Nomadic Poems dan repost
ኂሳዊ ንባብ በእያዩ ፈንገስ፣ ቧለቲካ
1. ይዘት
“እያዩ ፈንገስ” በቴአትር ይዘቱ ከፖለቲካዊ ስላቅ (political satire) እና ከማኅበራዊ ትችት (social commentary) ዘርፍ የሚመደብ የአንድ ሰው ተውኔት (one man show) ነው። የተውኔት ዝግጅቱ በአንዲት ሀገር ውስጥ ያለን ዐቢይ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ክስተቶችን፣ የጊዜውን መንፈስ (sign of the times) በጥልቀት በመታዘብ እና በማጥናት፣ በመተንተን (በተለይም ፖለቲካል ዲስኮርስ እርም በኾነበት ሀገር) ኪናዊ በኾነ መንገድ የራሱ ሕልውና ባለው በአንድ ገጸ ባሕርይ በኩል የነጠረ ትችትና ምክረ ዐሳብ በማቅረብ ላይ የተመረኮዘ ነው።
ትዕይንትና ቃለ ተውኔቱም የአንድን አካል በጌጥ የተለበጠ ውድቀት በድፍረት እያነሡ መሳቂያ፣ መሳለቂያ ማድረግ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። የገጸ ባሕርይው ተአምኖት ለእውነት ብቻ ነው። በዚህም አንድ በሥልጣን ኃይሉ የሚመካ አካል በቁም ነገር የወሰደውን አነዋወር (way of life) ያለምንም ፍራቻ እየተሳለቀ ውድቅ ያደርግበታል። ይህን ሲያደርግ ግን እንደ ሰይፍ በኹለቱም ገጽ በተሳለ፣ በተምሳሌት በታሸ ንግግርና መነባንብ ነው። ቃለ ተውኔቱ በታሪክ (story)፣ በግጥም፣ በመረጃ (fact)… የደረጀ ነው። ተውኔቱ እንደ ውኃ ላይ ኩበት ተንሳፋፊ አይደለም። ክሶቹና ትችቶቹ መሬት በያዘ ተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሠረቱ መኾን ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ለግልጋሎታዊ ኪነ ጥበብነት (utilitarian art) ይቀርባል።
ጸሐፈ ተውኔቱ በረከት በላይነህ በፈረስ አፉ ገጸ ባሕርይው (through his mouthpiece character) በእያዩ ፈንገስ በኩል ለሕዝብና ለመንግሥት ያለውን ኂስ ያቀርባል። ክፍተታቸውን እንዲያርቁ፣ ጉድለታቸውን እንዲሞሉ፣ አካሄዳቸውን እንዲያቀኑ፣ ስሕተታቸውን እንዲያርሙ እየነቀሰ ይጠቁማል። ይሞግታል። ለድምፅ አልባ ዜጎችም ጉልህ ድምፅ (voice for the voiceless) ይኾናል። እንዲያም ኾኖ በውብ ሥነ ጥበባዊ አቀራረቡና በትረካ ፍሰቱ ዓይነ ግቡ ነው። በሕይወት ምስቅልቅሎሽና ቀውስ ውስጥ ያለፈው ተደራሲ በመራር ሕይወቱ ላይ እንዲስቅ ይጋብዘዋል። በሳቁ ያክመዋል። የፈውስ ጉዞ "therapeutic" ይኾንለታል። በተመሳሳይ ቅጽበት አሳዛኝ ሕይወቱ አስቂኝ እንደ ኾነ ይገልጥለታል።
እዚህ ጋር ከማሳቅ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ላንሣ። ደረጄ ኃይሌ ስለኮሜዲ ተጠይቆ በተናገረበት አንድ ቃለ ምልልስ ላይ ቀልድ ከመረረ ሕይወት ውስጥ የሚወለድ ጥብብ እንደኾነ እንደ ተናገረ አስታውሳለሁ። የኮሜዲ አቻ አማርኛ “ቀልድ” ነው ብዬ አላምንም። ይህ ስያሜ ከያኒውንም ኾነ ይዘቱን እንደ አጫዋችና ጨዋታ ብቻ እንዲወሰድ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽዖ እንዳደረገ ይሰማኛል።
