እንኳን #ኀዳር21 ለሚከበረው ለእናታችን ንጽሕተ ንጹሐን፣ ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የ #ኀዳርጽዮን ክብረ በዓል በሰላምና በጤና ጠብቆ አደረሰን አደረሳችሁ።
የዚህ ታላቅ በዓል መከበር መነሻው የሊቀ ካህኑ የኤሊ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ከሠሩት ኃጥአት የተነሳ ብዙ ተአምራትን የምታደርግላቸው ታቦተ ጽዮን በፍልስጥኤማዊያን እጅ ብትማረክም ኃይሏን የገለጸችበትና የሚያስደንቁ ተአምራትን የፈጸመችበት ታሪክ ሲሆን፣ በዓሉም በወቅቱ የተፈጸሙትን ተአምራት በማሰብ ፤ እንዲሁም ታሪኩ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ያለውን ተዛምዶ በማስታወስ ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርብበትና ፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው።
ይህ ታሪክ በቅዱስ መጽሐፋችን ውስጥ ከ 1ኛ ሳሙ 5፥1 ጀምሮ ተጽፎ የሚገኝ ሲሆን ለአብነት ያህልም እንዲህ ይላል፦
"ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አገቡት፥ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት።
በነጋውም የአዛጦን ሰዎች ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ ዳጎንንም አንሥተው ወደ ስፍራው መለሱት።
በነጋውም ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ የዳጎንም ራስ እጆቹም ተቈርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር፤ የዳጎንም ደረት ብቻውን ቀርቶ ነበር።
ስለዚህም የዳጎን ካህናት ወደ ዳጎንም ቤት የሚገቡት ሁሉ በአዛጦን ያለውን የዳጎንን መድረክ እስከ ዛሬ ድረስ አይረግጡም።
የአዛጦንም ሰዎች እንዲህ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ፡— እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ፡ አሉ። " (1ኛ ሳሙ 5፥2-7)
ከላይ ተአምራትን የፈጸመችው የእግዚአብሔር ታቦት "ታቦተ ጽዮን" ተብላ ትጠራለች።
"ታቦተ ጽዮን” የሚለውን ስያሜ ያገኘችውም ጽዮን ተብላ በምትጠራው የእስራኤል (የዳዊት) ከተማ ስም ነው፡፡ (2 ሳሙ 5 :7)
ጽዮን ማለት ተፀወነ፡- ተጠጋ፣ ተማጠነ ማለት ነው፡፡ ክቡር ዳዊትም ጽዮንን አምባ፣ መጠጊያ አድርጎ ብዙ ጠላቶቹን ተዋግቶ አሸንፎ ድልን ተጎናጽፏል፡፡(2 ሳሙ 5 :7 ፣ 9_10)
ጽዮን የተባለችው የታላቁ የዳዊት ከተማ የተገፉና የተበደሉ ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት፣ ተሰብስበው የሚሰነብቱባት ከተማ ስለነበረች፣ የእግዚአብሔርም ታቦት በዚያ ስለነበረች ፣ በርሷ ተማጽነውም ችግራቸው ይቃለል ስለነበረ ታቦቷ “ታቦተ ጽዮን” ተብላ ተጠርታለች፡፡" (2 ሳሙ 5 ፥ 7 ፣ 9_10 ፣ 2 ሳሙ 6 ፥ 12 ፣ 17 ፣ ኢሳ 1 ፥ 27 ፣ ኢሳ 33 ፥ 5 ፣ ኢሳ 14 ፥ 32)
በሌላ መልኩም "ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች።"
ይህም፦ ታቦተ ጽዮን "በውስጡዋ የያዘችው የሕጉ ጽላት የጌታችን ፣ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የጌታን እናት ንጽሕናዋን ፣ ቅድስናዋን ያመለክታል ፤ በውጭም በውስጥም በጥሩ ወርቅ መለበጧም የእመቤታችንን ንጽሕናዋን ቅድስናዋን፣ ድንግል በሕሊና ወድንግል በሥጋ ( በሀሳቧም ድንግል ፣ በሥጋዋም ድንግል) መሆኗን ያስረዳል።
ከዚህም የተነሳ በዓሉ የአማናዊቷ (የእውነተኛዋ) ጽዮን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል ሆኖ ይከበራል።
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር እና የበረከት በዓል እንዲሆንልን እግዚአብሔር አምላካችን በቸርነቱ ይርዳን።
ለሀገራችን ሰላም ፣ ለሕዝቦቿም ፍቅርን ፣ አንድነትን ፣ መተሳሰብን ያድልልን ፤ ጥላቻን ፣ ጭካኔን ፣ ተንኮልን ፣ ክፉ ሀሳብና ተግባርን በሙሉ ሁሉን ቻይ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ከሀገራችን ያስወግድልን።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤
የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የቅዱሳን ፣ የጻድቃን ፣ የሰማእታት ረድኤት ፣ በረከት፣ ምልጃና፣ ጸሎት አይለየን።
አሜን!
@Deaconchernet @Deaconchernet @Deaconchernet