📌
መውሊደኞችና የቀን ቅዠታቸው[የሽርክና የተለያዩ ወንጀሎች መናኻሪያ የሆነውን መውሊድን የሚያከብሩ ሰዎችን፣ “መውሊድ አክባሪ” እያልን ከምንጠራ፣ “መውሊደኛ” ብንላቸው ጥሩ ነው - ቃላት በመቆጠብ በቀላሉ መግባባት እንችላለንና፡፡ “መውሊደኛ” በማለት ከመውሊድ ጋር 'ስላዋሀድናቸው' እነሱም ደስ ሳይላቸው አይቀርም - ቂል “በአሽሙር ሲወጉት ያደነቁት ይመስለዋል” እንዲሉ፡፡]
የሐገራችን መውሊደኞች ሸሪአዊ ማስረጃ የሌለውን መውሊድ፣ ኢስላማዊ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይወጡት ተራራ፣ የማይወርዱት ገደል የለም፡፡ ይህን ያህል ኳትነው የሚያቀርቡት ሀሰተኛ የማስረጃ ቡትቶ፣ በአሏህ ዲን ላይ ከመቀጣጠፍ የማይመለሱ ግብዞች መሆናቸውን ከማሳያት አይዘልም፡፡ መስከረም 5 ምሽት ላይ አሚኮ በትእይተን ዜና ፕሮግራሙ፣ “መውሊድና አሰተምህሮቱ” በሚል ርእስ ያቀረበው ዝግጅት፣ መውሊደኞች ምን ያህል በቀን ቅዠት የተለከፉ ከንቱዎች ለመሆናቸው አንድ ጥሩ አብነት ሆኖ አልፏል፡፡
በዚህ ዝግጅት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ድርሳናት መምህር ከሆነው ከዶ/ር እንድሪስ ሙሀመድ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ቀርቧል፡፡ ይህ ሰው የአህባሽ ዋና አቀንቃኝ የሆነው የሀሰን ታጁ የቀኝ እጅና የቀድሞው መጅሊስ የህዝብ ግንኙነት ባልደረባ የነበረ ነው፡፡
ዶ/ር እንድሪስ “ከቃል ፍች አኳያ ስለውልድት ነው የምናወራው፡፡ ውልደቱ ግን የስተዋልዶ ውልደት ላይ ያተኮረ አይደልም” ካለ በኋላ የነብዩን (አለይሂ ሶላቱ ወሰላም) “የውልደት ትኩረት” በሚከተለው መንገድይገልፃል፡-
“የስልጣኔ ውልደት፣ የስነመለኮት ትምህርት ውልደት፣ የስነ ምግባር ውልደት፣ የአኗኗር ዘይቤ ውልደት፣ የህግና ስርአት ውልደት፣ የሰላም ውልደት፣ የአብሮነት ውልደት፣ የእዝነትና የፍቅር ውልደት በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት የሚጠቅሙ የህይወት አስተምህሮቶችና ትግበራዎችን የምንዳስስበት፣ የምናይበት፣ ውልደቱ ከሪሳላ ወይም ከተልእኮ ጋር የተያያዘ ነገር ነው፡፡ የላክንህ ለአለም እዝነትን፣ መተዘዘንን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን ልታጎናፅፍ ነው የተላከው ይላል፡፡”
ሆኖም ዶ/ር እንድሪስ እዚህ ላይ የዘረዘራቸው ጉዳዮች፣ የአሏህ መልእክተኛ (አለይሂ ሶላቱ ወሰላም) የተወለዱበት ትኩረትም ሆኑ አላማዎች አይደሉም፡፡ ነብዩ ሙሀመድ፣ ነብይም ሆነ መልእክተኛ የሆኑት በውልደታቸው አይደልም፡፡ እንደተወለዱ ብቻ ሳይሆን እስከ 40 አመታቸው ድረስ ነብይ አልሆኑም፡፡ መውሊደኛው ዶ/ር እንድሪስ እዚህ የዘረዘራቸው ጉዳዮችም፣ ከነብይነት በኋላ እንጂ ስለተወለዱ የተገኙ ትሩፋቶች አይደሉም፡፡
