ጥር ፳ /20/
በዚች ዕለት ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ በሽተኞችንም ይፈውሱ ዘንድ ጌታችን መርጦ ከላካቸው ከሰብዓ ሁለቱ አርድእት አንዱ የከበረ ሐዋርያ አብሮኮሮስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ በጽርሐ ጽዮን ከሐዋርያት ጋር ሁኖ ሳለ የአጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተሞላ። እርሱንም ሐዋርያት መርጠውት ከሰባቱ ዲያቆናት ጋር የተቆጠረ ሆነ እነርሱ መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ዕውቀትም ያላቸው እንደሆኑ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስለርሳቸው ምስክር ሆነ።
ከዚህም በኋላ ለወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙሩ ሆነ ከእርሱም ጋር ወደ ብዙ አገሮች ሔደ በቢታንያ አገር በኒቆምድያ ከተማ ላይ በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሾመው። እርሱም የክብር ባለቤት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት አስተማረ ከዮናናውያንም ብዙዎችን መልሶ ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው የወንጌልንም ትእዛዞች እንዲጠብቁ አስተማራቸው ቤተ ክርስቲያንንም ሠርቶ ቀሳውስትን ዲያቆናትን ሾመላቸው።
ከዚህም በኋላ ያቺን አገር ወደሚከቧት አገሮች ወጣ በውስጣቸውም የከበረ ወንጌልን ሰበከ ብዙዎችንም ከስሕተት መለሳቸው አይሁድንም የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ነገር ግን ብዙ መከራና ስደት ደርሶበታል ስለ ክርስቶስ ስም ተጋድሎውንም ሲፈጽም ጌታችንንም አገልግሎ በመልካም ሽምግልና አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤️