#ተሰውፍ (ሱፍይነት) ክፍል-1
ተሰዉፍ ለዘመናት የእስልምና ትክክለኝነት መለኪያ ሆኖ ቆይቷል፤
አሁንም ነው፡፡ እንደ አንዳንድ ምሁራን የሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች
ሰፈፍ ነውም፤ በእስልምና ውስጥ ያሉ ወደ አላህ መሄጃ መንገዶች
የሚገናኙበት ብቻ ሳይሆን ከእስልምናም ውጭ ያሉ፡፡
ጀላሉዲን ሩሚ በታዋቂው ተሰዉፍን በገለፁበት ምሳሌያቸው
ስለአራት የተለያዩ አገራት ተጓዦች ታሪክ ይነግሩናል፡፡ እነዚህ አራት
ተጓዦች ያለቻቸውን አንዲት ሳንቲም ለምግብነት ሊያውሉ ፈለጉና
ክርክር ገጠሙ፡፡ አንድ በአጠገባቸው የሚያልፍ የቋንቋ ሰው
ውዝግባቸውን አድምጦ፣ ሳንቲሙን ከሰጡት ሁሉንም የሚያረካ
ምግብ ይዞላቸው እንደሚያመጣ ይነግራቸዋል፡፡ ሳንቲሙን ሰጡት፣
እርሱም ለአራቱም አራት ዘለላ ወይን ይዞላቸው መጣ፡፡ አራቱም
በመገረም ሁሉም ሲፈልጉት የነበረው ነገር ወይን እንደነበረ ተናዘዙ፡፡
ምንም እንኳ አንድ አይነት ነገር ቢፈልጉም፣ ከቋንቋ ጋ በመጡ
የተለያዩ ቅርፊቶች በእውነተኛው ነገር ላይ እንዳይግባቡ አድርጓቸዋል፡
፡ በእርግጥም ሁላችንም የአላህ ባሪያዎች ነን፤ እርሱን ብቻ ነው
የምንፈልገው፡፡
ሆኖም ይህ ድንቅ ሃይማኖታዊ ቅስቃሴ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ
በመጣው ቅርፃዊነት እና ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች እርሱ ራሱ
ምንነቱ እና ማንነቱ ተሸፍኗል፡፡ የእስልምና ሃይማኖት ኩራት ሆኖ
ፍቅርንና እዝነትን የሰብአዊነትን ቀንዲል ይዞ ሃይማኖቱን ለሰዎች
እንዳላዳረሰ አሁን ትክክለኝነቱን ሁሉ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከቱትውልዶች መጥተዋል፡፡ ሆኖም ይህ ለተሰዉፍ አዲስ አይደለም፡፡
ታሪኩ እንደሚያሳየው ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ ሆኖለት የደረሰበት ደረጃ
ላይ አልደረሰም፡፡ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማሳለፍ ነበረበት፡፡
ተሰዉፍ እንደ ቀድሞው አሁንም ለሰው ዘር፣ ቢያንስ ለእስልምና
ሃይማኖት ተከታዩ አስፈላጊ ነው፡፡ ቅርፃዊነት ያቀረበው ተግዳሮት
ለተሰዉፍ ብቻ አይደለም፣ ለሰው ዘርም ጭምር እንጂ፡፡ ቅርፃዊነት
በምንነቱ ቅርፍታዊ በመሆኑ ለልዩነት የተመቸ ነው፡፡ ሰው ከቅርፁ
በታች ያለውን ማየት ካልቻለ እና በውጭ ከቆየ አንድነትን ከማየት
ይልቅ ልዩነትን ማየቱ አይቀርም፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) በታዋቂ
ንግግራቸው ሰዎች በፊጥራ (አምላክን በማወቅ ተፈጥሯዊ ይዞታ
ላይ) ተወልደዋል፤ ነገር ግን አካባቢው ከወላጆቹ ጀምሮ ከባባዊው
ነባራዊ ሁነቶች ይሸፍነዋል እንዳሉት፣ በዚህ ከባቢያዊ ቅርጻዊ ነገሮች
ላይ ብቻ ካተኮርን ልዩነቶቻችንን ማየት ብቻ አይደለም፤
እውነተኛውን ተፈጥሯዊ መቅኔው ያመልጠናል፡፡
ሌላ ምሳሌ ለመስጠት፣ አላህ (ሱ.ወ) በቅዱስ ቁርአኑ የሰውን ልጅ
ከተለያዩ ጎሳዊ፣ ነገዳዊ እና ሃይማኖታዊ ማንነቶች እንደፈጠረ
ይናገርና፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ወተዋወቅ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡
ከሰዎች ሁሉ በላጩ ግን አላህን ተጠንቃቂው እንደሆነ ያሰርጻል፡፡
ቅርጻዊነት ጎሳዊ፣ ነገዳዊ፣ ብሔራዊ፣ ሃይማኖታዊ ልዩነቶች ላይ
አተኩሮ እውነተኛውን ነገር- መተዋወቁን እና አላህን ተጠንቅቆ
ህይወቱን መምራቱንና ለሰው ዘር በጎ መሆኑን ይዘነጋል፡፡
ይቀጥላል..........
https://t.me/YASIRAJEL_ALEM