1፦ ከዐረብ ሃገራት ውስጥ ፍልስጤም፣ ኢማራት፣ የመን፣ ኩወይት፣ በሕረይን፣ ቀጠር፣ ሊባኖስ፣ ሱዳን፣ የዒራቅ ሱኒዮች የወቅፍ ተቋም እና ሞሪታኒያ ዛሬ እሁድ ዒድ እንደሆነ ያወጁ ሃገራት ናቸው። የኛዎቹ "ምሁራን" ይህን ሁሉ ሃገር ጥለው ጉዳዩን የሳዑዲ ሴራ አድርገውታል።
2ኛ፦ አዘርቤጃን፣ አፍጋኒስታን፣ ካዛኽታን፣ ኡዝቤኪስታን፣ ቱርክ፣ ... ዒድ ዛሬ እሁድ እንደሆነ ያወጁ ሃገራት ናቸው።
3ኛ፦ እንዲሁም ዘጠኝ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት (ናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ማሊ፣ ጊኒ፣ ኮትዲቯር፣ ቤኒን፣ ሴኔጋል፣ ጋምቢያ እና ቶጎ) ዛሬ እሁድ ዒድ እንደሆነ አውጀዋል።
4ኛ፦ ከነዚህም ውጭ አናሳ ሙስሊሞች ባሉባቸው አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩሲያ፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ ወዘተ. በየሃገራቱ የሚገኙ ኢስላማዊ ተቋማት ዒድ ዛሬ እሁድ እንደሆነ ገልፀዋል።
ከተዘረዘሩት ውስጥ ከፊሎቹ የስነ ፈለክ ካሌንደር የሚጠቀሙ ናቸው።
ከነዚህ ሁሉ ሃገራት ነጥለው የሳዑዲው እወጃ ላይ ግርግር ማስነሳት ጅህልና እና ለሳዑዲ ያረገዙት ጭፍን ጥላቻ ተጣምረው የወለዱት ብልግና ነው። ስለ ሳዑዲ የራሳቸው ጉዳይ! ግን የሙስሊሞችን የደስታ ቀን እዚህ ግባ በማይባል ተልካሻ ሰበብ ወደ ግርግር መቀየር የለየለት ነውረኛ ተግባር ነው። በዚህ ነውረኛ ተግባር ላይ ከተሰለፉት ውስጥ በአካደሚ ትምህርት ገፋ አድርገናል ብለው የሚያስቡ አንዳንድ አካላት ከፊት ረድፍ ተሰልፈው አይተናል። ለነዚህ አካላት የምለው አለኝ። ድንበራችሁን ጠብቁ! አቅማችሁንም እወቁ። ሰው እንዴት አካውንቲንግ፣ ቢዝነስ አስተዳደር፣ ሳይኮሎጂ፣ ፍልስፍና ወይም የሳይንስ ዘርፎችን ተምሮ ይሄ ነው የሚባል ትኩረት ባልሰጠው የሸሪዐ ጉዳይ ውስጥ ጥልልቅ እያለ ግልፅ መረጃ በመጣባቸው የፊቅህ ጉዳዮች ውስጥ ያላቅሙ እየገባ ደፋር ግላዊ አስተያየት ይሰጣል?!
ወንድሞቼ! የተማራችሁት የቀለም ትምህርት አረቄ ሆኖ አጉል ድፍረት እየሰጣችሁ ጊዜ ባልሰጣችሁት የሸሪዐ እውቀት ላይ ፍርድ እንድትሰጡ ሲያደርጋችሁ ትንሽ ሐያእ አይሰማችሁም እንዴ? የምትከበሩትኮ የሚከበረውን ስታከብሩ ነው። ሃይማኖቱ የናንተም ነውና ስለ ኢስላም አታውሩ አይባልም። ግን ከቁርኣንና ከሐዲሥም፣ ከዑለማእ ንግግርም ርቆ ሌጣ ግላዊ እይታዎችን በድፍረት ማንፀባረቅ ነውር አይደለም ወይ? አንዳንዶቹ የፈለክ ምሁራንን ውሳኔ መከተል እንደሚገባ ያሳስቡናል። ያላስተዋሉት ግን የፈለክ ምሁራኑ ራሳቸው ወጥ ውሳኔ የላቸውምኮ። በተለያዩ አመታት በርካታ ታዋቂ የፈለክ ምሁራንን እርስ በርሱ የሚጋጭ ትንበያ ሲያወጡ ማየት የተለመደ ነው። ለምሳሌ ያህል የፈለክ ሂሳብን ከሚጠቀሙ ሃገራት ውስጥ የአሁኑን ዒድ ከፊሎቹ ዛሬ እሁድን፣ ከፊሎቹ ነገ ሰኞን መርጠዋል። ይሄ ምንድነው የሚያሳየው?
