🕊
[ † እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሆሴዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
🕊 † ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ † 🕊
† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን [አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር] : መጻዕያትን [ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን] የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::
ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: [ሐዋ.፲፩፥፳፯] ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::
ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: [ቅዳሴ ማርያም]
የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::
ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: [ዮሐ.፬፥፴፮]
ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: [ማቴ.፲፫፥፲፮ , ፩ዼጥ.፩፥፲] ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::
ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት
¤ ፲፭ [15] ቱ አበው ነቢያት :
¤ ፬ [4] ቱ ዐበይት ነቢያት:
¤ ፲፪ [12] ቱ ደቂቀ ነቢያትና
¤ ካልአን ነቢያት ተብለው በ፬ [4] ይከፈላሉ::
"፲፭ [15] ቱ አበው ነቢያት" ማለት :-
- ቅዱስ አዳም አባታችን
- ሴት
- ሔኖስ
- ቃይናን
- መላልኤል
- ያሬድ
- ኄኖክ
- ማቱሳላ
- ላሜሕ
- ኖኅ
- አብርሃም
- ይስሐቅ
- ያዕቆብ
- ሙሴና
- ሳሙኤል ናቸው::
"፬ [4] ቱ ዐበይት ነቢያት"
- ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
- ቅዱስ ኤርምያስ
- ቅዱስ ሕዝቅኤልና
- ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::
"፲፪ [12] ቱ ደቂቀ ነቢያት"
- ቅዱስ ሆሴዕ
- አሞጽ
- ሚክያስ
- ዮናስ
- ናሆም
- አብድዩ
- ሶፎንያስ
- ሐጌ
- ኢዩኤል
- ዕንባቆም
- ዘካርያስና
- ሚልክያስ ናቸው::
"ካልአን ነቢያት" ደግሞ :-
- እነ ኢያሱ
- ሶምሶን
- ዮፍታሔ
- ጌዴዎን
- ዳዊት
- ሰሎሞን
- ኤልያስና
- ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::
ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
- የይሁዳ [ኢየሩሳሌም]:
- የሰማርያ [እሥራኤል] ና
- የባቢሎን [በምርኮ ጊዜ] ተብለው ይጠራሉ::
በዘመን አከፋፈል ደግሞ :-
- ከአዳም እስከ ዮሴፍ [የዘመነ አበው ነቢያት] :
- ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል [የዘመነ መሳፍንት ነቢያት]
- ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት [የዘመነ ነገሥት ነቢያት]
- ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ [የዘመነ ካህናት ነቢያት] ይባላሉ::
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
ቅዱስ ሆሴዕ ቁጥሩ ከ፲፪ [12] ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ/ል/ክርስቶስ በ፰ መቶ [800] ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ ፲፬ [14] ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::
ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ሆሴዕ 'ዖዝያ' በመባልም ይታወቃል:: ቅዱሱ ነቢይ የቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ-ቃል ባልንጀራ የነበረ ሲሆን በ፬ [4] ነገሥታት ዘመን [ዖዝያን : ኢዮአታም : አካዝና ደጉ ሕዝቅያስ] ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናግሯል:: የትንቢት ዘመኑም ከ፸ [70] ዓመት በላይ ነው::
ከ፲፪ [ 12 ]ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሆሴዕ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራም በስፋት ተንብዩዋል:: ፲፬ [14] ምዕራፎች ያሉት የትንቢቱ ጥራዝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል:: ሆሴዕ ማለት መድኃኒት ማለት ነው:: የመዳን ትምሕርትንና ትንቢትን ሊናገር ተመርጧልና::
† ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ: በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን::
🕊
[ † የካቲት ፳፮ [26] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ [ከ፲፪ [12]ቱ ደቂቀ ነቢያት]
፪. ቅዱስ ሳዶቅ ሰማዕት
፫. ፰፻፰ ["808"] ሰማዕታት [ከቅዱስ ሳዶቅ ጋር የተሰየፉ]
[ † ወርሐዊ በዓላት ]
፩. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪. አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
፫. አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬. ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭. አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
† " ኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንመለስ:: እርሱ ሰብሮናልና: እርሱም ይፈውሰናል:: እርሱ መትቶናል: እርሱም ይጠግነናል:: ከሁለት ቀን በሁዋላ ያድነናል:: በሦስተኛውም ቀን ያስነሳናል:: በፊቱም በሕይወት እንኖራለን:: እንወቅ:: እናውቀውም ዘንድ እንከተል . . . " †
[ሆሴዕ.፮፥፩-፫] (6:1-3)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