለው? ክፉ የሚናገር እርሱ የወንድሙን ሥጋ ይበላል፤ የባልንጀራዉንም ሰውነት ይነክሳል፡፡ እንዲህም በመኾኑ ተወዳጅ ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ" በማለት አስፈሪ ኃይለ ቃልን ተናግሯል (ገላ.5፥15)።
ጥርስህን በሥጋው ላይ አላኖርህም፤ ሐሜትህን በነፍሱ ላይ ተክለህ ግን ቁስሉ ክፉኛ እንዲዛመት አድርገሃል፡፡ በሺሕ መንገዶችም ራስህንና ወንድምህን እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሰዎችን ጎድተሃል፡፡
ባልንጀራን በማማትህ ሐሜትህን የሚሰማ ሰው ይበልጥ እንዲያማ አነሣስተኸዋልና፡፡ እንዴት ያልከኝ እንደኾነም፦ ቀድሞም ቢኾን ክፉ ሰው ከነበረ አሁን ደግሞ በክፋቱ ሌላ ተባባሪ ሲያገኝ ይበልጥ ግድየለሽ ይኾናልና፡፡ ሐሜትህን የሚሰማ ሰው ጻድቅ ከኾነ ደግሞ ይታበያል፤ ይኮፈሳል፤ የሌሎች ሰዎችን ኃጢአት ሲሰማ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋልና፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም” ቤተ ክርስቲያንን በአጠቃላይ ትጎዳለህ፡፡ ይህን የሚሰሙህ ሰዎች ኃጢአተኛ ነው ብለው የሚያስቡት አንተ የነገርካቸውን ሰው ብቻ ሳይኾን አጠቃላይ ክርስቲያኖችን ወደ መንቀፍም ይፋጠናሉና፡፡
ኢ-አማንያኑ “እገሌ'ኮ ዘማዊ ነው፤ ወይም ባለጌ ነው" በማለት ብቻ አያቆሙም፤ ስለዚያ አንድ ኃጢአተኛ ሰው ከመናገር ይልቅ ክርስቲያኖችን በአጠቃላይ ይነቅፋሉ እንጂ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የእግዚአብሔር ክብር እንዲነቀፍ አድርገሃል፤ እኛ በጎ ምግባር ሲኖረን እንደሚከብር ኹሉ ኃጢአት ስንሠራ ደግሞ ይነቀፋልና፤ ይሰደባልምና!
አራተኛ ምክንያት ደግሞ የምታማውን ሰው አዋርደኸዋል፤ አንተን እንዲጠላህ ስላደረግኸውም ከቀድሞ ይልቅ ይበልጥ ሐፍረት የለሽ እንዲኾን አድርገኸዋል፡፡ አምስተኛ በማይመለከትህ ነገር ራስህን በመክተትህ በራስህ ላይ ፍርድን አከማችተሃል። ስለዚህ አንድ ሰውስ እንኳን፦ “የምናገረው ነገር ሐስት ከኾነ ሐሜተኛ ነኝ፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ሐሜተኛ አይደለሁም" ብሎ አይንገረኝ፡፡ ምንም እንኳን የምትናገረው ነገር እውነት ቢኾንም ይህም ቢኾን ክፉ ነው፤ ወንጀል ነው:: ያ ፈሪሳዊው ሰው ስለ ቀራጩ እውነት የኾነውን ነገር ተናገረ፤ ነገር ግን እንዲህ ስለ ተናገረ ምንም ጥቅም አላስገኘለትም፡፡
እስኪ ንገረኝ! የኋለኛው ሰውዬ ቀራጭና ኃጢአተኛ አልነበረምን? ቀራጭ እንደ ነበር ለማንም ሰው ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ፈሪሳዊው ሰው ወንድሙን በማማቱ ምክንያት ከቤተ መቅደሱ አንዳች ረብን ሳያገኝ ተመለስ፡፡
ወንድምህን ማስተካከል ትፈልጋለህን? አልቅስለት፤ ወደ እግዚአብሔር ጸልይለት፡፡ ብቻዉን ወስደህ ገሥጸው፤ ምከረው፤ ለምነው! ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ አድርጓል፡- “እንደገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ" (2ኛ ቆሮ.12፥21)።
ለኃጢአተኛው ፍቅርህን አሳየው፡፡ ለብቻው አድርገህ ስትገሥጸው፤ ስትመክረውና ስትለምነው ከኃጢአቱ እንዲመለስ ካለህ እንክብካቤና ጉጉት እንጂ እርሱን ከማጋለጥ አንጻር እንዳልኾነ አሳምነው፡፡ ስለዚህ በትክክል ከያዘው ደዌ እርሱን መፈወስ ፈልገህ ከኾነ እግሩን ያዘው፤ እቀፈው፤ ይህን ስታደርግም ምንም ምን አትፈር፡፡ ሐኪሞችም ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ያደርጋሉ! ታካሚዎቻቸው መድኃኒትን መውሰድ የማይፈልጉ ከኾነ እያቀፉአቸውና እየለመኑአቸው ቆይተው በኺደት ጠቃሚዉን መድኃኒት ይሰጡአቸዋል፡፡ አንተም እንደዚህ አድርግ፡፡ ቁስሉን ለካህን እንዲያሳይ አበረታታው፤ ልክ እንደ ሐኪሙ ኃጢአተኛዉን የሚንከባከበው፤ መድኃኒቱን የሚስጠው፣ ስለ መዳኑም እጅግ የሚጓጓው እርሱ ነውና፡፡
ይቀጥላል....
(ትምህርት በእንተ ምክንያተ ሐውልታት፣ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ገጽ 79-96 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)