🍂🍂ክፍል አስራ ሁለት🍂🍂
🌿🌿"ጤዛዉ ፍቅሬ"🌿🌿
✍✍(ኑዕማን ኢድሪስ)
...."ሙሀመድ ነቢና
ኡሙሁ አሚና
አቡሁ አብደላህ..." የሚለዉ የፎዚያ የስልክ መጥሪያ እስከ ንዝረቱ 'ዝ... ዝ... ዝ...." እያለ የነሀቢብ ፍቅር ማድመቂያ መስሏል። ጆሯቸዉ ከአፍንጫቸዉና ከከናፍሮቻቸዉ መካከል ሾልኮ በሚወጣዉ ሞቃት ትንፍሽ ተደፍኗል።
.
.... ሀቢብ የፎዚያን ስሜት እየጠበቀ ከጠበቀችዉ በላይ አስደስቷታል። የደስታን ማማ አፈናጧታል።
ጋደም ባለበት ፎዚን በቀኝ እጁ ወደ ደረቱ አስጠግቶ አቅፏት በግራ እጁ ያሰረዉን ሰአት ተመለከተ። ከቀኑ 11:25 ይላል።
.."ያ አላህ ፎዚዬ ..." አለና ፎዚን ከእቅፉ ዉስጥ አዉጥቶ ተነሳ። እሷም በግንባሯ በኩል ወርዶ የተዘናፈለዉን ጸጉሯን በእጇ ወደ ኃላዋ መለስ እያደረገች ቀስ ብላ ጋደም ካለችበት ሶፋ እየተነሳች....
"ምን ሆንክብኝ ሀቢቢ?" አለችዉ።
..."ሀምዛን እስካሁን ሳልጠይቀዉ!" አላትና እየተቻኮለ ወደ ሸዋር ቤት አመራ። ፎዚያም ሰአቱ ስንት እንደሆነ ለማወቅ ተንተርሳዉ ከነበረችበት ትራስ ስር ስልኳን አዉጥታ ተመለከተች። ስንት ሰአት እንደሆነ ካወቀች በኃላ ቁጥሩን የማታዉቀዉ ስልክ ሰባት ጊዜ ደጋግሞ ተደዉሎባት ነበር።
.
.
.
.... "ግን ሀቢብ ምን ሆኖ ነዉ?" ንዴቷን ፊቷ ላይ አንጸባርቃ እየነገረችዉ ነበር።
...."መኪዬ ስለመምጣቱ ሳይሆን ስለደህንነቱ ተጨነቂ ... እሺ!" አላት ሀምዛ። ቀጠል አድርጎም ..."ሀቢብ ደህና ከሆነ ይመጣል። ለጓደኛዬ ዱዓ የማደርግለት በመንገዱ ላይ እንቅፋት እንዳያገኘዉና የ'ኔ እጣ እንዳይደርሰዉ ነዉ።" ብሎ በረዥሙ ትንፋሹን አወጣ። የ'ሱ ቅጽበታዊ አደጋ ለዘላለም ጎደሎ አድርጎ እንዳስቀረዉ ሁሉ ለጓደኛዉ ሀቢብም ይሄ ነገር እንዳይገጥመዉ በመመኘት ነበር።
...." እሱስ ልክ ነህ! ወጥቶ መቅረትም አለ።" አለች መኪያ። ይሄ መልሷ ለሀምዛም ይሆናል። ምክንያቱም ሀምዛ የደረሰበት ዱንያ ላይ ካሉ አደጋዎች ፤ ምድር ላይ ካሉ ችግሮች እጅግ በጣም ትንሹ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም 'ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን እግር የሌላቸዉ አሉና!' አይደል ተረቱስ። ከቤታቸዉ እንደወጡ ያልተመለሱ ስንቶች አሉ - መንገድ ላይ በሚገጥማቸዉ አደጋ ህይወታቸዉ ላትመለስ ይከነፈችባቸዉ። ወይም ወደቤታቸዉ ሲመለሱ ቤታቸዉ አልሆኑ ሆኖ ቤት ንብረታቸዉን ፤ ሚስት ልጆቻቸዉን በአደጋ አጥተዉ ህይወት የጨለመችባቸዉ እልፍ ሰዎች እንዳሉ የማይካድ ሀቅ ነዉ። ከነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ምናልባትም የሀምዛ ቀላሉ ነበር።
'ወጥቶ መቅረትም አለ' ስትለዉ እዉነት መሆኑን ለማረጋገጥ ያክል ራሱን በአዎንታ ወደ ታችና ወደ ላይ ከፍ ዝቅ አድርጎ ነቀነቀ።
.
