---------ግጥም --------
#### ፉካሬ እውነት ####
' ሰማዩ እንዲህ እንደ ዛሬ ርቆ ሳይወረወር
ሁሉ እንጃሻው የሚቆርሰው
ሁሉ እንዳሻው የሚጎርሰው
ግዙፍ እንጀራ ነበር:: '
ብለሽ የነገርሽኝን እውነት ነው ተቀብያለሁ
ምክንያቱም እወድሻለሁ::
' አያቴ ሦስት መቶ ዓመታት ኖሩ
የመቶ ዓመት ሰው እያሉ ብርቱ ፅኑ ነበሩ::
ዝሆን በጥፊ ጣሉ
አንድ ጥይት ተኩሰው ሦስት ነብሮች ገደሉ:: '
ብለሽ የነገርሽኝን እውነት ነው ተቀብያለሁ
ምክንያቱም እወድሻለሁ::
' አባቴ ከሰዎች ሁሉ ይለያል
ባይኖቹ ብቻ ሳይሆን በማጅራቱም ያያል:: '
ብለሽ የነገርሽኝን እውነት ነው ተቀብያለሁ
ምክንያቱም እወድሻለሁ::
ግና ጅል እንዳልመስልሽ አይደለሁም ተላላ
በርግጥ በጄ ብላሻለሽ ነፍሴ ሁሉን ተቀብላ
እውነት ማለት...
ከሚወዱት መስማማት እንጂ አይደለምና ሌላ::
* በዕውቀቱ ሥዩም
@hasabbegaz123