ብፁዕ አባታችን። ድንግል ማርያም ቤዛዊት አትባልም ብለው ድምዳሜ ሰጥተው ሲያስተምሩ ሰማሁ። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አይባልም ብለን ከምንደመድም እንዲህ ብንል አይሻልምን?
🥀እናታችን ድንግል ማርያምን ቤዛዊተ ኩሉ ዓለም እንላታለን። ክርስቶስን ቤዛችን ስንለው በመስቀል ተሰቅሎ እኛን ስላዳነን ነው። ድንግል ማርያምን ቤዛዊት ስንላት ግን ቤዛኩሉ ክርስቶስን ስለወለደችልን ነው። ከእርሷ ተወልዶ ዓለምን አድኗልና ነው። ምክንያተ ድኂን ስለሆነች ነው። ልጇ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ ብሎ እንዳስተማረን እሱን ብርሃን እርሷን ደግሞ የብርሃን እናት እንላታለን። ልጇ አምላክ ስለሆነ እርሷ እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ ትባላለች። አምላክን የወለደች የአምላክ እናት ማለት ነው። ቤዛዊት ናት ስንል በጸጋ እንደሆነ ልብ እናድርግ። ምናልባት በባሕርይው ቤዛ ሆኖ ያዳነን ክርስቶስ ብቻ ነው ለማለት ፈልገው ከሆነ መልካም ነው።
🥀ንስጥሮስን ክርስቶስ ላይ ያለው የምንታዌ (Dualism) እይታ ድንግል ማርያምን ወላዲተ ሰብእ ከማለት አደረሰው። ድንግል ማርያም የወለደችው ሰው የሆነ አምላክን አምላክ የሆነ ሰውን ነው እንጂ ዕሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻን) አልወለደችም። ነገረ ክርስቶስን ከድንግል ማርያም በበለጠ የሚያውቀው ፍጡር የለም ። እርሷ ልጇን ይዛ ከሀገር ሀገር ተንከራታለች። በመስቀልም ጊዜ ከጽንዐ ፍቅሯ የተነሳ ከመስቀሉ ሥር አልቅሳለች። ድንግል ማርያምን እናከብራታለን፣ እናመሰግናታለን፣ እንሰግድላታለን። ነገር ግን ለእርሷ የምናቀርበው ስግደት እና ምስጋና የአክብሮት ስግደትና ምስጋና ነው እንጂ እንደ አምላክ የአምልኮ ስግደት አይደለም።
🥀ድንግል ማርያም ዓለም ጣዖትን በማምለክ ጨለማ ውስጥ ሳለ ብርሃንን የወለደችልን እናታችን ናት። ድንግል ማርያም ዓለም ለሰይጣን በመገዛት ባርነት ውስጥ ሳለ በመስቀል ተሰቅሎ የእኛን ሞት ሞቶ ነጻነት የሚያጎናጽፍ ጌታን ወለደችልን። ዓለም ተርቦ ነበር። እሷ ግን የሕይወት እንጀራን ወለደችልን። ድንግል ማርያም የትሕትና እናት ናት። ምሥጢራዊም ናት።ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ትጠብቀው ነበር ተብሏል። እውነትን ይዛ ሳለ በሐሰተኞች ወደ ግብጽ እንድትሰደድ ሆነች።
የቤዛነትን ትርጉም ንገረን ላላችሁኝ እነሆ
ቤዛነት ምንድን ነው?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጆች በሰው ልጆች ምትክ ያደረገው ሥራ ቤዛነት ይባላል። ቤዛ በአገባቡ "ስለ" ነው። ምሥጢሩ ምትክነትን፣ መቤዠትን ይገልጻል። ቤዛ "ቤዘወ-አዳነ" ከሚለው ግሥ ሲወጣ መድኃኒት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በሁለቱም ለክርስቶስ ቢነገር ያስኬዳል። መድኃኒታችንም ነውና። ቤዛ-ስለ በሚለው አገባብ ከተተረጎመ ስለእኛ በመስቀል ተሰቅሎ ማዳኑን ይነግረናል። ክርስቶስ ያደረገው ሥራ ሁሉ ስለእኛ ነው። በትርጓሜ በሐተታ በእንቲኣነ (ስለእኛ) እየተባለ የሚገለጸው እንደ ኃጥኣን ስቶ፣ እንደ ሰማዕታት ዕሴትን ሽቶ ያደረገው አለመሆኑን ለመግለጽ ነው።
ይህ ክርስቶስ ያደረገው የቤዛነት ሥራ የባሕርይ ሥራ ነው። ቅዱሳን ደግሞ አምላካቸው ክርስቶስን መስለው ስለሌላው ሰው ብለው የሚቀበሉት መከራ ቤዛነት ነው። ግን የጸጋ ቤዛነት ነው። "ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም" የሚለው ቃል ሰዎችም በአቅማቸው አንዱ ለአንዱ ቤዛ መሆን እንዲችሉ የተነገረም ጭምር ነው። ግእዙ "አልቦ ዘየዐቢ ወይኄይስ እምዝ ፍቅር ከመ ብእሲ ዘይሜጡ ነፍሶ ቤዛ ነፍሰ ቢጹ" ይለዋል (ዮሐ.15፥13)። ቅዱሳን ክርስቶስን አብነት አድርገው ስለሌሎች ሰዎች ሲጸልዩ፣ ሲጾሙ፣ ሲሞቱ አይተናል። ጌታም የእነርሱን ፍቅር አይቶ ኃጥኣንን ሲምር በብዛት ተጽፏል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሐዲስ ኪዳን ላይ ስንገባ በሰፊው እንመለከተዋለን።
©በትረ ማርያም አበባው
#ድምፀ_ተዋህዶ