..."ለይሰል ገሪቡ... ገሪብ አሽ-ሻሚ ወል የመኒ
ወላኪነል ገሪበ ... ገሪብ ወለህዲ ወል ከፈኒ
ዛሬ የሌሉ ከኛ ጋራ... ትናንት አብረዉን የኖሩ
ከመሬት በታች የገቡ ...የተጫናቸዉ አፈሩ
እሩቅ አስበዉ በተስፋ... ዳሩ ግን ባጭር የቀሩ
የራቁን የረሳናቸዉ ብዙ ወንድሞች ነበሩ....." የሚለዉ የሙሀመድ አወል ነሽዳ ከመኪያ ፖርሳ ዉስጥ ተሰማ - ስልኳ እየጠራ ነበር። ነሽዳዉ አቋርጡኝ አቋርጡኝ አይልም። በተስረቅራቂ ድምፁ ያዜማዉ ነሽዳ ቢሰማ የማይጠገብና የማይሰለች ነዉ። ይበልጥ ከሚያወሩት ርዕስ ጋር ስለገጠመ ተመሰጡብኝ ፤ አስተንትኑብኝ እንጂ ዝጉኝ አይልም - መካሪና ገሳጭ የሆነ ነሽዳ ነበር።
መኪያ የፖርሳዋን መቆፊያ ዚፑን ከከፈተች በኃላ ስልኩን አወጣች። ..."የፎዚያ ቁጥር ነዉ" አለችዉ። ሀምዛም አንገቱን መለስ አድርጎ አያት። አንሽዉና አናግሪያት ማለቱ ነበሩ። አይኖቹ እንጂ ልሳኖቹ አላናገራትም።
..."ሄሎ አሰላሙዓለይኩም" አለች መኪያ። ከወዲያ ማዶ ሆና የምታወራዉ ፎዚ የሰላምታዉን መልስ ከመለሰች በኃላ የመኪያን ስልክ ቁጥር ስላላወቀች ማንነቷን ጠየቀቻት።
..."መኪያ ነኝ ፎዚ.. የሀቢብ ስልክ አይሰራም አንቺም አልመለሽልኝም። ችግር አለ እንዴ ፎዚ!?" ብላ ጠየቀቻት። ሀምዛን የሚያስጨንቀዉና የሚያሳስበዉ የሀቢብንና የፎዚያን ወደ ሆስፒታል መምጣት ሳይሆን ደህንነታቸዉንና በመካከላቸዉ እርቅ መስፈኑን፤ በፍቅር አንድ መሆናቸዉን ነዉ። የሄን የምታዉቀዉ መኪያ ሀምዛ በሚፈልገዉ መልኩ ፎዚያን እያናገረቻት ነዉ። በዚህ መካከል ሀቢብ ከሸዋር ቤት ሰዉነቱን በፎጣ እየጠረገ ወጣ። ፎዚያ ለመኪያ የምትነግራት ምክንያት ስላጣች ሀቢብ ከሸዋር እስኪወጣ ተጠባብቃ መኪያን እንዲያናግራት ስልኩን አቃበለችዉ። አንገቱን ወደ ላይና ወደ ታች እየነቀነቀ 'ማን ነዉ?' በሚል አይነት ሁኔታ ጠየቃት።
ድምጿን ከፍ ሳታደርግ ከንፈሯንና ምላሷን ብቻ በማንቀሳቀስ ... "መ....ኪ....ያ ...ና...ት" አለችዉ።
.
..."መኪ አሰላሙአለይኪ እንዴት ነሽ?" ብሎ ሞቅ ያለ ሰላምታ አቀረበላት። የጓደኛዉን ጉድ አላወቀ ...
