፭
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ እውነተኛ ጾም፤ ስለ ሐሜት...በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ፦
ሐሜተኞችን ብቻ ሳይኾን ሌሎች ሰዎች ሲታሙ “እህ” ብለው የሚያደምጡትንም ጭምር ጆሮአቸውን እንዲዘጉ፣ “ወንድሙን በስውር የሚያማን እርሱን አሳደድሁ" ብሎ የተናገረውንም ነቢይ እንዲመስሉት እመክራለሁ (መዝ.100፥5)፡፡
ባልንጀራዉን ለማማት ብሎ ወደ አንተ የመጣውን ስው እንዲህ በለው፡- “ስለ እርሱ መልካም ነገር የምትናገርለት አሊያም ደግሞ የምታመሰግነው ሰው አለህን? ይህን በጎ መዓዛ ያለውን ዘይት ለመቀበል ጆሮዬን እከፍታለሁ፡፡ ክፉ ንግግርን የምታወራ ከኾነ ግን ቃሎችህ ወደ ጆሮዬ እንዳይገቡ እከለክላቸዋለሁ፤ ይህን ፍግና ቆሻሻ ወደ ጆሮዬ ለማስገባት አልፈቅድምና፡፡
ወንድምህ ክፉ መኾኑን ብትነግረኝ ግን ምን ይረባኛል? ይልቁንም እንዲህ ስታደርግ ራሴን እንድጎዳና ያለኝን እንዳጣ ታደርገኛለህ፡፡ ስለዚህ ስለ ወንድማችን ጥፋት ከምናወራ ይልቅ ስለ ራሳችን ኃጢአት እንጨዋወት! የሠራናቸውን መተላለፎች እንዴት ይቅርታ እንደምናገኝባቸው እንጨነቅ፣ ስለ ራሳችን ሕይወት እንደዚህ ያለ ትጋትና ምክክር እናሳይ፡፡
እስኪ ንገረኝ! ስለ ራሳችን ጉዳዮች ምንም ሳናስብ የሌሎች ሰዎችን ኃጢአት ለመመርመር እንዲህ በመፈለጋችን የምናገኘው ይቅርታ ወይም የሚደረግልን ምሕረት እንደ ምን ያለ ነው?! 'ሰው ቤት እንዲሁ ዘው ብሎ ገብቶ መመርመርና ቤቱ ውስጥ ምን ምን እንዳለ መበርበር ወራዳና እጅግ አሳፋሪ ተግባር እንደ ኾነ ኹሉ፥ የሌላ ስው ሕይወት ምን እንደሚመስል መመርመርም እንደዚሁ የመጨረሻው የጨካኝነት ደረጃ ነው፡፡
ከዚህ ኹሉ የከፋው ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሕይወትን የሚኖሩና የራሳቸውን ጉዳይ የረሱ ሰዎች፥ ይህን ሐሜታቸውን የሚነግሩትን ሰው ለሌላ ሰው እንዳይናገር መለመናቸውና መማጸናቸው እነርሱ እንደዚህ መናገራቸው ግን ተግሣጽ እንደ ኾነና ተገቢ ሥራን እንደ ሠሩ አድርገው ማሰባቸው ነው፤ ይህን ለሌላ ስው እንዳይናገር የምትማጸነው ከኾነ፡ አስቀድመህ እነዚህን ነገሮች ከመናገር ልትቈጠብ አይገባህም ነበርን? ጉዳዩ በአንተ እጅ እያለ ምሥጢሩ የተጠበቀ ነበር፤ አሁን ካጋለጥከው በኋላ ግን ለምሥጢሩ መጠበቅ አብልጠህ የምትተጋ ኾንክ፡፡ የሰማህ ሰው ለሌላ ሰው እንዳይናገር የምትፈልግ ከኾነ አንተው ራስህ ቀድመህ አትንገረው፡፡ የጉዳዩን ምሥጢራዊነት ለሌላ ሰው ከገለጥክ በኋላ የነገርከውን ነገር ምሥጢር እንዳያወጣ ብለህ ብታስጠነቅቀውና ብታምለው ግን ግብርህ አፍአዊና ረብ የለሽ ነው፡፡
