ሐምሌ 22 ሁለት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አባቶች በክብር ያረፉበት ታላቅ ቀን ነው። ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ እና ታላቁ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ዘሸዋ (ሀገረ ስብከት):: በረከታቸው ይደርብን። ጸሎታቸው እና አማላጅነታቸው የሚወዷትን ሀገራቸውን ሀገራችንን እና ሕዝቡን ይጠብቅልን። በዚሁ አጋጣሚ በ2006 ዓ.ም የጻፍኩትና አዲስ ጉዳይ ላይ የወጣውን ጽሑፍ እንድታነብቡ ልጋብዛችሁ።
+++++++++
“ምንም ብትሉ፣ ምንም ብትሉ፤ ይህ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው!!!!” (ታላቁ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤1933 ዓ.ም - ሐምሌ 22/ 1982 ዓ.ም)
+++++
(ከቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ፤ አዲስ ጉዳይ መጽሔት ሐምሌ 2ዐዐ6 ዓ.ም)
ሐምሌ 22/1982 ዓ.ም በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ያጡት በ20ኛው መቶ ክ/ዘመን የወንጌልና የታሪክ ብርሃንን በተለይ በወጣቱ ሕይወት ላይ የፈነጠቁት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ በድሮው የክፍላተ ሀገር አከፋፈል የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ። ከዚህ ዓለም ከተለዩ እነሆ 24 ዓመት ሞላቸው። መታወቂያቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስነታቸው እና አባትነታቸው ቢሆንም በጽሑፋቸው፣ በትምህርታቸው እና ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ባላቸው ጽኑዕ ፍቅር ከእምነት ድንበር ባሻገር የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልቡና ሊገዛ የሚችል ስብዕና የነበራቸው አባት ነበሩ።
ብፁዕነታቸው ሚያዚያ 23/1982 ዓ.ም፣ ሻሸመኔ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያስተማሩት ትምህርት ኢትዮጵያ አገራችን በዚያን ወቅት የነበረችበትን የጦርነት እሳት እና መጻዒውን የሕዝቧን ሁናቴ በቅጡ የሚያመለክት ነበር። ከተናገሯቸው ዐበይት ቃላት መካከል “ምንም ብትሉ ምንም ብትሉ፣ ይህ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ ደህና አድርጋ መሥራታዋለችና” የሚለውን አባባላቸውን ዛሬም ድረስ በቃሌ አስታውሰዋለሁ። “ምንም ብትሉ ምንም ብትሉ” ያሉት በዓይነ ልቡናቸው ማን ምን እያለ ታይቷቸው ይሆን? እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ።
በተለይም የሃይማኖት አባቶች መንፈሳዊ እና አገራዊ አቋማቸው በሚዋዥቅበት በዚህ ዘመን እጅግ በጣም ባልራቀው ዘመን የነበሩትን የነአቡነ ጎርጎርዮስን ሕይወት መጥቀስ ዙሪያ ገባው ጨለማ እንዳልሆነ ለማሳየት አንድም በእውነት እና በዕውቀት ብርሃን ለመመላስ አንገቱን ቀና ለማድረግ ለሚታትር ማንም ሰውም ጥብዓት ለመስጠት ይጠቅማል።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በጵጵስና ያገለገሉባቸው ዓመታት 10 ዓመታት ብቻ ናቸው። በነዚህ ጥቂት ዓመታት ያበረከቷቸው ተግባራት ግን ዛሬም ሕያው ሆነው ይታያሉ። ከአገር ቤት አገራዊውን ዕውቀት በቅጡ በማደላደል፣ ወደ ውጪውም ዓለም በመሔድም ከዘመናዊው ዓለም የዕውቀት ገበያ በመገብየት ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ኅሊና ባለቤት የሆኑት ገና ከማለዳው ነው።
የአገሩን ዕውቀት ሲጨብጥ የውጪው፣ የውጪውን ሲይዝ የአገሩ ለሚጎድልበት አገርና ምሁር ጥሩ ማሳያ ናቸው። የአገራቸውን ሳያውቁ የውጪውን ብቻ በማነብነብ ያልተፈተነ መፍትሔ ለአገራቸው ችግር ለመስጠት በመሞከር መክነው የቀሩ ብዙ ትውልዶቻችንን ያጣነው በዚህ ምክንያት ነው። አገራችን ከአፍሪካዊ ማንነት በአንድ ጊዜ ተነቅላ ፈረንጃዊ ለመሆን ሞክራ በመካከል ደክማ የቀረችው መሠረቷን ሳታጠብቅ በውጪው ላይ ለመንጠላጠል ባደረገችው ሙከራ ነው።