... "ወአለይኩም ሰላም ደህና ነህ?" በማለት መልሳ የሱን ደህንነቱን ጠየቀችዉ። የሷን ደህንነት ግን አልነገረችዉም። ምክንያቱም ደህና አይደለችም!። ባሏ በሚሰቃዬዉ ህመም የሷም ዉስጧ ታሟል።
... "አልሀምዱሊላህ ... ሀምዛ እንዴት ነዉ!?" ለመጠየቅ ያክል እንጂ ከሀምዛ ከተለዬ ብዙም አልቆየም። ሀቢብን ከሆስፒታል ወደ ቤቱ አላህ የወሰደዉ የሀምዛን አስደንጋጭ ዜና እንዳይሰማና ከፎዚያ ጋር ጣፋጭ የሆነ የፍቅር ጊዜን እንዲያሳልፍ ሽቶ ይመስላል። ... መኪያ ጭንቀትና ሀሳብ ያሞቀዉን ትንፋሿን በረጅሙ 'ኡህህህፍፍፍ...." ብላ አወጣች። ያወጣዉ ትንፋሽ በጣም ከመሞቁ የተነሳ ፊት ለፊቱ የፕላስቲክ ፌስታል ቢያገኝ ለማጨማድድ የሚያንስ አልነበረም።
... "አልሐምዱሊላህ ያዉ ነዉ..."
... "መጣሁ በቃ መኪ .. ብዙ አትጨነቂ" አላት። መኪያ መንታ ሀሳብ ዉስጥ ሆና ተወዛገበች 'ልንገረዉ ወይንስ ሲመጣ ይሻላል?' እያለች ከራሷ ጋር ስትወያይ ... ሀቢብ "ቻዉ መኪ" ብሎ ስልኩን ዘጋዉ።
.
... ፎዚያ አይን አይኑን እያየችዉ ነበር። ዘወር ብሎ ሲመለከታት ሶፋዉ ላይ ተቀመጣ ትቁለጨለጫለች። የሆነ ነገር እንዲላትና እንደሚወዳት እንዲነግራት ፈልጋለች።
... "የኔ ቆ..ን..ጆ...." ብሎ ከተቀመጠችበት ጎን ሂዶ ተቀመጠ።
... "ወይዬ ሁቢ" ስትለዉ ወደ ደረቱ አስጠግቶ እቅፍፍ.. አደረጋት። ፍጹም ሰላም ፤ ልዩ ደስታና ዘላለማዊ ሀሴት በይቅርታ ዉስጥ እንደ ወንዝ ዥረት በዝቶ ይገኛል። ይቅርታ ህመምን ያሽላል ፤ ዉሳኔንና ህግን ያሽራል። የዚህ ዉድ ነገር ባለቤቶች ግን ጠንካራ ሰዎች ናቸዉ። ፎዚ ደግሞ በዚህ አትታማም። እንኳን እሱዉ ይቅርታ ጠይቋትና ራሷ ሂዳ ይቅርታ ላድርግልህ ፍቅራችንን እናድስ እያለች ደጅ የምትጠና ልበ ብርቱ ሴት ናት።
... "እስከዛሬ ላደረግኩሽ ፣ ላስቀየምኩሽና ለበደልኩሽ ሁሉ ከልብ የሆነ ይቅርታሽን እፈልጋለሁ።" አላት። በአይኖቹ አይኖቿን እያየ ዉስጧን ሰርስሮ ልቧ ድረስ ዘልቋል። አሁን አንደበታቸዉ ብቻ ሳይሆን ልባቸዉም ሌላ ዉይይት ይዟል።
ሀቢብ ድንግል ያልነበረችበት ምክንያት ምን እንደሆነ ከይቅርታዉ በኃላ ሊጠይቃት ወስኗል። ግን ደግሞ 'እንዳዲስ በግድ ያገኘሁትን ፍቅር የማይሆን ጥያቄ ጠይቄ ባስቀይማትስ' ብሎ ፈራ። 'እሷስ በጥያቄዬ ተናዳብኝ መጥፎ መልስ ብትመልስልኝ የሚታገስ ልብ ይኖረኝ ይሆን?' ሙግቱ ከራሱ ጋር ነዉ። ይሄን እያሰበ ፎዚያ ትክ ብላ ስታዬዉ ቆይታ....
"ሀቢቢ የኔ ዉድ..." አለችዉ።
╔═══❖•💕💕•❖═══╗
ይቀጥላል...
╚═══❖•💕💕•❖═══╝
❥............🍃👑👑
@maraki_lyrics