بلغ العُلا
(ፉአድ ሙና)
.
ሰውነት ፋይዳ ያገኘው በእርስዎ ነው። የእርስዎ መገኘት ባልተፈጠረ የመኖር ትርጉም ጣዕም አልባ ነው። ስምዎን ስንሰማ የሚታገለን ሳግ ባልኖረ ለህይወት መጓጓት ምንም ነው።
እስልምናን ታግለን ያገኘን አይደለንም። ስለእምነትዎ እርስዎ እንደተወገሩት የሚወግረንን ችለን የተቀበልነው እምነት አይደለም። በአላህ ችሮታ ደም ሳይፈሰን በተፈጥሮ እምነታችን ላይ ቀጥለናል። ምናልባት የእኛንም መወገር ስለተወገሩት ይሆናል። መሰደብን ሁሉ እርስዎ ላይ ስላዘነቡም....
እንደ ሰልማን [ረዐ] ትክክለኛውን እምነት ፍለጋ አስር ጊዜ በባርነት አልተሸጥንም። እንደ አብዱላህ ዙል ቢጃደይን [ረዐ] ስለ እስልምና ሀብታችንን ተቀምተን በጆንያ አልተጠቀለልንም። እንደ አባታችን እንደ ቢላል [ረዐ] የባላባት አለንጋ እየሞሸለቀን አሀድ አሀድ አላልንም። እንደ ሰውባን [ረዐ] ከአይናችን ሲጠፉ ናፍቆትዎ በሽተኛ አላስመሰለንም። ግን ናፍቆትዎን እንናፍቃለን። በስምዎ ሀሴት እናደርጋለን።
ይህ ሁሉ የኢስላም ስኬት ከስምዎ ጋር የተቀራኘ ነው። አላህ ወዶ አስወደደዎ! የኛ ላኢላሀኢለሏህ የእርስዎ ድንጋይ ማሰር ውጤት ነው። ለእኛ እምነት የእርስዎ ጥርስ መሰበር ክፍያ ነው። ሚስኪኑ ነብይ!
እንደው ደግነትዎ ግዘፍ ቢነሳበት ሰብዓዊነትዎ ቢያስደንቀው ይመስለኛል ገጣሚው የእርስዎን ጉዳይ እንዲህ ሲል የገለጠው: ‐
بلغ العُلا بكمالـــــــهِ
كشف الدُجى بجمالـهِ
حَسُنت جميعُ خصالهِ
صَلُّوا عليه و آلــــــهِ
በምሉዕነት
ላይ የታከከው፣
ውበቱ ፅልመት
የገሸለጠው፣
ያማረችለት
ሙሉ ተፈጥሮው
ይውረድ ሰለዋት
በርሱም በአህሉ!
ቢፅፍዎት ቢያወድስዎት ህመም መቀስቀስ እንጂ ከልብ እንኳን አያደርስም! የካዝናው ባልተቤት ምንዳዎን አብዝቶ ይክፈልልን! አንቱ የጀነት ጌጥ!
.
@Fuadmu