ዕብራይስጥ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና አረብኛ ቋንቋዎችን በቅጡ የሚያውቁት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በዝዋይ ሐመረ ብርሃን በመሠረቱት የቅዱስ ገብርኤል ገዳም የዕውቀት ዓምባ አቋቁመው ኢትዮጵያዊውን ታሪክ ከዓለሙ ጋር እያነጻጸሩ ለደቀመዛሙርቶቻቸው ሲያሰተምሩ ቆይተዋል። ጭው ጭው የሚል የሩቅ አገር ሬዲዮ ድምጽ ከደጃፋቸው የሚሰማው እኒህ አባት ለገዳማውያኑና ለትምህርት ከየከተማው ለሚሰባሰቡት ተማሪዎቻቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለተማሪዎቹ ዕውቀትና ሥነ ልቡና በሚመጥን መልኩ ሲያቀርቡ መስማት ያስደንቃል።
የሃይማኖትና የታሪክ ጥናትና ምርምራቸውን “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” እና “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዓለም መድረክ” በሚሰኙ መጻሕፍቶቻቸው ቅልብጭ አድርገው አቅርበዋል። ለ፤መጻሕፍቱ መርጃነት የተጠቀሙባቸው ዋቤ መጻሕፍት ዝርዝር በሕዳግ በገጽ በገጹ ተጠቅሶ ይታያል። በአዋቂነት ድፍረት ሳይሆን በማስረጃ ጥንቁቅነት የቀረቡ፣ ከወጣት የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እስከ ካህናት ብሎም ከየዩኒቨርሲቲው ትምህርት የዕረፍት ጊዜውን ወስዶ ከርሳቸው ሊማር ለሚመጣው ዘመናዊ ትውልድ በሚሆን መልኩ የተዘጋጁ የጥናት ሥራዎች ናቸው።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሃይማኖት አባቶች የሚያሳዩትን የቅምጥል ኑሮ እንደሚቃወሙ በአንድም በሌላም ቢገልጹም "እኛ የመነኮስነው ለፍትፍት አይደለም" የምትለው አባባላቸውን ብዙዎች ያስታውሱታል። መነኮሳት ይህንን መስመር የሚመርጡት እንደማንኛውም ተርታ አማኝ በተቀማጠለ ኑሮ ለመመላለስ ሳይሆን ራስን በሚጎስም መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ለመጠመድ መሆኑን አበክረው ይናገራሉ። ለኑሮ የማይመቸውንና ከዝዋይ ሐይቅ በተጎራበተው የቅዱስ ገብርኤል ገዳማቸው ጠንካራ ኑሮን በመቋቋም ገዳሙን ለወላጅ አልባ ሕጻናት ማሳደጊያነት እና ለትምህርት ማዕከልነት የሚመች ሥፍራ ያደረጉት በዚሁ መርሐቸው ነበር። በተለይም በዚህ ዘመን፣ በሃይማኖት አባቶች ላይ የሚታየው የቅምጥል ኑሮ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሕይወት ሲመዘን እጅጉን ጎዶሎ ይሆናል።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አባትና እናት የሌላቸውን ሕጻናት ሰብስቦ ማሳደግ የቤተ ክርስቲያን አንዱ ዓላማ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል። እርሳቸው ባረፉበት ወቅት ከ200 በላይ ሕጻናት የሚያድጉበት የነበረው ያ ገዳም የነገ ተስፋ የሆኑ ልጆችን በመንከባከቡ በኩል የሃይማኖት መሪዎች ያለባቸውን ታላቅ ኃላፊነት የሚያመለክት ነው። የሌላውን እንኳን ብንተው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጥቂቱ ከሚታዩ ሙከራዎች ውጪ ይህ ነው የሚባል ሕጻናትን የመታደግ እንቅስቃሴ ስታደርግ አይታይም። በሀብት ደረጃቸው የናጠጡ የከተማ አብያተ ክርስቲያናት ለዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ጊዜ ያላቸውም አይመስሉም። የድሃ መብዛት የፈጣሪ ጸጋ ይመስል ድህነትንና ድሃውን በእነርሱ ኑሮ ማድመቂያነት የወሰዱት ይመስላል።
ሌላውና የዚህ ዘመን የአገራችንና የቤተ ክርስቲያን ሁነኛ ፈተና የሆነውን ዘረኝነትን በተመለከተ የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሕይወት ብዙ አስተማሪነት አለው። የሚያውቋቸው ሰዎች በሙሉ በአንድነት የሚመሰክሩላቸው በወገን፣ በወንዝ፣ በመንደርተኝነትን የማይጠረጠሩ፣ ዘረኝነትን በፍፁም የሚጠየፉ አባት መሆናቸውን ነው። ቤተ ክርስቲያናችንን ጨምድዶ ለያዛት የዘመነ መሳፍንት ዓይነት መንደርተኝነት፣ ጠባብነት እና ጎሰኝነት እንደ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ያለ ሰው ያስፈልጋል።
በምድራውያን ባለ ሥልጣኖች ፊት በሃይማኖታዊ ግርማ እንጂ በማጎብደድ መቆም ያልለመደባቸው ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ራሳቸውን አክብረው አባትነትን፣ ሃይማኖተኝነትን፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ብዙዎች ይስማሙበታል። የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን በቤተ መንግሥት መዳፍ ሥር ስትወድቅ ያለውን ጣጣ በመጻሕፍቶቻቸው መጥቀስ ብቻ ሳይሆን እርሳቸውም ያ ነገር እንዳይደገም በሕይወታቸው አብነት ሆነዋል።