የሀገራችንን መውሊደኞች የቀን ቅዠታቸው እንዲህ ነው የሚያደርጋቸው፤ እንዲህ ነው የሚያሰክራቸው፡፡ መውሊደኛው ዶ/ር እድሪስ፣ መውሊድን ገበያ እንደምትወጣ ሴት አዳሪ ኳኩሎ ለማቅረብ ሲል፣ የነብይነት ትሩፋቶችን የውልደት ቱሩፋቶች አድርጎ አቀረባቸው፡፡ የመውሊድ ፍቅር ሰዎቹን እንዴት በቀን ቅዠት እያሰከራቸው አንደሆነ ልብ በሉ፡፡
ማንም እንደሚያውቀው፣ የአሏህ መልእክተኛን (አለይሂ ሶላቱ ወሰላም) አሏህ ነብይ አድርጎ የላካቸው እድሜያቸው 40 አመት እንደ ሞላ ነው፡፡ አሏህ በተከበረው ቁርአኑ፣ “ለአለማት እዝነት አድርገን እንጂ አልላክንህም” (አል-አንቢያ፣ 107) ያላቸው፣ እድሜያቸው 40 አመት ሞልቶ በነብይነት ከላካቸው በኋላ ነው፡፡
ከዚህም በላይ መውሊደኛው ዶ/ር እድሪስ በከፍተኛ ድፍርት ተሞልቶ፣ እንዲህ ይላል፡- “በውልደታች የተከሰቱት፣ ከውልደትም እስከ አርባ አመታቸው ድረስ በምን ሁኔታ ነበር ነብዩ ሙሀመድ የኖሩት -
በጣም አስፈላጊው ዘመን እስከ አርባ አመት የኖሩበት ዘመን ነው፡፡ እንደ ሰው የኖሩበት ዘመን ስለሆነ” ይላል፡፡ ይህን የሚለን ግን፣ ከላይ ከፍ ሲል ነብይ ሆነው በመላካቸው የተገኙትን ቱሩፋቶች የመወለዳቸው ቱሩፋቶች አስመስሎ ካቀረበልን በኋላ ነው፡፡ በሌላ በኩል “
በጣም አስፈላጊው ዘመን እስከ አርባ አመት የኖሩበት ዘመን ነው” ብሎ ለወሸከተው፣ አንዲትም ማስረጃ ወይም ቱረፋት አልነገረንም፡፡
ወይ ቅዠት! ከሁሉ ክፉው ቅዠት ደግሞ የቀን ቅዠት ነው፡፡ የሌሊትን ቅዠት በመባነን ወይም በንጋት ይገላገሉታል፡፡ የቀን ቅዥትን ግን ምን ያደርጉታል? ሲቃዡ መኖር ብቻ! የመውሊድ ፍቅር እንዲህ ነው የሚያስቃዥ! ቢድአ እንደዚህ ነው - በስሜት አረቄ በማስከር፣ በማይጨበጥ የቅዠት አለም ውስጥ እንድትኖር ያደርግሀል፡፡
መውሊደኛው ዶ/ር እንዲህ በማለት ይቀጥላል፡-
“የነብይነት ማእረግ ከተሰጡ በኋላ ያለው ወቅት፣ መለኮታዊ እገዛም አለ፤ ተልእኮም ተሰጥቷቸዋል፤ አድናቆትህን የምትቸረው ቢሆንም፣ ከአርባ አመት በፊት ግን የነብዩ ሙሀመድ ስብእናና ማንነት በራሱ በዚህ የውልደት በአል የምናስተውለው ነው፡፡ ከአርባ አመት በፊት የነበራቸው ማንነት ነው ለነብይነትም እንዲታጩ ያደረገው፡፡”
ከዚህ የቀን ቅዠት ንግግር ውስጥ ሁለት አደገኛ ነጥቦችን እናገኛለን፡፡ አንደኛ ነገር፡- መውሊደኛው ዶ/ር እድሪስ ከልደታቸውም ቀን አልፎ እስከ አርባ አመት ያለውን የእድሜያቸው ጊዜ ክፉኛ ከፍ-ከፍ አድርጎታል፤ ክፉኛ ሰቃቅሎታል፡፡ በዚህ አያያዙ ነገ ከነገ ወዲያ “የነብዩ አስረኛ አመት የመውሊድ በአል”፣ “የነብዩ ሀያኛ አመት የመውሊድ በአል”፣ “የነብዩ ሰላሳኛ አመት የመውሊድ በአል”… የሚል ተጨማሪ፤ ቢድአ ይዞ ብቅ እንደማይል ምን ዋስትና አለ? መውሊደኞቹ መጅሊሶች “የኡለሞች መውሊድ” በማለት ተጨማሪ ቢድአ መስርተው ማክበራቸውን አትርሱት እንጂ!
