የውኃ ጥምቀት
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
2፥138 የአሏህን መንክር ያዙ! በመንከርም ከአሏህ ይበልጥ ያማረ ማነው? "እኛም ለእርሱ ብቻ ተገዢዎች ነን" በሉ፡፡ صِبْغَةَ اللَّهِ ۖ وَمَنْ أَحْسَنُ مِنَ اللَّهِ صِبْغَةً ۖ وَنَحْنُ لَهُ عَابِدُونَ
"ባፕቲዝማ" βάπτισμα የሚለው ቃል "ባፕቲዞ" βᾰπτῐ́ζω ማለትም "ነከረ" "አጠለቀ" "አጠመቀ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "መንክር" "ጥልቀት" "ጥምቀት" ማለት ነው፦
ማርቆስ 1፥4 ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ። ἐγένετο Ἰωάνης ὁ βαπτίζων ἐν τῇ ἐρήμῳ κηρύσσων βάπτισμα μετανοίας εἰς ἄφεσιν ἁμαρτιῶν.
ዮሐንስ የሚያጠምቀው ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት ሲሆን ሰዎች ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር፦
ማርቆስ 1፥5 ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።
ኢየሱስም የንስሐ ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፥ ሲጠመቅ ጸሎት ይጸልይ ነበር፦
ማርቆስ 1፥9 በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ።
ሉቃስ 3፥21 ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ።
የተጠመቀበት ምክንያት ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም ነው፥ ጽድቅ አምላክ ያዘዘው ትእዛዝ መታዘዝ ሲሆን ዓመፃ ደግሞ አምላክ የከለከለውን ማድረግ ነው። ኢየሱስ ጽድቅን በወደድ እና ዓመፃን በመጥላት የአምላኩን ትእዛዝ ለመጠበቅ እና ለማድረግ ተጠመቀ፦
ማቴዎስ 3፥15 "ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና"
ዕብራውያን 1፥9 "ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ"
ዮሐንስ 14፥31 "አብም እንዳዘዘኝ እንዲሁ አደርጋለሁ"
ዮሐንስ 15፥10 "እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ"
ኢየሱስ የተጠመቀው የውኃ ጥምቀት ብሉይ ኪዳን ላይ ያለ ጥምቀት ነው። የብሉይ ኪዳን ሰዎች የውኃ ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት ይጠመቁ ነበር፥ ይህንን የውኃ ጥምቀት የዕብራውያን ጸሐፊ ጥምቀት ይለዋል፦
ዘኍልቍ 8፥7 ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው።
ዕብራውያን 9፥10 እስከ መታደስ ዘመን ድረስ ስለ ምግብ፣ ስለ መጠጥ፣ ስለ ልዩ ልዩ "መታጠብ" የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና። μόνον ἐπὶ βρώμασιν καὶ πόμασιν καὶ διαφόροις βαπτισμοῖς, δικαιώματα σαρκὸς μέχρι καιροῦ διορθώσεως ἐπικείμενα.
እዚህ አንቀጽ ላይ "መታጠብ" ለሚለው የገባው ቃል "ባፕቲዝሞስ" βαπτισμός ሲሆን "ጥምቀት" ማለት ነው፦
ዕብራውያን 6፥2 እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሐ፣ በአምላክ እምነት፥ ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችንም ስለ መጫን፣ ስለ ሙታንም ትንሣኤ እና ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው።
እዚህ አንቀጽ ላይ "ጥምቀቶች" ለሚለው የገባው ቃል "ባፕቲዝሞን" βαπτισμῶν ሲሆን ይህ የውኃ ጥምቀት እስከ መታደስ ዘመን ድረስ ማለትም ኢየሱስ እስኪመጣ ድረስ የነበረ የብሉይ ሕግ ነው፥ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ስለ የውኃ ጥምቀት ምንም አላስተማረም። ቅሉ ግን እንደተናገረ አስመስለው አስዋሽተውታል፦
ማርቆስ 16፥16 ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።
የሚገርመው የማርቆስ ወንጌል የጥንት ዐበይት የግሪክ ዕደ ክታባት ኮዴክስ ቫቲካነስ እና ኮዴክስ ሲናቲከስ የሚጨርሰው ማርቆስ 16፥8 ላይ ነው፥ New International Version፦ "ከ 9-20 ያሉትን አናቅጽ ጥንታውያን እደ ክታባት እና ሌሎች የጥንት ምስክሮች የላቸውም"The earliest manuscripts and some other ancient witnesses do not have verses 9–20" በማለት ሐቁን ሳይሸሽግ ተናግሯል። አብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን ምሁራን ከ 9-20 ያሉት የማርቆስ የመጀመሪያ ጽሑፎች ክፍል እንዳልነበሩ ነገር ግን በኋላ የተጨመሩ እንደሆነ ይስማማሉ። ኢየሱስ "የውኃ ጥምቀት አጥምቁ" ብሎ አላዘዘም። ቅሉ ግን እንደተናገረ አስመስለው አስዋሽተውታል፦
ማቴዎስ 28፥19 “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው።
"በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው" የሚለው በግሪክ ዕደ ክታባት ላይ የተጨመረ ሲሆን ማቴዎስ በጻፈው በመጀመርያው በዕብራይስጥ የተቀመጠው ቃል ግን "አሕዛብን ሁሉ በስሜ ደቀ መዛሙርት አድርጉ" የሚል ነበር፥ ይህንን አሽቀንጥረው ስለጣሉት የሚያሳዝነው ይህ ንግግር ጠፍቷል። በዚህ ዙሪያ ከዚህ ቀደም የጻፍኩት መጣጥፍ ስላለ እንድትመለከቱት በትህትና እጠይቃለው፦
https://t.me/Wahidcom/3585ስናጠቃልልለው ውስብስብ እና ውዝግብ የሌለበትን የአሏህን የተፈጥሮ ጥምቀት እንድትይዙ ጥሪያችን ነው፦
2፥138 የአሏህን መንክር ያዙ! በመንከርም ከአሏህ ይበልጥ ያማረ ማነው? "እኛም ለእርሱ ብቻ ተገዢዎች ነን" በሉ፡፡ صِبْغَةَ اللَّهِ ۖ وَمَنْ أَحْسَنُ مِنَ اللَّهِ صِبْغَةً ۖ وَنَحْنُ لَهُ عَابِدُونَ
አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! እኛንም በተፈጥሮ ጥምቀት ጸንተው ከሚሞቱ ሙሥሊም ባሮቹ ያድርገን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcomወሠላሙ ዐለይኩም