ኮሜዲያን ዳኒ ቁንጮ ከአለቤሾው ጋር ባደረገው አንድ ቃለ ምልልስ ላይ ሰዎች ስለ ኮሜዲ ያላቸውን አሉታዊ እሳቤ የሚያንጸባርቅ የግል ገጠመኙን አውግቶ ነበር። እንዲህ ነው፦ ዳኒ በሥራው ዕውቅና እና የገንዘብ ሽልማት ማግኘቱን ተከትሎ ለእናቱ በግ አርዶ፣ ከገንዘቡ ላይም ተቆራጭ ያደርግላታል። ይህን ያየች እናቱ ቡና እያፈላች “አንተ ዳንኤል ቀልደህ ይህን ያህል ብር ካገኘህ ቁም ነገር ብትሠራ ስንት ልታገኝ ነው?” እንዳለችው ተናግሮ ነበር። መልእክቱ ግልጽ ነው። በየትኛውም “ቀልድ” ውስጥ መራር እውነታና ቁም ነገር አለ። እሴት (substance) አልባ ቀልድ ማለት ከሳቅ ጋር ሞቶ የሚረሳ ነው።
ለምሳሌ ያህል፦ የዝነኛው የቻርሊ ቻፕሊ ድምፅ አልባ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከበሳቅ ገዳይነታቸው ጀርባ በሴማቸው (as a theme) ከታላቁ ድቀት (the great depression) በኋላ በተከተሉ የአድማ፣ የሕዝብ አመፅ፣ የሥራ አጥነት፣ የድኅነት፣ የፋብሪካ ማሺኖች የበላይነትና በወዝ (በላብ) አደሮች ሕይወት፣ በሰው ልጅ የደስታ ኀሰሳ ላይ የተሰነዘሩ ኂሶች (bold statements) ነበሩ። ከመልእክቱ አብዛኛውን በዋናነት ያደረሰውም የዓለም ቋንቋ በኾነ “ዝምታ” ብቻ ነው። አሳየ እንጂ አልተናገረም። ነገር ግን ዓለም መልእክቱን በግልጽ ሰምቷል። መዝግቧልም።
ቻርሊ በታላቁ ድቀት ወቅት እንደ ዊንስተን ቸርችል፣ በርናንድ ሾ፣ አልበርት አንሽታይን… ካሉ ግለሰቦች ጋር የተገናኘበት አጋጣሚዎች እንዳሉ ጥቁምታ የሚሰጡ መረጃዎች አሉ። ዛሬ ዛሬም እነዚህ በቻርሊ የሲኒማ አበርክትዎች ቀድሞ የተነሡ ጉዳዮች በተለያዩ የክፍለ ዘመናችን ዐሳቢያን የመወያያ መድረኮችና የመጻሕፍት አጀንዳዎች ኾነው እንደ ዘለቁ ናቸው። ዓለም ቻርሊ ቻፕሊን ከጥምዝ ጽሕሙ፣ ከባርኔጣው፣ ከትልቅ ሸፋፋ ቆዳ ጫማው፣ ከተራ ሱቱ፣ ከአስቂኝ ገጽታው በላይ በተራማጅ ዐሳቦቹና በላቀ የትወና ጥበቡ ይዘክረዋል።
እያዩ ፈንገስ በዘውጉ ኮሜዲ አይደለም። ነገር ግን እንደ ዋና ቀለምና መሣሪያው (element and tool) ይገለገልበታል። ጥርስ ባያስከድንም ትችቱ አይነቅዝም። ተውኔቱ የተመደረከበት ጊዜና ዘመን አልፎም መልእክቱ አይነጥፍም። ከታዳሚ ሳቅ ጋር አይሞትም። የመልእክቱ ዕድሜ እንደ ታዳሚ ከምንስቀው ሳቅ ይረዝማል። ነገር ግን ስለ ኮሜዲም ኾነ፣ ስለ ፖለቲካና ማኅበራዊ ስላቅ ትክክለኛ የትርጉም ቅኝት በሌለው ማኅበረሰብና ተደራሲ ዘንድ የእያዩ ምጸቶች በተሳሳተ መንገድ ሊወሰዱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው።
የሚያስቅ ነገርንና ኩሸትን እንደ አዝናኝ ቀልድ ብቻ የመውሰድ ተለምዷዊ አረዳድ አለ። የዚህ አረዳድ ሰለባ ከኾኑ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል የበዕውቀቱ ስዩምን “መግባትና መውጣት” በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በአብዛኛው አንባቢ ዘንድ የብሉይ ሥራነት ስፍራ የተሰጠው በማሳቁ እንጂ በሥነ ጽሑፋዊ ዋጋው (based on its literary values) አይመስልም።
ከማሳቁ ባሻገር አልፈን ከያኒው በመግባትና መውጣት ሥራው በስተ መጨረሻ ለማለት የፈለገውን ነገር (say) ከልቡናችን መጻፍ አለብን። ይህን ማረቅ የሥነ ጽሑፍ ኀያሲያንና ዐቃቢያን ሥራ ነው። ከተውኔቱ ማግስት ኂሳዊ ዳሰሳዎች መጻፍ አለባቸው። በዚሁ አግባብ እያዩ ፈንገስ ከ “ዕብድነቱ”፣ ከፌስታሉና ከአጀንዳው፣ ከተዥጎረጎረ ልብሱ፣ ተጠግቶ ከሚኖርበት ግድግዳ በላይ ነው። እኛም እንደ ታዳሚ በ “ቀልዱ” ሳይኾን ይዞት በመጣው መልእክት ልናስታውሰው ይገባናል።
(ይህ ጽሑፍ መግቢያ ነው። ክፍል ኹለት ይኖረዋል።)