“ሐሜት ግን'ኮ ይጣፍጣል፡፡" በፍጹም! ጣፋጭስ አለማማት ነው፡፡ ምክንያቱም ሐሜተኛ ሰው ካማበት ጊዜ አንሥቶ ጠበኛ ነው፤ ተጠራጣሪ ነው፤ ይፈራል፤ ይጸጸታል፤ ከዚህም የተነሣ ምላሱን ይነክሳል (ይከነክኗል)፡፡ እንዲህ በፍርሐትና በረዓድ ተይዞ ሳለም ከዕለታት በአንዷ ላይ የተናገረው ነገር ወደ ሌሎች ሰዎች ይዛመታል፡፡ ታላቅ የኾነ መከራ እንደዚሁም ረብ የለሽና የማይገ'ባ ጠላትነትን ያመጣበታል፡፡ የጉዳዩን ምሥጢራዊነት ለሌላ ሰው የማይናገር ሰው ግን ዐረፍተ ዘመኑን ያለስጋትና እጅግ ደስ ብሎት ያሳልፋል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡- “የሰማኸው ቃል በአንተ ዘንድ ይሙት! እንዲህ ያደረግህ እንደ ኾነ የሚያገኝህ ክፉ ነገር እንደሌለ እመን” (ሲራ.19፡10)፡፡ “በአንተ ዘንድ ይሙት" ሲል ምን ማለት ነው? አጥፋው፤ ቅበረው! ከዚህ በላይ እንዲኼድ አትፍቀድለት! ምንም እንዳይንቀሳቀስ አድርገው፤ ከዚህ ኹሉ በላይ ግን ሰዎች ሐሜትን ሲለማመዱ ታግሠህ እንዳትስማቸው ተጠንቀቅ፡፡" አንተም ድንገት በኾነ ጊዜ ላይ ሐሜትን ብትስማ የሰማኸውን ቅበረው፤ የተነገረህን አስወግደው፤ ወደ መርሳት ባሕርውስጥ ጣለው፤ ይህን ያደረግህ እንደኾነም ነገሩን እንዳልሰሙት ሰዎች ኾነህ የዚህ ዓለም ሕይወትህን በሰላምና በጸጥታ ታሳልፋለህ፡፡
ሐሜተኞች ከሚያሙአቸው ሰዎች በላይ እኛ እነርሱን [ሐሜተኞቹን] እንደምንጸየፋቸው ቢያውቁ ኖሮ ከዚያን ጊዜ ጀምረው እነርሱ ራሳቸው ይህን ክፉ ጠባይ በተዉ፣ ኃጢአታቸውን ባስወገዱ፣ ከዚያ በኋላም እኛን እንደ ታዳጊዎቻቸውና ረዳቶቻቸው አይተው ባመሰገኑን ነበር፡፡ እኛን ማመስገናቸው የወዳጅነታቸው ምልክት እንደ ኾነ ኹሉ ማማትና ስም ማጥፋትም አሁን ላዳበሩት ጠላትነት፣ ቂምና በቀል ጥንትና መሠረት ነበርና፡፡
ለሐሜት የሚሯሯጥና የሌሎች ሰዎችን ሕይወት በማጥናት የተጠመደ ሰው መቼም መች የራሱን ሕይወት መመልከት አይቻለውምና፥ የሰውን ምሥጢር ለማወቅ ከመጓጓትና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ዘው ብሎ ከመግባት ልማድ በላይ የራስህን ጉዳይየሚያስረሳ ምንም የለም፡፡ ምርምሩ ኹሉ በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ መግባት ስለ ኾነ እርሱን የሚመለከቱ ኹሉም አስፈላጊ ነገሮች ለአደጋ የተጋለጡ ኾነው ይተ'ዋሉ፤ ችላም ይባላሉ፡፡ ሰው ትርፍ ጊዜዉን የገዛ ራሱን ኃጢአቶች እንደዚሁም እንዴት ሊያስወግዳቸው እንደሚገባው ቢያስብ መልካም ነው፤ መንፈሳዊ ምንድግናንም ገንዘብ ያደርጋል፡፡ ኹልጊዜ በሌሎች ሰዎች ጉዳይ የምትጠመድ ከኾነ ግን የራስህን ክፉ ግብሮች የምታስተውላቸው መቼ ነው?
ይቀጥላል....
(ትምህርት በእንተ ምክንያተ ሐውልታት፣ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ገጽ 79-96 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)