ቅበላ
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንኳን ለታላቁ ጾም አብይ ጾም የቅበላ መዘጋጃ ቀን አደረሰን አደረሳችሁ!
በዚህ የዐብይ ጾም ዝግጅታችን ወቅት ሁላችን ክርስቲያኖች እንደሚታወቀው የመጀመሪያው ዓላማችን ከመምህረ ንስሐችን ጋር መገናኘት ነው::
የተጣላነውን መታረቅ የበደልነውን መካስ ለጾም ለጸሎት ለስግደት ለምጽዋት መልካምና በጎ ነገር ለማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር መነሳሳት:: የጸሎት የሰዓታት የኪዳን የቅዳሴ የስብከት ፕሮግራሞችን ለመካፈል ዕቅድ ማውጣት::
በመቀጠል የፀሎት መጻሕፍትን ማዘጋጀት መንፈሳዊ መጻሕፍቶችን ማዘጋጀት በዐብይ ጾም ወቅት የምንሳለማቸውን ገዳማት በዕቅድ በመያዝ ለበረከት ለመባረክ ለመቀደስ ዕቅድ ይዘን ዐቢይ ጾምን መጎዝ ያስጠቅማል::
ቅበላ
በዚህ ጽሑው ውስጥ ደግም ስለ ቅበላ አንዳንድ ነገሮች እንማማር:: ቅበላ ቃሉ ራሱ ወደ አንድ ነገር ነው የሚመራን:: አንድ የሆነ ነገርን መቀበል መጠበቀ ወደሚለው::
በዚህም አንድ የምንቀበለውን ነገር ለእንግዳው ነገር መዘጋጀት መዘጋጂያ ጊዜ ነው እንደ እንግዳው ዓይነት ክብር ዝግጅት በማድረግ::
በዚህም ምክንያት አሁን ከፊታችን የምንቀበለው ታላቅ የጾም እንግዳ አለ ታዲያ ይህን እንግዳ ለመቀበል ቅበላ እናደርጋል የምንቀበለውም እንግዳ ጾም ነውና በንስሐ ታጥበን ከቂም ከበቀል ርቀን ይህን እንግዳ መቀበልን ግድ ይለናል::
አባቶቻችን ዐብይ ጾም ከመግባቱ በፊት ለሰባትም ለሦስትም ቀን ጾምን ጾመው ቅበላ ያደርጋሉ::
ቅበላን በመብል በመጠጥ ሳይሆን ጾምን ራሱን ጹመው ቅበላ ያደርጉባታል አበው:: ምክንያቱም በጉጉት የሚጠብቁት የሚጠቀሙባት በዓመት የሚናፍቁት ታላቅ የጾም እንግዳ ሊቀበሉ ነውና! እንግዳ ሲመጣ እንደ እንግዳው ክብር መዘጋጀት ይገባልና::
እኛ ልጆቻቸው ዛሬ እንደሚታየው እንደነርሱ ባንሆን እንኳ እነርሱ የሰሩትን ሥራ ሠርተን ልንመስላቸው ይገባ ነበር:: ግን ፈጽሞ ተለየን ራቅናቸው ሆድ አምላኪዋች ስለሆን በፀጋም በረድሄትም ራቅናቸው::
ቅበላ ምግብን በመበቀል አልነበረም በጾም እንደ አበው ይገባ ነበር:: ግን ለክርስቲያኖች በማይገባ በመብል በመጠጥ በዝሙት በጭፈራ በዳንኪራ ጾምን መቀበል ነውር ኢ-ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ አደረግነው::
በዚህም ቅበላን በተሳሳተ አካሔድ ሔደን ዓለም በምተደሰኩረው ዲስኩር ተነድተን በጭፈራ በስካር በመብል እንዳናደርገው እንድንጠነቀቅበት የቤተ ክርሥቲያን የሥርዓት መጻሕፍት ያስተምረናል::
በማንኛውም ቀን ቢሆን ለክርስቲያን በዚህ ግብር መታደም መታየትም ማሰብም አይገባም:: በክርስቶስ ደም የከበረን ሰውነት በእንደዚህ ግብር ማቆሸሽ ተገቢ አይደለምና::
በየደብሩና በየገዳሙም ሱባኤ ያሰብንም ንስሐ ገብተን የበደልነውን ክሰን የቀማነውን መልሰን በፊት ከምንበላው ከምንጠጣው ቀንሰን በመጥን ብቻ ሳይሆን በዓይነትም ቀንሰን አስመሳይ ሳንሆን ሆነን መጾም መጸለይ መስገድ መመጽወት እንዳለብን የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍት ይነግሩናል::
አበው "ከምግብ ከመከልከል ብቻ ጾምን እንጾማለን አትበሉ ይህንንም ጨምሩ ከክፉ ግብር መራቅም ጾማችንን ትክክል ታደርጋለች" ይላሉ::
ከጾም በኋላ በሚኖረው ሕይወታችን በረከታችንን ሳናስወስድ የተውነውን ግብር ተመልሰን ሳንደግመው ልንጓዝ ያስፈልጋል::
በዚህም የአባቶቻችን ልጆች እንባላለን አባቶቻችን የወረሷትን መንግስት በእውነት እንወርሳለን:: ለዚህም አምላከ ተክለ ሃይማኖት ይርዳን አሜን! ይቅርታውና ቸርነቱ ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹
@fkl26 ⛪️
.
@fkl00