ለማንኛውም ተምረናል የምትሉ አካላት እረፉ። በየዘርፉ ጥልቅ እያላችሁ የእርጎ ዝንብ አትሁኑ። ሁሉም ዘርፉን ሊጠብቅ ይገባል። ኢንጂኔር በህክምና ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማይገባው አካደሚ የተማረውም ትኩረት ባልሰጠው የሸሪዐ እውቀት ላይ እጁንም ምላሱንም ሊሰበስብ ይገባል። ብዙም ይሰማሉ ብዬ አይደለም ይህን የማነሳው። ብዙዎቹ እነዚህ አካላት ትኩረት ፈላጊ (attention seekers) ናቸው። ችግራቸው እራሳቸውን ከመሀይማን መሀል የተገኙ ልዩ አድርጎ የመመልከት በሽታ ነው። ስለዚህ የሚሸወድባቸው አካል ይነቃ ዘንድ በሚግገባቸው መልኩ ማናገር ይገባል። ቆማጣን ቆማጣ ካላሉት ገብቶ ይፈተፍታል ይሉት አባባል በነሱ ጎልቶ እየታየ ነው።
ሃገራችን እስከ መቼ ሳዑዲን ትከተላለች?
~
ጥያቄው ንፁህ ጥያቄ ሆኖ ሚዛን የሚደፋውን ለመለየት ከሆነ ጥሩ ነው። አንድ ሃገር ካወጀ ተመሳሳይ የሰዓት አቆጣጠር ያላቸውና ሰዓታቸው ከኋላ የሆኑ ሌሎች ሃገራት መከተል አለባቸው ወይ የሚለው በዑለማእ መካከል የተለያየ ሃሳብ የተሰነዘረበት ጉዳይ ነው።
1- ኢማሙ ማሊክ፣ ሻፊዒይ፣ አሕመድ፣ ለይሥ እና ሌሎችም በርካታ ዓሊሞች አንድ ሃገር ጨረቃን ካየ ሌሎችም ሊከተሉ ይገባል ይላሉ። ይሄ አቋም የኢብኑ ተይሚያ፣ የሸውካኒይ፣ የሲዲቅ ሐሰን ኻን፣ የአልባኒይ እና የኢብኑ ባዝ ምርጫ ነው። ይህንን የማነሳው በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ሰው እንዲሁ የሳዑዲን ወይም የሌላ ቀድሞ ያወጀን ሃገር ምርጫ እንከተላለን ቢል እንደዋዛ የምናጣጥለው ሃሳብ እንዳልሆነ ለማስታወስ ያክል ነው።
2- ሌላ ተመሳሳይ የሰዓት አቆጣጠር መስመር ላይ ያሉ ሃገራት አንዱ ባየው ሌላው ሊከተል ይገባል የሚል አቋም አለ። ይሄ የኢብኑ ዑሠይሚን፣ የሙቅቢልና የሌሎችም አቋም ነው። በዚህም ሂሳብ ቢኬድ ከሳዑዲ ጋር የቀረበ ሁኔታ አለን።
3- እያንዳንዱ ሃገር ራሱን የቻለ ስለሆነ የአንዱ ሃገር ማየት በሌላው ላይ አስገዳጅ አይሆንም የሚል አቋም የመረጡም አሉ።
እነዚህ በጉዳዩ ላይ ከተሰነዘሩ ሃሳቦች ውስጥ ጠንካራዎቹ ናቸው። የሃሳቡ መለያየት ምክንያት "ጨረቃውን ስታዩት ፁሙ ። ስታዩትም አፍጥሩ" በሚለው ሐዲሥ ያለ የግንዛቤ ልዩነት ነው።
ሚዛን የሚደፋው የትኛውም ቢሆን ዛሬ እኛ ላለንበት ተጨባጭ ሳዑዲን መከተል ትክክለኛ ምርጫ ነው። ሃገራዊ ቅቡልነት ያለው ሁሉን የሚያግባባ ተቋም ሲኖር መስአላውን መፈተሸ ወግ ነው። እንዲሁ በመዝሀብ ጎጠኝነት ስለታሰሩ ብቻ በራሳቸው ጨረቃ እያዩ ሳይሆን "ወሃB ያየውን አንቀበልም" በሚል አጉል ድርቅና ብቻ በፆምም በዒድም ካልተለየን የሚሉት ግን እልህ ወለድ ሙግት እንጂ ውሃ የሚያነሳ ሃሳብ አይደለም።
በድጋሚ ተቀበላለሁ ሚና ወሚንኩም!
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሸዋል 1/1446)
=
የቴሌግራም ቻናል :-
https://t.me/IbnuMuneworhttps://t.me/IbnuMunewor