የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት አዋጅን አጸደቀ።
አዲስ አበባ፤ጥር 29/2017 ዓ.ም
ምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ ምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ስርዓትን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አድምጧል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነጎ (ዶ/ር)፥ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ የመንግስት አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍና የዜጎችን የወሳኝ ኩነቶች መረጃ በተደራጀ መልኩ ለመያዝ ያስችላል ብለዋል።
በአግባቡና በወቅቱ የተመዘገቡ ወሳኝ ኩነቶችና የቤተሰብ ምዝገባ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የልማት ዕቅዶችን በማሳካት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሚናቸው የላቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከዚህ አኳያ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ነዋሪነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የውጭ አገር ዜጎች እንዲመዘገቡና የተሻለ የደህንነት ጥበቃ እንዲኖር እንደሚያስችልም ነው ያነሱት።
አዋጁ የሚመለከታቸው አካላት በህግ በሚሰጣቸው ስልጣንና ሃላፊነት መሰረት በቅንጅት እንዲሰሩ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፥ ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ የሲቪል ምዝገባው በአግባቡና በተደራጀ መልኩ ባለመቀመጡ በጉዞና በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል።
በሌሎች አገሮች የተጠናከረ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ በመኖሩ አገልግሎቶችን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።
ልደትና ጋብቻን ጨምሮ ወሳኝ ኩነቶችን በአግባቡ መዘግቦ መያዝ ለሀገር የልማት ፖሊሲ ዝግጅትና ክለሳ ወሳኝ ነው ብለዋል።
አዋጁ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚደረጉ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው በተናበበ መልኩ እንዲሆን አጋዥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
(ኢዜአ)
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
--
Telegram:
https://t.me/ICS_EthiopiaFacebook:
https://www.facebook.com/ICSEthiopiaTwitter:
https://twitter.com/ics_ethiopiaTikTok:
https://www.tiktok.com/@ics_ethiopiaLinkedIn:
https://www.linkedin.com/company/icsethiopiaYouTube:
https://www.youtube.com/@Ics_Ethiopia