✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን፡፡ ✞
ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ
መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው: አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ7 ዓመታት ስቃይ በኋላ ተሰይፏል:: ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ:-
ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::
ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት-ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::
ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና 70 ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ::
ከዚያም ለተከታታይ 7 ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ:: 3 ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው: ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል:: "ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ: ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ::
ከ7 ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: 7 አክሊላትም ወርደውለታል::
"ዝርወተ ዓጽሙ"
ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ 'ዝርወተ አጽሙ' ትባላለች:: በቁሙ 'አጥንቱ የተበተነበት' እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው:: 70 ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ::
በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት:: ያለ ርሕራሔም አካሉን አሳረሩት:: ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት::
በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት:: "ሐረድዎ ወገመድዎ: ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል:: (ምቅናይ)
እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ:: ስለዚህም ይህቺ ዕለት ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው::
ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ: አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው:: 70ው ነገሥታት ግን አፈሩ::
ዝክረ ቅዱሳን
ወስብሐት ለእግዚአብሄር
💚
@ortodoxmezmur 💚
💛
@ortodoxmezmur 💛
❤️
@ortodoxmezmur ❤️