ሁለተኛ ነገር፡- በተማኙ ጅብሪል አማካኝነት ቁርአን ከሰባቱ ሰማያት በላይ ወደ መልእክተኛው (አለይሂ ሶላቱ ወሰላም) የወረደበትን፣ የተውሂድ ፓውዛ የተንቦገቦገበትን፣ የጃህልያ ስርአትና ስፍር ቁጥር የሌላቸው የአረቡ ምድር ጣኦታት የተንኮታኮቱበትን፣ የኢስላም ብርሀን ከመካ መንደር በአራቱም አቅጣጫ ወደ አለም የተሰራጨበትን፣ የአሏህ በብቸነት ተመላኪነት የበላይ የሆነበትን፣ የከሀድያኑ የሮምና የፋርስ ግዛቶች ለኢስላም እጅ የሰጡበትን… ባጭሩ ከአርባ አመት በኋላ ያለውን የነብይነት ጊዜ፣ “አድናቆትህን የምትቸረው ቢሆንም” በማለት ከነብይነት በፊት ካለው ስኬታቸው ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ ለማድረግ ሞክሯል - መውሊደኛው ዶ/ር እድሪስ፡፡
አሁን ይሄ ምን ይባላል? ይህን መሰሉ የቀን ቅዠት በምን ይገለፃል? በቁርአንም ሆነ በሀዲስ ምንም ማስረጃ በሌለው የመውሊድ ቢድአ ከንቱ ፍቅር ተለክፈው፤ በቀን ቅዠት የሚሰቃዩት እነዚህ የሀገራችን መውሊደኞች፤ ቆሻሻ የሆኑ የሽርክ ተግባራት መናገሻ የሆነውን መውሊድን ጥሩ አስመስሎ ለማሳየት የማይፈነቅሉት የሀሰት ድንጋይ፣ ፀያፍ የሆኑ ወንጀሎች መናኻሪያ የሆነውን መውሊድ ለማቆንጀት የማይጠቀሙበት የውሸት ኮስሞቲክስ የለም፡፡ ቢድአን አምልኮ አድርጎ ከያዘ ሰው የበለጠ እውር፣ ስሜቱን አምላክ አድርጎ ከያዘው የበለጠ ጠማማ ማን አለ?
“ዝንባሌውን አምላኩ አድርጎ የያዘውን፣ አላህም ከዕውቀት ጋር ያጠመመውን፣ በጆሮውና በልቡ ላይም ያተመበትን፣ በዓይኑም ላይ ሺፋን ያደረገበትን ሰው አየህን! ታዲያ ከአሏህ በኋላ የሚያቀናው ማነው? አትገሠጹምን?” (አል-ጃሲያህ፣ 23)
መውሊደኛው ዶ/ር እድሪስ ስለመውሊድ የቦተለከው የቀን ቅዠት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በፕሮግራሙ የተላለፈውን “ክሊፕ” እያስፈለኩ ነው፡፡ ከተገኘ በጋራ የምናየው ይሆናል፡፡
ዝግጅት/በዶክተር ጀማል ሙሐመድ - ሀፊዞሁሏህ -
https://t.me/alateriqilhaqكن على بصيرة